“Our true nationality is mankind.”H.G.

የት ላይ ነን? ዳንኤል ኪባሞ -ዶ/ር

የአፈና ሥርዓት ልዩ ባሕርይው ሕዝብን አቅመ-ቢስ ማድረጉ ነው፡፡ አገዛዙ ቀዳሚ የአገርና የሕዝብ ተቆርቋሪ፣ የአገዛዙ ተቀናቃኞች የሕዝብ ጠላቶች ሆነው የሚቀርቡበት፤ ይህን ትርክት ሕዝብ በውድም በግድም አሜን ብሎ እንዲቀበል የሚደረግበት፤ የማይቀበሉ አካላት የሚታሰሩበት፣ የሚገደሉበትና የሚሳደዱበት ሥርዓት ነው የአፈና ሥርዓት፡፡

ተቀናቃኝ ኀይሎች በልዩ ልዩ እመቃ ምክንያት ረብ-የለሽ ሆነው የሚታዩበት እና በሥልጣን ላይ ያለው የፖለቲካ ኀይል በምንም ዓይነት መንገድ ሊነቀነቅና ሊሸነፍ የማይችል (invincible) ሆኖ የሚታይበት ወይም እንዲታይ የሚደረግበት ሥርዓትም ነው፡፡

የለውጥ ኀይሎች ተቀዳሚ ተልዕኮ ይህንን የአፈና አገዛዙ ያሰፈነውን የ“አይነቀነቅም፤ አይሸነፍም” አስተሳሰብ በተግባር መናድ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. ታኅሣሥ 17 ቀን 2010 ሞሐመድ ቧዚዚ ራሱን አቃጥሎ ከገደለ በኋላ የቱኒዚያ ወጣቶች ገንፍለው ወደ አደባባይ በመውጣት ያደረጉት ይህንን ነበር፡፡ የቱኒዚያ ወጣቶች ትልቁ ድል የቤን አሊ አምባገነናዊ አገዛዝ የማይፈርና የማይገረሰስ በተግባር ማሳየት መቻላቸው ነው፡፡ አምባገነነናዊ አገዛዝ አንዴ ሊደፈርና ሊገረሰስ እንደሚችል በሕዝቡ ዘንድ ግንዛቤ ከተያዘ ሥርዓቱ (የፖለቲካ ማሻሻያ ካላደረገ በስተቀር) በነበረበት አካሄድ በሥልጣን ላይ የመቆየት ዕድሉ የመነመነ ነው፡፡

በአገራችን በአቶ መለስ ይመራ የነበረው ኢሕአዴግ ለ14 ዓመታት አስፍኖት የነበረው የ“አይነቀነቅም፤ አይሸነፍም” መንፈስ ከባድ ነበር፡፡ በ1997 ዓ.ም. የተካሄደውን ብሔራዊ ምርጫ ታሪካዊ የሚያሰኘው፣ ያ ምርጫ የአቶ መለስ ኢሕአዴግ አስፍኖት የነበረውን የ“አይነቀነቅም፤ አይሸነፍም” መንፈስ በመስበሩ ነው፡፡ አቶ መለስ ሕዝቡ የአገዛዙን ስስ ብልት በደንብ እንደተገነዘበውና አንድ ቀን እንደሚጥለው ሲገነዘቡ፣ መንግሥታቸው በአንድ በኩል ያለ የሌለ ኀይሉን በመጠቀም የተቃውሞ ጎራውን ማንኮታኮት ሥራዬ ብሎ ተያያዘው፤ እዚያው በዚያው ደግሞ “ልማታዊ መንግሥት” ያሉትን የልማት አማራጭ ይዘው ከተፍ በማለት፣ አገሪቱ በልማት ላይ እንድትረባረብ፣ ወጣቱም በገፍ ወደ ሥራ እንዲገባ ሰፊ ሥራ ለመሥራት ሞከሩ፡፡ መገናኛ ብዙሃኑም፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትም፣ ወጣቶችም፣ እማውራዎችም በአንድ ቃል ስለልማት ማውራት ጀመሩ፡፡ ኢትዮጵያ ለተከታታይ ዓመታት ባለ ሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች እንደሆነ፣ በዚህም ምክንያት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከመካከለኛ ገቢ አገሮች ተርታ እንደምትሰለፍ፣ ወዘተ. ሌት ተቀን ተነገረን፡፡ አቶ መለስም የልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ መሪ ተዋናይ ሆነው ቀረቡ፡፡ ይህን ካደረጉ በኋላ በ2002 ዓ.ም. ኢሕአዴግ 99.6 በመቶ በሆነ ድምጽ ማሸነፉን፣ ውጤቱም በአገራችን የአውራ ፓርቲ ሥርዓት እየተገነባ መምጣቱን እንደሚገልጽ ነገሩን፡፡ ድርጅቱ በዚህ ሳይወሰን በ2007 ዓ.ም. መቶ በመቶ ማሸነፉን በመኩራራት ስሜት ገልጾልን እንደነበርም አይዘነጋም፡፡

ይህ የኢሕአዴግ ማበጥና የተቃውሞው ጎራ መዳቀቅ በሕዝቡ ዘንድ “ኢሕአዴግ አይደፈርም፤ አይነቀነቅም፤ አይሸነፍም” የሚል ስሜትና ተስፋ መቁረጥ ፈጥሮ ነበር፡፡ 
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ይህንን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ ስሜት መሸርሸር በመጀመሩ ፋና ወጊ እንቅስቃሴ ሲሆን፣ እሱ በአገዛዙ ከባድ በተር ምክንያት ከተዳከመ በኋላ የአዲስ አበባንና የአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞንን የጋራ ማስተር ፕላን በመቃወም የተጀመረው የኦሮሞ ወጣቶች እንቅስቃሴም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ በሕገ-ወጥ መልኩ ሊያፍኑት የመጡትን አካላት እጀን አልሰጥም በማለት “እምቢ” ማለቱና ራሱን ሲከላከል የተወሰኑትን መግደሉ ደግሞ ከሁሉም በላይ አገዛዙ የማይደፈር አለመሆኑን በግልጽ ያሳየ እጅግ ታሪካዊ ክስተት ነበር፡፡ ከዚያች ታሪካዊ ዕለት በኋላ፣ አገዛዙ የአስቸኳይ ጊዜ ቢያውጅ፣ በዐሥር ሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን እያፈሰ ቢያስር፣ ተቃዋሚዎችን በጠራራ ጸሐይ ቢገድል፣ በአጠቃላይ አለኝ የሚለውን ስትራቴጂ ሁሉ ቢከተል በምንም ዓይነት ወደ ቀደመ አቅሙ ሊመለስ አልቻለም፡፡

እነዚህ ወሳኝ የሆኑ ክስተቶች ሕዝብ እንዲተባበርና አቅም እንዲያገኝ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ሕዝቡ አገዛዙ ሊደፈርና ሊገደሰስ እንደሚችል ሲረዳ በየጊዜው አቅሙ እያደገ መጥቶ በመጨረሻም ከሥርዓቱ ውስጥ የሕዝቡን ጥያቄ የሚደግፉ የለውጥ ኀይሎች በመውጣታቸው አፋኙ አገዛዝ ተቀይሯል፡፡ አገሪቱ አሁንም በኢሕአዴግ እንደምትመራ የታወቀ ቢሆንም የአሁኑ ኢሕአዴግ እንደ አቶ መለስ ኢሕአዴግ ፈላጭ ቆራጭ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የታየው ትልቅ ለውጥ ሕዝቡ በትግሉ ሥርዓት መቀየር እንደሚችል ማመኑ ነው፡፡ ይህ ትልቅ ነገር ነው፡፡

የሆነ ሆኖ፣ አምባገነናዊ አገዛዝን ታግሎ መቀየር ትልቅ ስኬት ቢሆንም ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ካልተቻለ ለውጡ ትርጉም አይኖረውም፡፡ የኢትዮጵያዊያን ትልቁ ፈተና ይህ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኀይሎች መሀከል ያለው አቋም የተራራቀ ከመሆኑም በላይ፣ የተለያየ አቋም ያላቸው ኀይሎች የጋራ መድረክ አግኝተው በመሀከላቸው ስላሉት የተራራቁ አቋሞች የሚወያዩበት፣ የሚመካከሩበት እና ልዩነቶቻቸውን የሚያጠቡበት መድረክም የለም፡፡ ሌላውና ዋናው አደጋ፣ ሥልጣኔን ተነጠቅሁ የሚለው ኀይል ሥልጣኑን ለማስመለስ፣ “ተራው የእኛ ነው” የሚል እምነት ያለው ኀይል የራሱን ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅ እና ለውጡ እንዲቀጥል የሚፈልገው ወገን ሒደቱ እንዲቀጥል በሚያደርጉት የተናጠል ሩጫ አገሪቱን ፈተና ላይ መጣሉ ነው፡፡ በየቦታው ሁሉም የየራሱን ጎሳና አካባቢ እየያዘ በመንግሥት ውስጥ መንግሥት የመመሥረት አዝማሚያ እየታየ ነው፤ የመንጋ ፍትሕ አስተሳሰብ ስር እየሰደደ ነው፤ ዜጎች በሰላም ወጥተውና ሠርተው የሚገቡበት ሁኔታ እየጠበበ ነው፤ ኢትዮጵያዊያን በየቦታው እንደ ሌላ ዜጋ እየተቆጠሩ በገፍ እየተፈናቀሉ ነው፤ ሥርዓት አልበኝነት እየነገሠ ነው፡፡ ይህ ሁሉ በጣም አስፈሪ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ መረን-የለሽ አካሄድ ከቀጠለ የሕዝብ ትኩረት ከዴሞክራሲ ይልቅ ወደ ሰላምና መረጋጋት ይወርዳል፡፡ ትልቁ መከራ ይህ ነው!

ሽግግሩ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በሚያዋልድ መልኩ ፍጻሜ ካላገኘ ለሁላችንም ትልቅ አደጋ ነው፡፡ ሁላችንም አሸናፊዎች ልንሆን የምንችለው ሰላምና መረጋጋት ሲኖር፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሲገነባ እና የሕግ የበላይነት ሲከበር ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአርቆ አሳቢነት መንፈስ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል፡፡ ሁላችንም በብዙ ወገኖቻችን መስዋዕትነት የተገኘው ይህ ታሪካዊ ዕድል እንዳያመልጠን ዘብ መቆም ይገባናል፡፡ ሁሉም ዜጋ የፈለገውን አመለካከት መያዝ የሚችልበት፣ የፈለገውን እምነት በነጻነት ማራመድ የሚችልበት፣ የፈለገውን መምረጥ ብቻ ሳይሆን መመረጥም የሚችልበት ወዘተ. ሥርዓት፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሆኑን አውቆ የዴሞክራሲ ዘብ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያችን ከዚህ በኋላ አምባገነናዊ አገዛዝ የምትሸከምበት አቅም የላትም፡፡

The Black lion

0Shares
0