የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር /ህወሃት ሊያደርግ ባሰበው የመተዳደሪያ ደንብ ውስጥ  ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው አገር ውስጥ ወይም ከአገር ውጭ የሚኖር የትግራይ ተወላጅ፣ ወይም በትግራይ የሚኖር ኢትዮጵያዊ የድርጀቱ አባል እንዲሆን የሚያስችል የማሻሻያ ረቂቅ መዘጋጀቱ ተሰማ። 

ሪፖርተር ጋዜጣ ከቅርብ የወሬ ምንጮቹ እንዳገኘው ገልጾ እንደዘገበው በቀደመው የህወሃት መተዳደሪያ ደንብ ውስጥ በአባልነት ምልመላ፣ እድሜ፣ የአገልግሎት ዘመን በመሳሰሉት ጉዳዮች ማሻሻያ ተደርጓል። በድርጅቱ የማእከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ለመቆየት የመጨረሻው የድሜ ጣሪያ ስልሳ አምስት መሆኑም ተመልክቷል። ሙሉ የሪፖርተር ዜና ከታች ያንብቡ

ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በመተዳደርያ ደንቡ ላይ መጠነኛ ማሻሻያ ለማድረግ ረቂቅ ሰነድ ማዘጋጀቱን፣ ከነሐሴ አጋማሽ በኋላ በሚካሄደው በድርጅቱ ጠቅላላ ጉባዔም ተወያይቶ እንደሚያፀድቀው ተጠቆመ፡፡

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የሪፖርተር ምንጮች ለሕወሓት አባልነት የመመልመያ መሥፈርቶች፣ ለድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ለመመረጥ የዕድሜና የአገልግሎት ዘመን ገደቦችን የተመለከቱ ማሻሻያዎች እንደሚኖሩ ገልጸዋል፡፡

በድርጅቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነትን በተመለከተ ሁለት ማሻሻያ ሐሳቦች የቀረቡ ሲሆን፣ በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት የሚመረጥ ሰው ዕድሜው ከ20 ዓመት በላይ መሆን እንዳለበትና ከአራት የጠቅላላ ጉባዔ ዓመታት (ከስምንት ዓመታት) በላይ ማገልገል እንደማይችል፣ ረቂቅ የማሻሻያ ሰነድ መቅረቡን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነትን በተመለከተ ሌላው በረቂቁ የተካተተው ማሻሻያ፣ ዕድሜው ከ65 በላይ የሆነ ለማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት መመረጥ እንደማይችል፣ በማዕከላዊ ኮሚቴ በማልገል ላይ የሚገኝ ከሆነም እንዲለቅ አስገዳጅ የዕድሜ ገደብ ሆኖ መቅረቡን ገልጸዋል፡፡

የሕወሓት አባል ለመሆን አዲስ የተካተተው መመዘኛ ፍላጎት ያላቸውን በሙሉ ማካተት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው አገር ውስጥ ወይም ከአገር ውጭ የሚኖር የትግራይ ተወላጅ፣ ወይም በትግራይ የሚኖር ኢትዮጵያዊ የድርጀቱ አባል መሆን እንዲችል በማሻሻያነት ቀርቧል፡፡

ከድርጅቱ መባረርን ከሚያስከትል ጥፋቶች መካከል አዲስ ማሻሻያ ሆኖ እንዲገባ የተደረገው ሐሳብ፣ ከጥቅም ጋር የተገናኘ ቡድናዊ ዝምድናን በመፍጠር አስተሳሰብን በሚቃረን ላይ ጥቃት መሰንዘር፣ ወይም በተቃራኒው ይጠቅማል የተባለ ወገንን ደግፎ መከላከል፣ ከፍተኛ የዲስፕሊን ጥፋትና ከድርጅቱ የሚያስባርር ጥሰት ሆኖ በማሻሻያነት መቅረቡን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎችን ከሕወሓት ጽሕፈት ቤት አመራሮች ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   መከላከያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ “ጁንታውን” ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን አስታወቀ! በርካታ በቁጥጥር ስር ውለዋል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *