የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በ2009 በጀት ዓመት 35 ነጥብ 4 ቢልዮን ብር በማጽደቅ ወደ ስራ ገብቶ ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤትም በተሻሻለው የከተማው አስተዳደር ቻርተር አዋጅ እንዲሁም፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤትን እንደገና ለማቋቋም በወጣው አዋጅ በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት የከተማ አስተዳደሩን የፋይናንስና ሕጋዊነት ኦዲት፤የልዩ ኦዲት እና የክዋኔ ኦዲት ይሰራል፡፡ በቅርቡ የ2009 አመት አፈጻጸምን በተመለከተ ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ሪፖርት አቅርቧል፡

አዲስ ዘመን ጋዜጣም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር ከሆኑት ወይዘሮ ጽጌወይን ካሳ ጋር በኦዲት ሪፖርቱ ዙሪያ ያደረገውን ቃለ መጠይቅ እንደሚከተለው ያቀርባል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት አመታዊ አፈጻጸም ምን ይመስላል ?
ወይዘሮ ጽጌወይን፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የከተማ አስተዳደሩን የፋይናንስና ሕጋዊነት ኦዲት፤የክዋኔ ኦዲትና የልዩ ኦዲት በእቅድ ይዞ ይሰራል፡፡ በእቅድ ከተያዘው ውጪ ኦዲት ይደረግልን የሚል ሲመጣም ተቀብለን እንሰራለን፡፡ በከተማው ውስጥ ወደ 515 ተቋማት አሉ፡፡ ትምህርት ቤቶች፣ጤና ጣቢያዎች፣ 117 ወረዳዎች፣10 ክፍለ ከተሞችና 56 ሴክተር መስሪያ ቤቶች ኦዲት የሚደረገው በእኛ ነው፡፡ እነዚህን አሁን መቶ በመቶ ማዳረስ አይቻልም፡፡ ስለዚህ የኦዲቱን ስራ ‹‹ሀ›› ‹‹ለ›› ‹‹ሐ›› እና ‹‹መ›› ብለን በመለየት ስጋት ያለባቸውና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ በጀት የሚመድብላቸው ቢሮዎች ላይ ነው ትኩረት አድርገን የምንሰራው፡፡ የተያዘው በጀት አመት አፈጻጸማችን 65 በመቶ ደርሷል፡፡ አምና ከነበረው 58 በመቶ ሲነፃፀር የሻተለ ነው፡፡ በተያዘው በጀት አመት 46 የፋይናንስ፣ 3 የክዋኔና 14 ልዩ ኦዲት ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኦዲት ግኝቶቹ የተለዩት ዋና ዋና ክፍተቶች ምንድን ናቸው ?
ወይዘሮ ጽጌወይን፡- በኦዲት ግኝቶቹ እንደ ክፍተት የተገኙት የግዢ ደንብ መመሪያ አለመከተል፣ ከተሰብሳቢ ሂሳብ ጋር ያለው አሰራር፤ ተቋማት ንብረታቸውን ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ባወጣው አዋጅ ደንብና መመሪያ መሰረት እያስተዳደሩ አለመሆናቸው እና የሂሳብ አሰራር ግድፈቶች ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በፋይናንስ ኦዲት ግኝት መሰረት ያልተሰበሰበ ወደ 329 ሚሊዮን ብር በ11 ተቋማት መገኘቱ ተመልክቷል፤ ይሄንን ቢያብራሩልን ?
ወይዘሮ ጽጌወይን፡- እንደተጠቀሰው 329 ሚሊዮን 677 ሺ 934 ብር በወቅቱ ያልተሰበሰበ ሂሳብ መኖሩ በኦዲት ተረጋግተጧል፡፡ ይሄ በ11 ተቋማት ነው የተገኘው፡፡ ተቋማት መሰብሰብ አለብን የሚሉትን ሂሳብ ሲኖር ማስረጃ መኖር አለበት፡፡ ማስረጃ ሳይኖር እንሰበስባለን የሚሉ አሉ፡፡ ተቋማት ይሄንን ገንዘብ ሰብስበው ማሳወቅ አለባቸው፡፡ ጊዜ የተሰጣቸው እስከ መስከረም 30 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ነው፡፡ የ2010 ማጠቃለያ ሪፖርት ቀርቦ ሰኔ ላይ በምክር ቤት ውይይት ሲደረግ አባላት ጥያቄ አንስተው መሰብሰብ ያለበት ገንዘብ ተሰብስቦ ለመንግስት እንዲገባ የሚል አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ የማይሰበሰብ እንኳን ቢሆን ምክንያቱና ማስረጃው ተገልጾ ማቅረብ አለበት፡፡ ተቋሙ ላይ በተሰብሳቢ ማሳየት የለበትም፡፡ ስለዚህ እስከ መስከረም ድረስ ተቋማቱም ለዋናው ኦዲተር አሳውቀው ሪፖርቱ ለዘገባ እንዲቀርብ በተቀመጠው አቅጣጫ እንሰራለን፡፡

170621131514-africas-fastest-growing-cities-addis-ababa-exlarge-169
አዲስ ዘመን፡- ተቋማቱ እነማን ናቸው ?
ወይዘሮ ጽጌወይን፡- መንገዶች ባለስልጣን ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ የመንገዶች ባለስልጣን ወደ 228 ሚሊዮን 994 ሺ 31 ብር ከ 63 ሳንቲም፣ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የውሃና ሳኒቴሽን ልማትና ማስፋፊያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ብር 92 ሚሊዮን 744 ሺ 576 ብር ከ 82 ሳንቲም እና የሙያ ብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ማዕከል ደግሞ 6 ሚሊዮን 108 ሺ 172 ብር ከ 29 ሳንቲም ያልተሰበሰበ ሂሳብ ተገኝቶባቸዋል፡፡
እነዚህና ሌሎችም ያልተሰበሰበ ሂሳብ የተገኘባቸው ተቋማት መሰብሰብ ያለባቸውን በወቅቱ ሰብስበው ማሳወቅ አለባቸው፡፡ የማይሰበሰብም ከሆነ ማስረጃውን አቅርበው የሚቀነስ ከሆነም ተቀናሽ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኦዲት ግኝታችሁ ከእነማን እንደተሰበሰበ የማይታወቅ ከፍተኛ ገንዘብ መኖሩ ይታያል፤ ምን ማለት ነው ?
ወይዘሮ ጽጌወይን፡- አንዳንድ ተቋማት ኦዲት ሲደረጉ ተሰብሳቢ ሂሳብ አለን ይላሉ፡፡ ይሄ ማለት ሲዞር የመጣ ሂሳብ ነው፡፡ ተሰብሳቢ ማሳየት ያለበት የአሁኑን ብቻ ነው፡፡ ይሁንና የአምስትና የአራት አመት ተሰብሳቢ ሂሳብ ያላቸው ተቋማት ይኖራሉ፡፡ ማስረጃ አቅርቡ ሲባል ማስረጃ የላቸውም፡፡ ከማን እንደሚሰበስቡ አያውቁትም፡፡ ግን ተሰብሳቢ አለ ይላሉ፡፡
ተቋማት ይህን የሚያደርጉት ሒሳብ አልገጥም ሲላቸው ነው፡፡ ሂሳብ ሲሰራ አንዱ ይበልጥና አንዱ ያንሳል፡፡ ይሄኔ ተሰብሳቢ አለ በሚል ያስገቡና ሂሳቡን ነፃ ያደርጉታል፡፡ ለፋይናንስ ሂሳቤን ዘግቻለሁ ብለው ያቀርባሉ፡፡ ግን የሚሰበሰብ ገንዘብ የላቸውም፡፡ ተከፋይ አለብኝ ካሉ ሊጠየቁ ነው፡፡ ስለዚህ እንደዚህ እያደረጉ ሂሳብ ለመዝጋት ፣ ለሂሳብ ማምታቻ የሚጠቀሙ ተቋማት አግኝተናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ገንዘቡ ምን ያህል ነው ? ተቋማቱስ የትኞቹ ናቸው?
ወይዘሮ ጽጌወይን፡- ከማን እንደሚሰበሰብና የመቼ ሂሳብ እንደሆነ የማይታወቅ 3 ሚሊዮን 959 ሺ 337 ብር ከ 19 ሳንቲም ተገኝቷል፡፡ ተቋማቱ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮና ካዛንችስ ጤና ጣቢያ ናቸው፡፡ የምትሰበስቡትን ሰብስቡና ለመንግስት ገቢ አድርጉ፤ ዝም ብሎ ከሂሳብ መዝገብ መሰረዝ አይቻልም ህግና ስርአት አለው እያልን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በምን መንገድ ነው እንደዛ ማድረግ የሚቻለው ?
ወይዘሮ ጽጌወይን፡- ሂሳቡን ከመዝገብ መሰረዝ በተመለከተ እስከ 7 ሺ ብር ድረስ ማስረጃዎችን አይቶ መርምሮ አገናዝቦ በራሱ በተቋሙ ኃላፊ መሰረዝ ይችላል፡፡ አንድ ሚሊዮን ብር ድረስ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ከሂሳብ መዝገብ መሰረዝ ይችላል፡፡ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ሲሆን ግን ካቢኔ ይወያይበትና ማስረጃ በማቅረብ ፍርድቤት ማስረጃዎቹን አይቶ ከሂሳብ መዝገብ መሰረዝ ይቻላል ሲባል መሰረዝ ይቻላል፡፡

children on the street
አዲስ ዘመን፡- ካልተሰበሰበ ሂሳብ ጋር በተያያዘ ያለው አሰራር ለሙስና አያጋልጥም ?
ወይዘሮ ጽጌወይን፡- ያጋልጣል እንጂ፡፡ ይህን አሰራር ነው እኮ እኛም እየተቸን ያለነው፡፡ አንድ ሂሳብ የሚሰራ ተቋም በሂሳብ ስርአቱ መሰረት ነው ሂሳቡን መዝጋት ያለበት፡፡ ዜሮ ነጥብ አንድ ሳንቲም ባላንሱ ካልመጣ ሂሳብ አይዘጋም፡፡ ተሰብሳቢ አለ ተከፋይ አለ እየተባለ ለሂሳብ መዝጊያ መደረግ የለበትም፡፡ ለዚህ ነው ማስረጃ አቅርቡ ሲባሉ አንዳንዶቹ አዲስ ነን አናውቅም ይላሉ፡፡ የሚሰበሰብ የመንግስት ገንዘብ መሰብሰብ አለበት፡፡ የሚከፈልም ካለ መክፈል ነው፡፡ የሚከፍለው ከሌለ ከሂሳብ መዝገብ ተሰርዞ የአመቱን ሂሳብ ነጻ መደረግ አለበት ነው የእኛ እምነት፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኦዲት ግኝቱ ለማን እንደሚከፈል የማይታወቅ ገንዘብ መኖሩ ታይቷል፤ ተቋማቱ የትኞቹ ናቸው ?
ወይዘሮ ጽጌወይን፡- የኦዲት ግኝቱ ለእነማን እንደሚከፈል የማይታወቅ ወደ 123 ሚሊዮን 321 ሺ 342 ብር ከ50 ሳንቲም መኖሩን ያሳያል፡፡ መንገዶች ባለስልጣን 115 ሚሊዮን 739 ሺ 111 ብር 46 ሳንቲም፣ መሬት ልማት ማኔጅመንት 7 ሚሊዮን 483 ሺ 397 ብር ከ 54 ሳንቲም ነው፡፡ ካዛንችስ ጤና ጣቢያ 98 ሺ 833 ብር ከ 52 ሳንቲም ለእነማን እንደሚከፈል የማይታወቅ ሂሳብ እንዳለ ተረጋግጧል፡፡ እነኚህ የምንከፍለው አለ ብለው ይዘዋል፡፡ ግን ማስረጃ የላቸውም፡፡ ለማን እንደሚከፍሉ አያውቁትም፡፡ አጥርተውም ሰነድ አልያዙም፡፡ ቅድም እንዳልኩት ሊሂሳብ አላማ የተቀመጠ ነው ማለት ነው፡፡ የምከፍለው አለኝ አለ፡፡ ለማን ነው የሚከፍለው ? አንድ ተቋም እኮ ማስረጃ መያዝ አለበት፡፡ ማስረጃ አቅርብ ሲባል ማስረጃ አያቀርብም፡፡ ለዚህ ነው ለማን እንደሚከፈል አይታወቅም የሚባለው፡፡
እነዚህ ተቋማት ማስረጃ እስካላቀረቡ ድረስ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት በጀት ስለማይለቅላቸው ገንዘቡ ተከፋይ አይሆንም፡፡ የሚከፈለው ለማን ነው ብሎ ይጠይቃል፡፡ አሁን አሁን የኦዲት ስራውም እየተጠናከረ ስለሄደ መፈናፈኛ መንገድ አይገኝም፡፡ በፊት ቢሆን ለሌብነት መንገድ ይከፍታል፡፡ ማስረጃ ባይኖረውም እከፍላለሁ ብሎ ይዞ በቀጣይ ሊከፍል ይችላል፡፡ ያለማስረጃ የተከፈለ ገንዘብ እናገኛለን፡፡ በኋላ ደግሞ ለከፈለበት ማስረጃ የማያቀርብ ተቋም አለ፡፡ እሱን በፋይናንስ እኛ ኦዲት ካደረግን በሕጋዊነት ላይ ያ ያለማስረጃ የተከፈለው ገንዘብ ለመንግስት ይመለስ ብለን ነው የምንይዛቸው፡፡ ወደዛ እንዳይሄድ ነው ይሄ ግኝት የሚያስፈልገው፡፡
ለማን እንደሚከፈል አይታወቅም ብለናል፡፡ በቀጣዩ ደግሞ ያለ ማስረጃ ከፈለ ተብሎ ሊቀርብ ነው፡፡ እንደዛ እንዳይሆን ነው የምንይዘው፡፡ ይሄንን የመንግስት ወጪ ቁጥጥርና በጀት ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ይከታተለዋል፡፡ ማስረጃውን ይይዙና ይሄ ግኝት ተገኝቶብሀል በምን ጊዜ ነው የምትመልሰው የድርጊት መርሀ ግብርህ የታል፤እንዴት ነው የምትሰራው ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ለእኛም ግብረ መልስ ይሰጣሉ፡፡ ይሄ አሰራር አሁን ነው የተጀመረው፡፡ ይህ አሰራር ስለተጀመረ አሁን መክፈል አይችሉም፡፡ በፊት ግን ይከፍሉ ነበር፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንዲህ አይነት ሁኔታ ሲፈጠር ምንድን ነው የምታደርጉት ?
ወይዘሮ ጽጌወይን፡- እንዲህ አይነት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ያጋጠሙም ነበሩ፡፡ በከተማው ላይ እንደዚህ ሲያጋጥም የፋይናንስ ግልጽነትና ተጠያቂነት ኮሚቴ አባላቶች አሉት፡፡ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ፣ የከንቲባ ጽህፈት ቤት፣ ፍትህ ቢሮና ስነምግባርና ጸረ ሙስና እንዲሁም እኛ በአስረጅነት እንቀርባለን፡፡ በዚህ ኮሚቴ መሰረት ለውጦች መጥተዋል፡፡ ከተጀመረ አንድ አመት ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን ክፍተቱ እንዳለ ነው፡፡ ይህ ኮሚቴ ከተጠናከረ በኋላ ግን ነገሮች እልባት እያገኙ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የግዢ መመሪያና አዋጅ በመጣስ በኩል የታየው ክፍተት ምን ይመስላል ?
ወይዘሮ ጽጌወይን፡- የግዢ አዋጅ ደንብና መመሪያ ሳይከተሉ የተፈጸሙ ግዢዎች 112 ሚልዮን 277 ሺ 277 ብር ከ 85 ሳንቲም ደርሰዋል፡፡ ይህ ኦዲት ካደረግናቸው ውስጥ በሰባት ተቋማት የተገኘ ነው፡፡ ግዢ ሲፈጸም ስድስት መመሪያዎች ተቀምጠዋል፡፡ አንድ ተቋም ከአንድ ሚሊዮን ብርና ከዚያ በላይ ግዢ ሲፈጽም ግልጽ ጨረታ ማካሄድ አለበት፡፡ የዋጋ ማወዳደሪያ ፕሮፎርማ መሰብሰብ አለበት፡፡ እነዚህንና ሌሎችን የግዢ ደንቦች ሳይከተሉ ግዢ የሚፈጽሙ ተቋማት አሉ፡፡
ተቋማቱ የግዥ መመሪያ ጥሰት አድርገዋል፡፡ የግኝቱ መነሻ የመንግስት ገንዘብ ጠፋ የሚል ሳይሆን፤ የግዢ ስርአቱን በመጣሳቸው መንግስት ከሚከፈለው ገንዘብ ላይ ሊያገኘው የሚችለውን ጥቅም አሳጥተዋል የሚል ነው፡፡ ጨረታው ኮሚቴ ሳያየው የሚፈጸም ግዢ አለ፡፡ ጨረታ ኮሚቴው ያሸነፈው ይሄ ነው ብሎ ዝቅተኛ ዋጋ ሰጥቶ ያለ ምንም ምክንያት ከፍተኛ ዋጋ ሰጥተው የሚገዙ አሉ፡፡ ሌላው ደግሞ ኮሚቴ ሲዋቀር አንዱ ቴክኒክ ኮሚቴ የሚባል አለ፡፡ይሄ ቴክኒክ ኮሚቴ ጥራትን ነው የሚያየው፡፡ ይሄ ዋጋ በዚህ ዋጋ ቢገዛ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብሎ አስተያየት መስጠት አለበት፡፡ የቴክኒክ ኮሚቴው አስተያየት ሳይኖርም የሚገዙ አሉ፡፡ የግዢው መመሪያ መከበር አለበት፡፡ እልባት ካልተበጀለት ወደ ምዝበራ የሚሄድ ስለሆነ መቀጨት አለበት ነው የምንለው፡፡

staigt children
አዲስ ዘመን ፡- በኦዲት ሪፖርቱ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ከውል ውጭ ገንዘብ መክፈሉ ተጠቁሟል፤ ግኝቱ ምንድን ነው የሚያሳየው?
ወይዘሮ ጽጌወይን፡- በሁለት ተቋማት 4 ሚልዮን 598 ሺ 751 ብር ከ88 ሳንቲም ለግንባታ ሥራ ክፍያ ሲፈፀም ከውል በላይ መሆኑ በኦዲት ሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ የወንዞችና የወንዝ ዳርቻዎች ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት 4 ሚልዮን 444 ሺ ብር እንዲሁም የመሬት ይዞታና ምዝገባ መረጃ ኤጀንሲ ጽህፈት ቤት 154 ሺ 680 ብር ከ48 ሳንቲም ነው፡፡ ይህ ከመመሪያ ውጪ ነው፡፡ አንድ ተቋም መዋዋል የሚችለው ከዋናው ገንዘብ እስከ 30 በመቶ ብቻ ነው፡፡ የተከፈለው ግን ከ30 በመቶ በላይ ነው፡፡ ትክክል አይደለም ይሄ ገንዘብ መመለስ አለበት ነው የምንለው፡፡ ፈቃጅ አካል ሳይኖር ተቋሙ በራሱ ፈቅዶ እንዴት ከፈለ? የፈቀደ አካል ካለ ማስረጃው ይቅረብ፤ ይህ በሌለበት ሁኔታ ግን የመንግስት ገንዘብ ተመዝብሯል ነው የምንለው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ይህን ስትሉ የሚሰጡት ምላሽ ምንድን ነው ?
ወይዘሮ ጽጌወይን፡- አንዳንዶቹ ፕሮጀክቱ ባለማለቁ ጊዜ ስለወሰደ ነው፤ስለተራዘመ ነው የሚል ነው፡፡ ያም ቢሆን ፕሮጀክቱ ስለመራዘሙ አፕሩቫል (ያጸደቀው) አካል ካለ እሱ ይቅረብ ነው፡፡ ተቋሙ በራሱ ውል እያደሰ በአራት አመት የሚያልቀውን እስከ አስር አመት ካቆየው የመንግስት ንብረት ለምዝበራ ተጋልጧል፡፡ ስለዚህ ይሄ ምላሽ የሚያስፈልገው ነው፡፡
አዲስ ዘመን ፡- ለመንግስት ገቢ መሆን የነበረበት 840 ሺ ብር ያልተቀነሰ የስራ ግብር መኖሩ በኦዲት ግኝቱ ተመልክቷል፤ ይህን የፈጸመ የትኛው ተቋም ነው ?
ወይዘሮ ጽጌወይን፡- በወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ለአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኞችና ተጫዋቾች በገቡት ውል መሰረት ክፍያ ሲፈጸም ለመንግስት ገቢ መደረግ የነበረበት የስራ ግብር ሳይቀነስ ብር 840 ሺ ብር ክፍያ ተፈጽሞ ተገኝቷል፡፡ ማንም ሰው ከሚያገኘው ገቢ ላይ የስራ ግብር ይቆረጥበታል፡፡ እነርሱም ከሚያገኙት ገቢ የስራ ግብር ይቆረጥባቸዋል፡፡ ይሄንን ገንዘብ እስከ መስከረም ገቢ እንድታደርጉ ተብሏል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በየክፍለ ከተማው በሚገኙ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ጽህፈት ቤቶች ለፋርማሲ አገልግሎት የሚውሉ ከጋራ ህንጻ ንግድ ቤቶች የተገዙ ሱቆች ስራ ላይ አልዋሉም፤ የኦዲት ግኝታችሁ ምን ያመለክታል ?
ወይዘሮ ጽጌወይን፡- ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች አገልግሎት እንዲሰጡ በ 11 ሚሊዮን 475 ሺ ብር ወጪ በከተማ አስተዳደሩ ተፈቅዶ በተለያዩ ሳይቶች የተገዙ ቤቶች ነበሩ፡፡ ለፋርማሲ አገልግሎት መዋል ሲገባቸው ተዘግተው የተገኙ ናቸው፡፡ አንዱ ሳይት ላይ ቻይና ሬስቶራንት የሚባል መጋዘን አድርጎ ሲጠቀምበት አግኝተናል፡፡ ሌላው ደግም ሶፋ ተደርድሮ መብራት ከጎረቤት ተስቦ አይተናል፡፡ ይሄንንም የሚመለከተው አካል ማስረጃ የለኝም አላውቀውም ብሏል፡፡ የመንግስትን ሀብት ይሄን ያህል ገንዘብ ወጪ አድርጎ ጥቅም ሳይሰጥ መቀመጡ አግባብ አይደለም ብለን ስንተች በአንድ ወቅት የተሰጠው መልስ አካባቢው ባለመልማቱ ምክንያት ፋርማሲዎቹን መክፈት አልቻልንም የሚል ነበር፡፡ እኛ በአካባቢዎቹ ባደረግነው ቅኝት የግል ፋርማሲዎች መከፈታቸውን አረጋግጠናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ የገዛቸው ብረቶች ለብልሽት ተዳርገው መገኘታቸው በኦዲት ሪፖርቱ ታይቷል፤ምን ምላሽ ተሰጠው ?
ወይዘሮ ጽጌወይን፡- ለአርባ ስልሳ ቤቶች ግንባታ ተገዝቶ ጎፋ ማእከላዊ መጋዘን ለብልሽት በሚዳርግ መልኩ ተቀምጦ የተገኘ ብረት ነው፡፡ 271 ነጥብ 3 ቶን ባለስድስት ብረት ዋጋው 114 ሚሊዮን 217 ሺ ዶላር የሚያወጣ እንዲሁም 3 ሺ 850 ነጥብ 6 ቶን ባለ 8 ብረት ዋጋው 1 ሚሊዮን 617 ሺ ዶላር የሚያወጣ ብረት ለዝናብ ለጸሀይ በተጋለጠ መልኩ አገልግሎት ላይ ሳይውሉ ተገኝተዋል፡፡ ተቋሙ ሲጠየቅ በ2005 ዓ.ም እንደገዛው ጠቅሶ፤ አሁን ያለው ዋጋው በመጨመሩ መገዛቱ ለመንግስት ጥቅም አለው ብሏል፡፡ እኛ ደግሞ መግዛቱ አንድ ነገር ሆኖ በአግባቡ አልተቀመጠም፤ በአግባቡ ጥቅም ላይ አልዋለም ነው ያልነው፡፡ ከተሰጠው መልስ ጋር ይቃረናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደ ብረት ያሉ ግብአቶች ባለመሟላታቸው ስራቸው የዘገዩ ቤቶች የሉም?
ወይዘሮ ጽጌወይን፡- እዚህ መጋዘን ውስጥ ይሄ ንብረት ተከማችቶ እያለ ስራቸው የቆሙ ቤቶች ነበሩ፡፡ ለምን ቆሙም ብለናል፡፡ የሚሰጡት መልስ እዚህ ያለው ብረት ለስራው አይሆንም የሚል ነው፡፡ ባለሙያ ስላልሆንን ያንን መመለስ አልቻልንም፡፡ ዞሮ ዞሮ ይህ የመንግስት ንብረት ለብልሽት በሚዳርግ መልኩ መቀመጡ አግባብ አይደለም ነው ያልነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኦዲት ካረጋገጣችኋቸው ጉዳዮች ሳይነሳ መታለፍ የሌለበት ግኝት ካለ?
ወይዘሮ ጽጌወይን፡- ሳይነሳ መቅረት የሌለበት በአሽከርካሪ ማሰልጠኛዎች አካባቢ ያለው ጉዳይ ነው፡፡ በአንድ የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋም አርባ ሰልጣኞች ስልጠና ይወስዳሉ ተብሎ ቦታው ላይ ተኪዶ ሲረጋገጥ ለፈተናም ጭምር ተቀጥረው የሚያገለግሉ ሰዎች ተገኝተዋል፡፡ አንድ ሰልጣኝ ሲኖትራክ መኪና ያለአሰልጣኝ ብቻውን ሲነዳ አግኝተናል፡፡ የትራፊክ አደጋ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ አደጋ እያደረሰ ያለው እንደነዚህ አይነት ተቋማት በሚሰሩት ህገ ወጥ ተግባር ጭምር ነው፡፡
ለተፈታኞች መጠይቆችን በትነን ነበር፡ ፡አንድም ተፈታኝ ገንዘብ ሳይጠየቅ አያልፍም፡፡ በተለይ ሴቶች ከ3000 እስከ 5000 ብር ድረስ ይጠየቃሉ፡፡ ችሎታ ቢኖራቸውም ያንን ካልከፈሉ አያልፉም፡፡ ችሎታም የሌለውም ያንን ከፍሎ ይወስዳል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ይሄ የአንድ አመት የኦዲት ግኝት ሪፖርት ነው፡፡ በተከታታይ አመታት ለሚፈጸሙ ግድፈቶች የሚሰጠው ምላሽ ምን ይመስላል?
ወይዘሮ ጽጌወይን፡- እኛም እሱን ነው እየጠየቅን ያለነው፡፡ ለኦዲት ግኝት ምላሽ ይሰጥ እያልን ነው፡፡ ከ2003 አስከ 2007 ኦዲት የተደረጉ ተቋማት ምን እርምጃ ተወሰደ የሚለውን ለምክርቤት አቅርበናል፡፡ አንዳንዶቹ አዲስ ነን አናውቀውም ይላሉ፡፡ እኛ ደግም እናንተ ባታውቁም የኦዲት ሪፖርቱ ዝርዝር መረጃ እኛ ጋ አለ ኑና ውሰዱ እንላለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከእናንተ ኦዲት ሪፖርት በመነሳት አቃቤ ሕግ እየወሰዳቸው ያሉት እርምጃዎች አጥጋቢ ናቸው ?
ወይዘሮ ጽጌወይን፡- እኛ ሪፖርት እንሰጣለን፡፡ ወደ ሕግ መሄድ ያለበትን እነሱ ናቸው የሚወስኑት፡፡ በዚህ መሰረት ተጠያቂ የሆኑ ተቋማት አሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- እናንተ የኦዲት ግኝት ሪፖርቱን በመንተራስ ለተቋማት ማሳሰቢያ ትሰጣላችሁ፤ የሚሰጧችሁ ግብረ መልስ ምን ይመስላል ?
ወይዘሮ ጽጌወይን፡- እኛ ማሳሰቢያ ስንሰጥ በተለይ መመለስ ያለበት ገንዘብ ተመልሶ ለተቋማችን ይገለጽ ብለን እንልካለን፡፡ ተቋማት እንደ በፊቱ አይደለም፡፡ ምላሽ መስጠት ጀምረዋል፡፡ ተጠናክሮ ግን መቀጠል አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- የቅንጅት ስራዎችን በተመለከተስ ምን እየተሰራ ነው ?
ወይዘሮ ጽጌወይን፡- ከአዲስ አበባ ፖሊስ እንዲሁም ከጠቅላይ አቃቤ ሕግና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል፡፡ መታየትና መታወቅ ያለበት ኦዲተር ስህተት ፈላጊ አይደለም፡፡ አመራሮችን ባለሙያዎችን ሊወነጅል አይደለም የሚሰራው፡፡ ደጋፊ ነው፡፡ ሁሉም አካላ አጋዥ ኃይል መሆኑን ተረድተው በጋራ ሊሰሩ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስራችሁን በተመለከተ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚሰራ ስራ አለ ?
ወይዘሮ ጽጌወይን፡- ከአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሀን የአየር ሰአት ገዝተናል፡፡ እሁድ ከ1፡20 እስከ 1፡30 ድረስ የእኛ ፕሮግራም ይቀርባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በጣም እናመሰግናለን !
ወይዘሮ ጽጌወይን፡- እኔም አመሰግናለሁ !

 ወንድወሰን መኮንን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *