“Our true nationality is mankind.”H.G.

ባንኮች በሁለት ሳምንት ውስጥ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ መንዝረዋል

Foto ilustracion dolar Foto: Fernanda Corbani

በጥቁር ገበያውና በባንኮች መካከል ያለው የምንዛሪ ልዩነት የቱንም ያህል ቢሆን፣ በባንክ በኩል መመንዘር የዜግነት ኃላፊነትን እንደመወጣት የሚቆጠር ነው፡፡ በርካቶችም እንዲህ ባለው በጎ አመለካከት ተነሳስተው የውጭ ገንዘቦችን በባንክ በኩል እንደመነዘሩ ይገምታል፡፡ ምንጭ ሪፖርተር

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በቅርቡ የውጭ ገንዘብ በእጃቸው የሚገኝ ዜጎች ወደ ባንክ እንዲያስገቡ ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡ ይህንኑ ተከትሎም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የግል ባንኮች ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በሁለት ሳምንት ውስጥ እንደመነዘሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማሳሰቢያና ማስጠንቀቂያ ተከትሎ በጥቂት ቀናት ውስጥ በእጃቸው የሚገኘውን የውጭ ገንዘብ ከመነዘሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ውስጥ፣ የታክሲ ሾፌሩ ወጣት ምትኩ አንዱ ነበር፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማሳሰቢያ በተላለፈ ማግሥት ወደ ባንክ ጎራ በማለት አስቀምጧቸው የነበሩ የሁለት አገሮች የውጭ ገንዘቦችን መንዝሯል፡፡

ወጣት ምትኩ የባንኩ ሌሎች ደንበኞችም ዶላርን ጨምሮ የበርካታ አገሮችን መገበያያ ሲመነዝሩ እንደታዘበ ይገልጻል፡፡ የውጭ ገንዘቦች ያሏቸው በርካታ ነዋሪዎች፣ በግልና በመንግሥት ባንኮች በኩል ከሰሞኑ የታየውን ያህል መጠን ያለው ገንዘብ የመነዘሩበት ወቅት እንደሌለ ሪፖርተር ካነጋገራቸው የባንክ ኃላፊዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከወትሮው ባልተመለደ ሁኔታ ብዛት ያለው የውጭ ገንዘብ ይዘው የሚቀርቡ ደንበኞች የተበራከቱባቸው ባንኮች፣ ለዚሁ አገልግሎት በቅርንጫፎቻቸው ውስጥ ራሱን የቻለ የውጭ ገንዘቦች ማስተናገጃ መስኮት ከፍተው ማስተናገድ ጀምረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የውጭ ምንዛሪ አገልግሎት ሰጥተው የማያውቁ የባንክ ቅርንጫፎች ሳይቀሩ የውጭ ገንዘቦችን የመመንዘር ዕድል እንዳገኙ ታይቷል፡፡

ከአንዳንዶቹ ቅርንጫፎች እንደሚነገረው፣ ለመንፈቅ ዓመት ያህል የውጭ ገንዘብ ይመንዘርልን ጥያቄ የሚያቀርብላቸው ደንበኛ አያገኙም ነበር፡፡ አንዳንዶቹ የመንዝሩልኝ ጥያቄ እንደማያስተናግዱም ሲገለጽ ይመደጣል፡፡ በተለይም የገንዘቡ መጠን አነሰ፣ ከ100 ዶላር በታች አንቀበልም የሚሉ፣ ለመመንዘር የሚመጣውን ሰው ወዝፈው የሚያውሉ፣  የመታወቂያና የሌሎች ሰነዶችን የኮፒ ጋጋታና መሰል ጣጣ የሚያበዙት ባንኮችና በዚህ የተመረሩት ተገልጋዮች፣ ወደ ባንክ መሄድ ከማይፈልጉባቸው ምክንያቶች ውስጥ እንዲህ ያሉትን የተንዛዙ ቢሮክራሲዎች ለመሸሽ እንደሆነ ሲጠቅሱ ይደመጣሉ፡፡ ዋናውና መሠረታዊው ወደ ባንኮች ለምንዛሪ የማይሄዱበት ምክንያት ግን በባንክና በጥቁር ገበያው መካከል የነበረው የምንዛሪ ዋጋ ልዩነት ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በባንኮቹና በጥቁር ገበያ ዘርዛሪዎች መካከል ያለው የዋጋ ልዩነት በመጥበቡ፣ በርካቶች ወደ ባንኮች በማቅናት ሲዘረዝሩ ታይተዋል፡፡ በቀን የሚመነዘረው የውጭ ገንዘብ ብዛት አስገራሚ ሆኗል፡፡ ባለፉት 15 ቀናት ውስጥ ወደ ባንኮች  የሄደውና የውጭ ገንዘብ የዘረዘረው ተገልጋይ ቁጥር ከዚህ ቀደም ቀርቦ የማያውቅ መሆኑን ከተለያዩ ባንኮች ያገኘነው መረጃ ያረጋግጣል፡፡   

በሁለት ሳምንታት ውስጥ ከሌሎች ባንኮች ይልቅ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ገንዘቦች ቁጥር ስለመመንዘሩ የሚጠቅሰው ንግድ ባንክ፣ በየዕለቱ በአማካይ ከሦስት ሚሊዮን ዶላር በላይ እየመነዘረ ስለመሆኑ አስታውቋል፡፡ እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ በነበረው መረጃ መሠረት፣ ንግድ ባንክ ብቻውን ወደ 50 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ መመንዘሩን ለመረዳት ተችሏል፡፡

የግል ባንኮችም የውጭ ገንዘቦችን ለመመንዘር የሚመጡ ደንበኞች ቁጥር ከዚህ ከቀደም ባልታየ መጠን ማስተናገዳቸውን እየገለጹ ነው፡፡ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ንግድ ባንክና 16ቱ የግል ባንኮች በጥቅሉ ወደ 100 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ገንዘብ እንደመነዘሩ ተገምቷል፡፡

ሪፖርተር ከተለያዩ ባንኮች ያሰባሰበው መረጃ ይህንኑ የሚጠቁም ሲሆን፣ በዚህ ጉዳይ መረጃ ከሰበሰብንባቸው አምስት የግል ባንኮች በጥቅሉ ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ ምንዛሪ ስለማከናወናቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ አዋሽ ባንክ 11 ሚሊዮን ዶላር፣ ኅብረት ባንክ አምስት ሚሊዮን ዶላርና አቢሲኒያ ባንክ 6.8 ሚሊዮን ዶላር መመንዘራቸው  ታውቋል፡፡ ብርሃን ባንክ በበኩሉ አራት ሚሊዮን ዶላር ሲመነዝር፣ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክም ከአራት ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማከናወኑ ተመልክቷል፡፡

የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቢ ሳኖ እንደገለጹት፣ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ የተመዘገበውን ብቻም ሳይሆን፣ እ.ኤ.አ. በጁላይ 2018 ውስጥ ብቻ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ መጠን በአንድ ዓመት ውስጥ ባንኩ ያገኘው የነበረውን የውጭ ምንዛሪ መጠን የሚያስንቅ ነው፡፡ ልዩነቱን በመቶኛ በማስቀመጥ ሲያብራሩም፣ በወሩ ወደ ባንካቸው ከመጡ ደንበኞች የተሰበሰበው የምንዛሪ ዋጋ  የ1200 በመቶ ጭማሪ የታየበት ነው፡፡ አጠቃላይ መረጃው ባይጠናቀርም፣ በአንድ ወር ብቻ ከአራት ሚሊዮን ዶላር በላይ ሳይገኝ እንዳልቀረ አቶ አቢ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ባንኩ ከተገልጋዮች ከሚቀርብ የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ በዓመት የሚሰበስበው ከሁለት ሚሊዮን ዶላር ያልበለጠ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

 አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የተሰበሰበው የውጭ ምንዛሪ ከዚህ በፊት በትንሹ ከሦስት ወራት በላይ ይፈጅባቸው ከነበረው አኳያ ብልጫ ያለው የውጭ ገንዘብ ወደ ባንኮቹ እየገባ ስለመሆኑ ባንኮቹ ይፋ እያደረጉ ነው፡፡ ስለዚሁ ጉዳይ ያነጋገርናቸው የኅብረት ባንክ አንድ ኃላፊ እንደገለጹት፣ ባለፉት 20 ቀናት ውስጥ ከአምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ በባንኩ መመንዘሩን፣ ይህም ከዚህ ቀደም በዚህ ጊዜ ውስጥ ሲሰበሰብ ያልታየ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ደንበኞች ይህን ያህል ገንዘብ በባንካቸው በኩል ሲመነዝሩ አለማየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

እንደ ኅብረት ባንክ ሁሉ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ 6.8 ሚሊዮን ዶላር መመንዘሩን የሚያመለክተው የአቢሲኒያ ባንክ፣ ከዚህ ቀደም የውጭ ገንዘብ እንዲመነዘርላቸው የሚጠይቁ ደንበኞች ያን ያህል ነበሩ ለማለት እንደሚያስቸግር  ይገለጻል፡፡ በዚህ መንገድ ባንኩ ከ100 እስከ 200 ሺሕ ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ሊመነዝር የሚችልበት አጋጣሚዎች ብቻ ነበሩ፡፡

በብርሃን ባንክ መረጃ መሠረት፣ ቀደም ብሎ ከነበረው ልማድ አንፃር ሲታይ፣ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ለምንዛሪ አገልግሎት የተጠየቀበት የውጭ ምንዛሪ መጠን ከዚህ በፊት በአራት ወራት ውስጥ ይገኝ የነበረውን ያህል እንደሆነ የሚጠቁም ነው፡፡

አንድ የባንክ ባለሙያ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ግኝታቸውን ለማሳደግ የተለያዩ ጥረቶች ሲያደርጉ ከመቆየታቸውም በላይ እርስ በርሳቸው ፉክክር ውስጥ ለመግባት የተገደዱበት ወቅትም ሆኗል፡፡ በርካቶቹ የውጭ ምንዛሪ ለመመንዘር ለሚመጣ ወይም ከውጭ የሚላክለት ደንበኛ በባንካቸው ሽልማት እንደሚሰጠው፣ የሎተሪ ዕድል እንደተዘጋጀለት ወዘተ. የሚገልጹ ማስታወቂያዎች ሰርክ ሲያስነግሩ ይደመጣልሉ፡፡ ይህን ሁሉ አድርገውም ሲያገኙ የቆዩት የውጭ ገንዘብ ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከተገኘው አኳያ በብዙ እጥፍ ብልጫ ያለው ውጤት ተመዝግቧል፡፡

ከባንኮች የውጭ ግኝት ውስጥ አንዱና ዋነኛው ከወጪ ንግድ የሚገኘው እንደሆነ የገለጹት ባለሙያዎች፣ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚላክ የውጭ ገንዘብም ትልቅ ድርሻ እንዳለው ያብራራሉ፡፡ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ግኝታቸውን ለማሳደግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቁ ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶችና የፋይናንስ ተቋማት ጋር በመሥራት ወደ አገር ውስጥ የሚላከውን የገንዘብ መጠን ገቢ ያደርጋሉ፡፡ የገንዘብ አስተላላፊዎቹም ሆኑ የውጭ ባንኮች አገር ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ከአብዛኛዎቹ ጋር የአገር ውስጥ ባንኮች በመዋዋል የሚሠሩ ናቸው፡፡

ይህ በመሆኑም ባንኮች ከውጭ የሚላከው ገንዘብ በባንካቸው በኩል እንዲገባ የተለያዩ የሽልማት መርሐ ግብሮችን በማመቻቸት ገንዘብ የሚላክላቸው ደንበኞች እንዲመጡላቸው ለመሳብ ሲጣጣሩ የሚታዩት፡፡ ነገር ግን ከሁለት ወይም ከሦስት ሳምንታት ወዲህ እየታየ ያለው ግን፣ በርካታ ወጪዎችን ለሽልማት መድበውና አዘጋጅተው በስድስትና በሰባት ወራት ያላገኙትን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት የቻሉበት ፖለቲካዊ ድባብ መፈጠሩ እየታየ ነው፡፡

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አስተያየት ከሰጡ ኃላፊዎች መካከል የብርሃን ባንክ አንድ ኃላፊ እንደገለጹት፣ በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት በተላለፈ በመጀመርያው ሳምንት በቀን እስከ 200 ሺሕ ዶላር የሚጠጋ የውጭ ገንዘብ በተለያዩ የባንኩ ቅርንጫፎች ተመንዝረዋል፡፡ ከሦስት ሳምንት በፊት ግን ግፋ ቢል ይመነዘር የነበረው እስከ 500 ሺሕ ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ነበር፡፡ ይሁንና በሁለት ሳምንት ውስጥ አራት ሚሊዮን ዶላር መመንዘሩ የተለየ ክስተት እንደሚያደርገው ገልጸዋል፡፡

እንዲህ ባለው መንገድ የተገኘውን የውጭ ምንዛሪ ሕጉን በጠበቀ መንገድ የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ ለሚያቀርቡ ደንበኞች በተወሰነ ደረጃ አጥጋቢ ሊባል የሚችል ምላሽ ለመስጠት ቢያስችልም፣ ካለው የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት አንፃር ሲታይ ግን እየተሰበሰበ ያለው የውጭ ምንዛሪ ብዙም ለውጥ ሊያመጣ የሚችል እንዳልሆነ የጠቅሱ አሉ፡፡ ነገር ግን የተጀመረው ነገር እየተለመደ ከሄደ፣ ከፍተኛ ውጤት እንደሚያስገኝና ያለውንም የአቅርቦት ችግር እያስተነፈሰው እንደሚሄድ ይታመናል፡፡

በርካታ ደንበኞች ወደ ባንኮች በመቅረብ መመንዘራቸውን ቢገፉትም፣ በአብዛኛዎቹ ባንኮች እየታየው ያለው ፍሰት ግን እንደ መጀመርያው ሳምንት  እንዳልሆነ እየተገነገረ ነው፡፡ ቀስ በቀስ እየቀነሰ የመጣው የምንዛሪ ሒደት እንዳይቀንስ ሐሳብ የገባቸው ባንኮችም ይህንኑ ሥጋት እየገለጹ ነው፡፡

ወጣት ምትኩ እንደሚለው፣ በጥቁር ገበያውና በባንኮች መካከል ያለው የምንዛሪ ልዩነት የቱንም ያህል ቢሆን፣ በባንክ በኩል መመንዘር የዜግነት ኃላፊነትን እንደመወጣት የሚቆጠር ነው፡፡ በርካቶችም እንዲህ ባለው በጎ አመለካከት ተነሳስተው የውጭ ገንዘቦችን በባንክ በኩል እንደመነዘሩ ይገምታል፡፡

ይህ ሁሉ ቢባልም ከአንድ ወር በላይ በጥቁር ገበያውና በባንኮች መካከል የነበረው ጠባብ የምንዛሪ ዋጋ ልዩነት፣ ከሰሞኑ በጥቁር ገበያው እያንሰራራ መምጣቱን ለመረዳት ተችሏል፡፡ መሳ ለመሳ የነበረው የምንዛሪ ዋጋ አሁን ላይ በጥቁር ገበያው ጭማሪ ማሳደሩ ብቻም ሳይሆን፣ የደንበኞች እንደ መጀመርያው ሰሞን በብዛት አለመምጣት ባንኮችን አሳስቧል፡፡

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   አገርን የከዱ ተደመሰሱ፤ የሳተላይት መገናኛና መድሃኒት " ጁንታው" እጅ ሳይገባ ተያዘ
0Shares
0