ሪፖርተር – በኢትዮጵያ ማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊውል ኮርፖሬሽን ሥር የሚተዳደረው የቀንጢቻ የታንታለም ማዕድን ማውጫ በግለሰቦች እየተዘረፈ እንደሆነ ተገለጸ፡፡

በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጉጂ ዞን ሰባ ቦሩ ወረዳ፣ ልዩ ስሙ ቀንጢቻ በተባለ ሥፍራ የሚገኘው የታንታለም ማዕድን ማውጫ ከታኅሳስ 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ማምረት ማቋረጡ ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ ማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊውል ኮርፖሬሽን ታንታለም ኮንሰንትሬት በማምረት ለውጭ ገበያ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ከአካባቢው ማኅበረሰብና አስተዳደር ጋር በተፈጠረ አለመግባባት የማዕድን ማውጫው ሥራ እንዲያቆም ተደርጓል፡፡

ምንጮች ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የአካባቢ ነዋሪዎች ወደ ማዕድን ማውጫው ክልል በመግባት የታንታለም ማዕድን በባህላዊ መንገድ በማምረት ላይ ይገኛሉ፡፡ ኮርፖሬሽኑ የማዕድን ማምረት ሥራውን እንዲያቋርጥ የታዘዘ ቢሆንም፣ ግለሰቦች ወደ ማዕድን ይዞታው በመግባት ታንታለም በሕገወጥ መንገድ እያመረቱ ነው ብለዋል፡፡

በኮርፖሬሽኑ ቀደም ሲል ተመርቶ የተከማቸ ታንታለም ኮንሰንትሬት በግለሰቦች መዘረፉን ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ሥራ ከማቋረጡ በፊት ያመረተው አራት ቶን ታንታለም ውስጥ፣ ሁለት ቶን ያህሉ ከሁለት ሳምንት በፊት እንደተዘረፈ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የተዘረፈው ታንታለም በገንዘብ ሲሰላ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት የተናገሩት ምንጮች፣ ጉዳዩን የኦሮሚያ ፖሊስ እየተከታተለው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር አስተያየት የጠየቃቸው የኢትዮጵያ ማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊውል ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ ሰዒድ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ሕዝባዊ አመፅ ከተከሰተ በኋላ የቀንጢቻ አካባቢ ነዋሪዎች በማዕድን ማውጫው የሚገኘው ግድብ ውኃ ከአቅሙ በላይ በመያዙ፣ ግድቡ ከተናደ አካባቢያችንን ያጠፋል የሚል ቅሬታ ሲያሰሙ ቆይተዋል፡፡ ከማዕድን ማውጫው የሚወጣው ፍሳሽ አካባቢያችንን እየበከለ ነው የሚል አቤቱታ ከማቅረባቸውም በተጨማሪ፣ የአካባቢው ወጣቶች የተጠቃሚነት ጥያቄ አንስተዋል፡፡ የኅብረተሰቡን ቅሬታ የተቀበለው የወረዳው አስተዳደር የማዕድን ማውጫው በታኅሳስ 2010 ዓ.ም. ሥራ እንዲያቋርጥ አድርጓል፡፡

ችግሩን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጋር የተደረጉ ድርድሮች እስካሁን ውጤታማ ሊሆኑ እንዳልቻሉ፣ አንድ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ኃላፊ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ የታንታለም ማዕድን ማምረቻውን በማስፋት እሴት የተጨመረባቸው የታንታለም ምርቶች ለማምረት በማሰብ ትልቅ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ተነድፎ እንደነበር የገለጹት ኃላፊው፣ ይህን ፕሮጀክት በሽርክና ከኢትዮጵያ ማዕድን፣ ነዳጅና ባዩፊውል ኮርፖሬሽን ጋር የሚሠራ ዓለም አቀፍ ኩባንያ እየተፈለገ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በመስኩ ልምድ ያለው አጋር ኩባንያ ለመምረጥ ጨረታ አውጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ በማዕድን ማውጫው አካባቢ ያለውን ችግር ባለመፍታቱ ምክንያት ጨረታውን ለመሰረዝ እንደተገደደ አስረድተዋል፡፡ በቀንጢቻ ታንታለም ማውጫ ላይ የተፈጠረው ችግር ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ መቅረቡ ታውቋል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ስለጉዳዩ ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡

የታንታለም ማዕድን በፋብሪካ ተጣርቶ ለሞባይል ስልኮችና ለሌሎች ኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ማምረቻ የሚውል ስለሆነ፣ ኢትዮጵያ ጥሬ ታንታለም ለውጭ ገበያ በተለይ ለቻይና ኩባንያዎች ስታቀርብ ቆይታለች፡፡ የኢትዮጵያ ማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊውል ኮርፖሬሽን በቀንጢቻ ታንታለም ማውጫ በዓመት እስከ 100 ቶን ታንታለም ኮንሰንትሬት በማምረት 20 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ሲያስገኝ ቆይቷል፡፡ የማዕድን ማውጫው በዓመት 174 ቶን ታንታለም ኮንሰንትሬት የማምረት አቅም ያለው ቢሆንም፣ በመሣሪያዎች ማርጀት ምክንያት ዓመታዊ ምርቱ ከ95 እስከ 97 ቶን ተገድቦ ቆይቷል፡፡

የታቀደው የማስፋፊያ ሥራ ቢከናወንና እሴት የተጨመረባቸው ምርቶች ፋብሪካ ቢገነባ፣ ለአገር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት እንደሚቻልና ለአካባቢው ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ የማዕድን ማውጫው በመዘጋቱ መንግሥትና የአካባቢው ሕዝብ እየተጎዳ ከመሆኑም በላይ፣ ሕገወጦች ክፍተቱን በመጠቀም የአገር ሀብት እየመዘበሩ ናቸው ብለዋል፡፡

ቃለየሱስ በቀለ 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *