ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

ግልጽ ደብዳቤ ለወ/ሮ ሙፈሪያት ከሚል የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤና የደኢህዲን ሊቀመንበር

ለክብርነትዎ! በቅድሚያ የከበረ ሰላምታዬን አቀርባለሁ፡፡ ይህንን ጽሑፍ ያዘጋጀሁት ሰሞኑን በዳውሮ ዞን ተርጫና ዋካ ከተሞች የተፈጠረውን የሕዝብ ቁጣና አመጽ ምክንያቱን ከሕዝብ ተረድተው የመፍትሔ አቅጣጫ ለማመላከትና ችግሩን ለመቅረፍ ወደ አካባቢው ያቀናሉ የሚል ወሬ ስለሰማሁ ይህችን ደብዳቤ ልጽፍልዎት ወሰንኩ፡፡ በዚህች ጽሑፌ የችግሩ መነሻ ምክንያት ምን እንደሆነ ትንሽ ወደ ኋላ ሄድ ብዬ እጠቁምዎታለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ በተፈጠረው ሁኔታ ህይወታቸውን ላጡት ወገኖቼ የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን እገልጻለሁ፡፡ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን እመኛለሁ፡፡

ለመግቢያ ያህል የዳውሮ ሕዝብ ላለፉት በርከት ያሉ ዓመታት ለመንግሥት የተለያዩ ጥያቄዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ፍትህ ዴሞክራሲና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የእኩል ተጠቃሚነት መብት አለመከበር፣ የወረዳ ማዕከል ወደ ሚያማክልበት ሥፍራ ይዛወርልኝ ጥያቄ፣ የተጨማሪ ወረዳ ጥያቄ፣ የመንገድና የሌሎች መሠረተ ልማት ጥያቄዎችን በየአስተዳደር እርከኑ ሲያሰማ ቆይቷል፡፡ መፍትሔ የሚሰጥ አቤቱታ ሰሚ አካል በማጣቱ ምናልባት እሰማ ይሆን ወይ በሚል የተከበሩ የሀገር ሽማግሌዎችንና የሐይማኖት አባቶችን መርጦ በመወከል ወደ ክልል አስተዳደርና ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በተደጋጋሚ በመላክ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

ጥያቄው ምላሽ ባለማግኘቱ የተነሳ በተደጋጋሚ የዋካ ከተማ፣ ሎማ ወረዳ የዲሳ አካባቢ ሕዝብ፣ የጌና ወረዳ የወልደሃኔ አካባቢ ሕዝብ፣ በቶጫ ወረዳ የቶጫ ከተማ ሕዝብ በልማትና ከወረዳ ጋር በተያያዘ ሕዝባዊ አመጽና ትግል ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ታስሯል፡፡ ተንገላቷል፡፡ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ ተከፍሎበታል፡፡

የተከበሩ አፈ ጉቤና የደኢሕዴን ሊቀመንበር ሆይ! ከሕዝብ ትግል ጋር በተያያዘ አንድ እጅግ ሲያሳዝነኝ የቆየ ነገር ላንሳልዎት፡፡ የዳውሮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አለው፡፡ የማረሚያ ቤትም አለው፡፡ ይሁን እንጂ የልማት ጥያቄ አንስታችኋል የተባሉ ወንድሞቻችን ግፍ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ምንም ፍላጎታቸው ሳይጠየቅ ተገድደው በግዞት ወደ ሌላ  ዞን / አካባቢ  ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲከሰሱና ወደዚያው ማረሚያ ቤት ተዛውረ እንዲታሰሩና በቅርብ ሆነው ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ስንቅ እንዳያገኙ ተደርጓል፡፡ የሐስት ማስረጃ በገንዘብ እየተገዛ፣ ሕግ ወደ ጎን ተትቶ  ዳኞች ከወቅቱ የደኢሕዴን ሊቀመንበርና የፖለቲካ ክፍል ኃላፊ ፖለቲካዊ መመሪያ ተሰጥቷቸው  ያለርህራሄ በጭካኔ ምንም ወንጀል ባልሰሩ ሰዎች ላይ አምስት ዓመት ፈርደውባቸው ወላይታ ሶዶ ማረሚያ ቤት በእሥራት ተቀጥተዋል፡፡ እጅግ የሚያሳዝን ነው፡፡ ከሕዝብ አደራ የተሰጠው አመራር በሌላ ወገኑ ላይ እንዲህ ያደርጋል? የሚገርመው ሁለቱም በሥልጣን ላይ አሁን የሉም፡፡  ወደፊት እግዚአብሔርና ጊዜ አንድ ቀን በሕግ ፊት ተጠያቂ ያደርጋቸዋል፡፡

ይህ የሕዝብ በደል ያንገሸገሸው መምህር የኔሰው ገብሬ ወጣቶችን አስተባብረሃል ሕዝብን አነሳስተሃል ተብሎ አላግባብ ታስሮ ተቀጥቷል፡፡ የሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ፍጹም አንባገነን በሆኑት ጥቂት የዞንና የክልል አመራር መጨፍለቁና የሕዝብ መንገላታት አንገሽግሾት ራሱ ላይ ቤንዚን አርከፍክፎ በእሳት በመቃጠል ዴሞክራሲያዊ ትግሉን የበለጠ አቀጣጥሎት አልፏል፡፡ የተከበሩ አፈ ጉባኤ ይህ የሰሞኑ የወጣቶች እንቅስቃሴና አመጽ የተዳፈነ ብሶት የወለደው ነው፡፡ መፍትሄውም እንደዚሁ ጥናትና ግልጽ የመንግሥት ምላሽ የሚሻ ነው፡፡

ለመግቢያ ያህል ይህን ካልኩ ወደ ሰሞኑን የወጣቶች / ላካይቶዎች አመጽ ላምራ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ በወላይታና በዳውሮ ዞን አዋሳኝ ሆኖ የሚፈሰው የኦሞ ወንዝ ግልገል ግቤ ቁጥር 3 ግድብ ተሰርቶበታል፡፡ ግድቡ በሀገር ደረጃ ያለውን የኃይል ምንጭ እጥረት ለመቅረፍ ከሚጫወተው ሚና በላይ ለሀገራችን የሚያበርክተው የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ከፍ ያለ ነው፡፡ የተጠራቀመው ውሃ ከ2/3ኛው በላይ የተኛው ወደ ዳውሮ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ የለበቂ የንብረት ካሳ የተባረሩትን አርሶ አደሮች በደል ሳይጨምር ሁለት ጉዳቶችን አስከትሏል፡፡

የመጀመሪያው ከዳውሮ ተርጫ ዋካ ወላይታ ሶዶ አዋሳ የሚወስደውን የጠጠር መንገድ ከ50 ኪ.ሜ. በላይ አርዝሞታል፡፡ ሁለተኛው አይተኬውን የዳውሮ ቅርስ የሆነውን የካዎ ሃላላ የድንጋይ ካብ አጥር ላይ የግድቡ ውሃ ተኝቶበታል፡፡ በዚህ የተነሳ ታሪካዊ ቅርሱ ተጎድቷል ከጥቅም ውጭ አድርጎታል፡፡ ወደ አዋሳ የሚወስደውን የመንገድ ርዝማኔ ከግንዛቤ አስገብቻለሁ ያለው የኢሕአዴግ / ወያኔ መንግሥት ዳውሮን ከአዋሳ የሚያገናኝ አዲስ የጠጠር መንገድ እገነባለሁ ብሎ ቃል ይገባል፡፡ የሚገነባውም አዲስ መንገድ ዳውሮ ተርጫ ወልደሃኔ ዱርጊ ዱራሜ አዋሳ እንደሚሆን ለሕዝብ ይፋ ተደርገ፡፡ ይህ ሊሰራ ቃል የተገባው የጠጠር መንገድ ወደ አዋሳ ለመጓዝ በወላይታ ሶዶ በኩል ከሚያልፈው መንገድ ፍጹም አጭር ነው፡፡

ሕዝቡም ተደሰተ እግዚአብሔርንና መንግሥትን አመስግኖ ውጤቱን ይጠብቅ ጀመር፡፡ ካድሬዎቹም መንግሥታችን መንገድ በብዙ ሚሊዮን ብር ሊገነባ ነው የምርጫ ድምጽ ስጡን ንቧን ምረጡልን ብሎ ስበኩ፡፡ ሕዝቡም ካድሬውን መንግሥትን አምኖ አደረገ፡፡ ከዚያ ቢጠበቅ ቢጠበቅ ምንም የመንገዱ ወሬ የለም፡፡ ወረዳ አመራር ቢጠየቅ ዞን ያውቃል ሆነ መልሱ፡፡ ዞን ሲጠየቅ ክልል ያውቃል እኔ አላውቅም ይል ገባ፡፡ ይህ ጉዳይ እያደር ወጣቱን ያስቆጣው ጀመር፡፡

የዳውሮ ወጣቶች ይህ ቃለአባይ የሆነ ውሸተኛ መንግሥት አበሳጫቸውና ምን እናድርግ ብለው መክረው ጥንት አያቶቻችን ከጠላት ራሳቸውን ለመከላከል የዳውሮን ዙርያ መለስ በድንጋይ ካብ አጥረዋል፡፡ ስለዚህ እኛም የእነርሱን የአያቶቻችንን ወኔ አንግበን ይህን መንገድ በዶማ በአካፋና ባለን ኋላቀር መሳሪያ መሥራት አለብን ብለው ይወስናሉ፡፡ ወደ ተግባርም ይገባሉ፡፡ ባለፈው ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም የመጀመሪያውን የመንገድ ሥራ ዘመቻ እጅግ በሚደንቅ ወኔ ፍቅርና አንድነት አከናወኑ፡፡ ላባቸውን አፈሰሱ፡፡ የሀገር ሽማግሌዎች የሃይማኖት አባቶች የተሳተፉ ሲሆን ሴቶች እናቶቻችን ያላቸውን አዘጋጅተው ስንቅ ቋጥረው ከወጣቶቹ ጎን ተሰልፈዋል፡፡ ቃላት የማይገልጸው ትልቅ ሥራ ተሰራ፡፡

ይህንን የመሰለ የወጣቶች / ላካይቶዎች  እልህ የተሞላውን የሥራ ዘመቻ የሕዝብ ተሳትፎ ድካምና ውጤት የደቡብ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ተሳለቀበት፡፡ ቀደም ሲል የነበረ መንገድ በሕዝቡ ተሳትፎ ተጠገነ የሚል ውሸት የሆነ ዜና በፌስ ቡክ አካውንቱ አሰራጨ፡፡ ከላይ በመግቢያው ላይ በጠቀስኳቸው መነሻዎች ሆድ ብሶት የነበረውን ወጣት ዜናው የበለጠ አበሳጭቶት አስቆጥቶት ወደ አመጽ መሩት፡፡ መጣቱ የራሱን ንብረት መልሶ አጠቃው፡፡

አመጽ በምንም መስፈርት አይደገፍም፡፡ የሕዝብንም ሆነ የግለሰብን ንብረት ማቃጠል፣ ከየቢሮው  መረጃ መቀዳደድና ማውደም ፍጹም ተገቢ አይደለም፡፡  ሕገ ወጥነት ነው፡፡ ስህተት ነው፡፡የመረጃና ማስረጃ ማውደም ተግባር የተከናወነው በወጣቶች / ላካይቶዎች ፍላጎት ብቻ የሆነ ነው ብዬ ለማመን ይቸግረኛል፡፡ ሌላ ብዙ ለማለት መረጃ የለኝም፡፡ ሌላውና ትልቁ ችግር ሕዝብና የፖለቲካ አመራሩ በተለያዩ በርካታ ምክንያቶች  ሆድና ጀርባ ሆኗል፡፡ በፍጹም ላይስማሙ ተለየይተዋል፡፡ ይሄ ችግሩን አባብሶታል፡፡

የዳውሮ ካድሬዎና አመራሮች አሁን ሀገራችን ውስጥ ለውጥ ለማምጣት ትግል ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑ ማወቃቸው ያጠራጥረኛል፡፡ ምክንያቱም ከወጣቶች ለሚቀርብላቸው ጥያቄ የሚሰጡት ግብረ መልስ ይገርመኛል፡፡  ዶክተር ዐቢይ አህመድ በአጭር ጊዜ ያመጡትን ለውጥ በመደገፍ ሰልፍ ለማድረግ ወጣቶች እንደተቸገሩ አውቃለሁ፡፡ ሰልፍ ማድረግ አትችሉም ብለው ማስታወቂያ በመለጠፍ ወጣቶችን ያስፈራሩ ወረዳዎች አሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው በሀገራችን ላይ እየመጣ ያለውን ለውጥ የማይደግፍ ብቻ ሳይሆን ለማደናቀፍ እንዲሁም ወጣቱ ሕዝቡ ጸረ ለውጥ እንዲሆን እየሰሩ ያሉ ይመስለኛልና ይህንን የማስተካከል ሥራ ሊሰራ ይገባል፡፡

የተከበሩ የደኢህዴን ሊቀመንበር አንድ ትክክለኛ መረጃ ልስጦት፡፡ እውነትነቱን አጣርተው አረጋግጠው  ለዚህ ሕዝብ እንደሚያዝኑ እርግጠኛ ነኝ፡፡ የዳውሮ ተርጫ ወልደሃኔ ዱርጊ ዱራሜ መንገድ በፌዴራል ደረጃ የቅየሳ ሥራ ተሰርቷል፡፡ የመንገዱ ግንባታ  ሥራ እንዲከናወን የጨረታ ማስታወቂያ በ2007 ዓ.ም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በይፋ ወጥቷል፡፡ በወቅቱ የነበሩ የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስትርን ይጠይቁ፡፡ ስማቸውን ላለማንሳት ብዬ ነው፡፡ የአዲሱ የለውጥ ኃይል አጋዥ በመሆናቸው  በአቅራቢያዎ አሁንም አሉ፡፡ መስሪያ ቤታቸው ያወጣውን ጨረታ በሌላ ማስታወቂያ ጨረታውን  ቶሎ ሰርዝ ተብለው ተገድደው እንዲሰርዙ ተደርጓል፡፡ ለምን ይህ እንደተደረገና ይህን እንዲፈጽሙ ማን እንዳዘዛቸው ይጠይቋቸው፡፡ የመንገድና ትራንስፖርት ሚኒስትሩ ታዘው ነው ሥራው የቆመው፡፡ የወቅቱ የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስትር ለሕዝብ ይፋ ባያደርጉ እንኳን ለእርስዎና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እውነቱን ይናገራሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ መንገዱ እንዳይሰራ የተቆለፈው በፌዴራል ደረጃ ነው፡፡ መፍትሔው ቁልፉን ፈትቶ ጨረታው እንደገና እንዲወጣ አድርጎ ሥራውን ማስጀመር ብቻ ነው፡፡ ቢቻል ይህንን ሆን ብሎ የቆለፈውን ግለሰብ ሕዝብን ይቅርታ እንዲጠይቅ ማድረግ ነው፡፡

ችግሩን ለመፍታትና ለሕዝቡ ፍትሃዊ ውሳኔ እሰጣለሁ የሚል አመራር ፌዴራል ደረጃ ያለ ባለሥልጣን ብቻ ነው፡፡ ችግሩ በክልል ደረጃ አይደለም፡፡ እርስዎ ደግሞ እንደ አጋጣሚ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ እንደመሆንዎ መጠን ያልዎትን ሥልጣን ተጠቅመው ሁሉንም ነገር ወደ መንደሬ በሚል ኢትዮጵያዊነት በጎደለው መንደርተኛ አንባገነን የተዘጋውንና የተሰረዘውን መንገድ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጋር ተወያይተው ከቆመበት ቢያስቀጥሉ ፍትሃዊ የሆነ አመራር /  መሪ /  ያስብልዎታል፡፡ ችግሩን ደርሰውበት መፍትሔ ይሰጡ ዘንድ የዚህን ደብዳቤ ግልባጭ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አደርጋለሁ፡፡

አንዲት ነገር ላክልና ላብቃ፡፡ፌዴራል ፖሊስ በተደጋጋሚ ዳውሮ ገብቶ ያውቃል፡፡ ጊዜያዊ ማስታገሻ በመሆን አመጹን ይበትናል እንጂ ዘለቄታዊ መፍትሄ አይሰጥም፡፡ በመሆኑም በዚህ የዳውሮ ተርጫ ጉዞዎ ከሕዝቡ በተለይም ከወጣቶች ለሚነሱ ጥያቄዎች ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ተጨባጭ ምላሽ የሚሆን ነገር ለማቅረብ ይዘጋጁ፡፡ ፖለቲካዊ የሆነ የውሸት መልስ መድረክን ለመሹለክ ተብሎ የሚሰጥ የፈጠራ ወሬ ሕዝብንና መንግሥትን የለየው በመሆኑ እንደ አንድ የለውጥ ኃይል ይህ ከእርስዎ አይጠበቅም፡፡ በመሆኑም  ህዝቡን ያዳምጡት ተጨባጭ ምላሽ ይስጡት፡፡

በመጨረሻም የግል አስተያየቴን ላስቀምጥና ላብቃ፡፡ የዳውሮ ወጣቶች/ ላካይቶዎች ሕግና ሥርዓትን የሚያውቁና የሚያከብሩ ናቸው፡፡ ዳግም እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ እንዳይከሰት የየበኩላቸውን ድርሻና ኃላፊነት እንደሚወጡ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በእርስዎ በኩል የሚከተሉትን ነጥቦች ቢያዩዋቸው በጎ ነው፡፡

ሕዝብን የበደሉ፣ ሕዝብ የጠላቸውን አመራሮች በሕዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎ ከቀበሌ እስከ ዞን አመራር ድረስ ያሉት ካድሬዎች ገምግመው ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ቢያደርጓቸው? ሕዝብን የበደሉ የመዘበሩ የዘረፉትን ሌቦች ከሕዝብ በሚቀርበው መረጃ ትክክለኛነቱ በኦዲት ተጣርቶ ወደ ሕግ እንዲቀርቡ ቢያደርጉ? አውቀውም ይሁን ሳያውቁ አዲስ እየመጣ ያለውን ለውጥ ወደ ዴሞክራሲ እየሄድን ያለንበትን መንገድ ለመዝጋት፣ ጉቶ ለመሆን፣ ከቻሉም  ዴሞክራሲያዊ ትግሉን ለመቀልበስ የሚሰሩ ካድሬዎች  አሉና ከመንገድ ላይ ዞር እንዲሉ ማድረግ ቢችሉ? የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብት እንደመሆኑ ማንም ካድሬ መከልከል እንደማይችል በይፋ ካድሬዎችን ቢመክሩ ቢያስተምሩ? በየመዋቅሩ በምትካቸው የሕዝብ ተቀባይነትና አመኔታ ያላቸው፣ የተማሩ፣ ጨዋ የሆኑ፣ ሕዝብን በተለይም ወጣቱን ማዳመጥ የሚችሉ ሰዎች የድርጅትዎ አባል መሆኑ እንደ መሥፈርት ሳይታይ በሕዝብ ቀጥጠኛ ተሳትፎ እንዲተኩና አመራሩን እንዲይዙ ቢያደርጉ? በዞኑ መረጋጋት ከመምጣቱም ባሻገር ቀጣይ ሀገራችንን ፍጹም ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ የሚደረገውን የለውጥ ትግል  ያሳድገዋል፡፡ ሕብረተሰቡም መጠነኛ ፋታ ያገኛል እርስዎንም ያመሰግንዎታል ብዬ አምናለሁ፡፡

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ኢትዮጵያ ሀገራችንን እግዚአብሔር ይባርክ!

ግልባጭ ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር   ዐብይ አህመድ

አዲስ አበባ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሀገሪቷን ከጥፋት ለመከላከል ፣ ህግን ለማስከበር ፌዴራል ፖሊስ ተግባሩን ያጠናክራል
0Shares
0
Read previous post:
ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት እና የተጀመረውን የለውጥ ሂደት የሚያደናቅፍ እንቅስቃሴ የሕዝብ ጠላትነት ተግባር ነው! (ሰማያዊ ፓርቲ)

ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ የቁርጥ ቀን ልጆች በከፈሉት መራር መስዋዕትነት ባለፉት አራት ወራት...

Close