“Our true nationality is mankind.”H.G.

አብይ አህመድ አስጠነቀቁ – ነጻነት ሀገወጥ መሆን አይደለም

ወደ ኢ-ዲሞክራሲያዊ አሰራሮች መመለስ ልንቀበለው የማንችለውና ለምርጫም የማይቀርብ የከሰረ አካሄድ ነው። እንደ እሴትም መንግስት የሚያራምደው ነፃነት፤ ሰላምና ማህበረሰባዊ ብልፅግናን የማረጋገጥ ራእይ፤ ሕግ-አልባነትንና አመፃን በሚታገስ ስርአት ወይም የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ተፈፃሚ ሊሆን እንደማይችል ሊታወቅ ይገባል፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓቢይ አህመድ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሰጡት መግለጫ
የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን ውስጥ በሁሉም መስኮች መሰረታዊና ተስፋ ሰጪ ለውጦች እየተመዘገቡ ያሉበት ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ ብንገኝም በተጀመረው ስፋትና ጥልቀት ለውጡን ለማስቀጠል የሚደረገውን ጥረት የሚያደነቅፉና የለውጡን አቅጣጫ የሚያስቱ ችግሮችም አብረው እየታዩ መምጣታቸውን በውል እንገነዘባለን፡፡
ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚረዳው አገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት የቆየ ሥልጣኔ ባለቤት የሆነች፣ በዓመታት የጎለበተ የመንግሥት መዋቅርና ሥርዓት ያላት፣ የፍትህና ርትዕ ማህበረ ባህላዊ መረዳትም በህዝቦቿ ዘወትራዊ ህይወት ውስጥ የሰፈነባት እና ህዝቦቿም ለዘመናት ስለነጻነት ታሪካዊ ገድል የፈጸሙባት ታላቅ አገር ናት። በዘመናት ሂደት ውስጥ ከማዕከላዊው መንግስት በተጨማሪ በአገራችን የተለያዩ ክፍሎች ባሉ ማህበረሰቦች ተቀርፀው በቆዩ ልዩ ልዩ ባህላዊ ሥርዓተ-መንግሥታት መሰረት ህዝቦችም ሆኑ መሪዎች በሕግና ደንቦች ተገድበው ሲኖሩ ቆይተዋል። በመላው አገሪቱ የሚኖሩ ሕዝቦች በባህላዊ ትውፊታቸው እና በምሳሌያዊ አነጋገሮቻቸው ጭምር ለፍትህና ርትዕ የሚሰጡት ቦታ እጅጉን ትልቅ ነው።

አብሮነትና መቻቻል በመልካምም ሆነ በፈታኝ የታሪክ አጋጣሚዎች ሁሉ የአገራችን ህዝቦች አይነተኛ ዕሴት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይህች አገር ከትውልድ ትውልድ አንድነቷን ጠብቃ በሰላም የመቆየቷ ዋናው እና አይነተኛው ሚስጢርም ይሄው በመኖር የተፈተነ እና በአብሮነታችንም የገነነ ሀገራዊ ታሪካችን ነው፡፡ በህዝቦቿ መካከል ፀንቶ የኖረውና ከዘር ከሀይማኖት በላይ የቆመው የመተሳሰብ፤ የህብረት፣ የፍቅር እና የጽኑ አብሮነት ባህል ስር ሰዶ መቆየቱም በዘመናት የመውደቅ መነሳት ታሪካችን ውስጥ እንዳንለያይ አርጎ በፍቅር የገመደን የአብሮነት ማህተባችን ነው።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ዋስትና ያለው ዲሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት እንዲፋጠን፤ በሕግ የበላይነት እና በህዝቡ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ መገንባት፣ ይህንንም ለማሳካት የግለሰብና የቡድን መሰረታዊ መብቶች ካለአንዳች ልዩነት እንዲከበሩ ማድረግ እና ለዚህም የሚያሥፈልገውን የፖለቲካ ምህዳር በህገ-መንግስቱ መሰረት ማደራጀት ያስፈልጋል።

ባለፉት አራት ወራት የወሰድናቸው የእርምት እርምጃዎች የሕዝቡን ጥያቄ በተወሰነ ደረጃ በመመለስ ፋታ ያስገኙልን ቢሆኑም መሠረታዊ የሆኑት የፍትህ፣ የዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት ጥያቄዎችን በመመለስ ረገድ ገና ብዙ ይቀረናል። ቀደም ባሉት ዓመታት ይስተዋል የነበረውን ሕግን እንደመሣሪያ ተጠቅሞ የመግዛት አካሄድ ያመጣቸውን መዘዞች ለማረም ከተወሰዱት እርምጃዎች መካከል አንዱ ያላግባብ ይወነጀሉ የነበሩ ዜጎችንና የፖለቲካ ቡድኖችን ጉዳይ በይቅርታና በምህረት ዕልባት እንዲያገኝ ማድረግ ነው። በዚህ ሂደት ላይ እያለን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አንዱ የተጋረጠብን ፈተና ነጻነትንና ሥርዓት አልበኝነትን ባለመለየት፤ መረን የለቀቀ፣ ሕግና ሥርዓትን የማያከብር እንቅስቃሴ እና ድርጊት መስፋፋት ነው።

አሁን በአገራችን እየታየ ያለውና ለሕግ የበላይነት ትልቅ ፈተና የሆነው ጉዳይ ለሕግ ተገዥነትን ወደ ጎን የማድረግ ትልቅ ዝንባሌ ብቻ ሳይሆን በስሜትና በጥላቻ የሚወሰዱ እርምጃዎች፣ ሕግን ወደ ራስ ፍላጎት እና ስሜት በመውስድ በመንጋ የሚሰጡ ስርአት አልባ ፍርዶች ጭምር ናቸው፡፡ ድርጊቶቹ በአንድ ክልል፣ ብሔር፣ ቋንቋ ወይም ሃይማኖት የተወሰኑ አይደሉም፡፡ እንዲህ ያሉት እንቅስቃሴዎች የዜጎችን ደህንነትና የአገሪቱን ሰላም በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈታተኑ ይገኛሉ። በመሆኑም እነዚህ ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመሩ የመጡ በመንጋ የሚሰጡ የፍትህ እርምጃዎች እንደ አገር ለመቀጠል አሳሳቢ እንደሆኑ እና በፍጥነትም መታረም እንዳለባቸው መንግስት በጥብቅ ያምናል።

በአገር-አቀፍ ደረጃ ከተጀመረው የሪፎርም፣ የይቅርታ፣ የነፃነትና የፍትህ ፋና-ወጊ ሥራዎቻችን በተፃራሪ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በጥቂት ግለሰቦችና አካላት በዘፈቀደና በስሜት የሚፈፀሙ በአመዛኙ የብሔር ማንነትን መሰረት ያደረጉ አካላዊ ጥቃቶች፤ ግድያዎች፤ የንብረት ውድመቶችና መፈናቀሎች የሕዝቡን ሰላም፤ ነፃነትና የኑሮ ዋስትና ከመሰረቱ እያናጉ በመሆናቸው ከእንግዲህ መንግስት እንዲህ ያሉ ተግባራትን ፈፅሞ የማይታገስ መሆኑን ሁሉም አካል በውል ሊገነዘብ ይገባል።

በአዳጊ የዴሞክራሲ ሂደት ውስጥ ከመሆናችን አንፃር የህዝባችንን ዘርፈ-ብዙ ፍላጎቶች በአንድ ጀምበር ማሟላት የሚቻል ባይሆንም በፈጣን፣ ተስፋ ሰጪ እና ትክክለኛ መስመር ውስጥ የገባን በመሆኑ እንደ ሀገር መውደቅም ሆነ ወደ ኢ-ዲሞክራሲያዊ አሰራሮች መመለስ ልንቀበለው የማንችለውና ለምርጫም የማይቀርብ የከሰረ አካሄድ ነው። እንደ እሴትም መንግስት የሚያራምደው ነፃነት፤ ሰላምና ማህበረሰባዊ ብልፅግናን የማረጋገጥ ራእይ፤ ሕግ-አልባነትንና አመፃን በሚታገስ ስርአት ወይም የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ተፈፃሚ ሊሆን እንደማይችል ሊታወቅ ይገባል፡፡

ስለሆነም በሀገራችን የዜጎቻችንን መብት እና ነፃነት ለማረጋገጥና የአካል፣ የህይወትና የኑሮ ዋስትናቸውን ለማስጠበቅ ብቸኛው መሳርያ ሕግና ሕገ-መንግስታዊ ስርአትን በሙሉ አቅም ማስከበር በመሆኑ፤ ማንም ሰው ህግ ሲተላለፍ ተጠያቂ የሚደረግበትን የአሰራር ስርአት መዘርጋት እና መተግበር እንደዜጋ ለእያንዳንዳችን፤ እንደ ሀገርም ለሁላችን የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ስለሆነ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከመንግስት ጎን በመሆን ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪዬን አቀርባለው፡፡

የመንግሥት የፀጥታ አካላትና ባለሥልጣናት የሕግ የበላይነት በተባባሪነት- ዝምታም ሆነ በድርጊት፤ በግለሰቦች ወይም በቡድኖች ሲጣስ በቸልታ ባለመመልከት ለህግ የበላይነት መከበር በሙሉ አቅም እንድትንቀሳቀሱ በጽኑ እያሳሰብኩ ችግሮችን ከሥር መሠረቱ ለመፍታት ስለእኩልነት፤ ስለፖለቲካና ኢኮኖሚ ፍትህ የምናደርገው ትግል ከማህበረሰባችን የሞራልና የሀይማኖት እሳቤዎች ጋር የተዋሃደ እንዲሆን ከሀይማኖት አባቶች፣ ከምሁራን፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከጎሳና ባህላዊ መሪዎች እንዲሁም ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ሰፊ ስራ እንደሚጠበቅ በጥብቅ ላሳስባችሁ እወዳለሁ፡፡

ከምንም በላይ የግልና የቡድን ጥቅሞቻችሁን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማስጠበቅ እየቻላችሁ በተለያዩ ወንጀሎችና ሰላምን የማደፍረስ እኩይ ተግባራት ላይ ለመሰማራት የምታስቡ አካላት ከድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ እያሳሰብኩ በማንኛውም የህዝብን ፀጥታ በሚያደፈርሱና ህዝብን ከህዝብ በሚያጋጩ ህገወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርቶ የተገኘ እንዲሁም ለእንደዚህ አይነት ህገወጥ ተግባራት በምንም መልኩ ትብብር ያደረገ አካል ላይ ህግን ተከትሎ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ መንግስት ቁርጠኛ እንደሆነ በጥብቅ ለማሳወቅ እወዳለሁ፡፡

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን አብዝቶ ይባርክ!!

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   አሜሪካ ለጊዜው ሲባል የከረመ ሃሳብ ያካተተ መግለጫ አወጣች፤ ምርጫውን በተዘዋዋሪ ደግፋለች
0Shares
0