የዓለም ባንክ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለኢትዮጵያ ሊሰጥ መሆኑን ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ አስታወቁ። የአለም ባንክ ድጋፉን ለማድረግ የወሰነው በኢትዮጵያ በታዩት መሻሻሎች ምክንያት እንደሆነ ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ በዛሬው ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስረድተዋል።

ጠቅላይ ምኒስትሩ “በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ቢያንስ አንድ ቢሊዮን ዶላር በቀጥታ በጀታችንን ይደግፋል። ይኸምንድነው ወደ ሰላም ጎዳና እየገባችሁ ነው። ሰላም ካለ ልማት ይመጣል። አካታች ሆናችኋል። እያሳተፋችሁ ነው የሚል ዕምነት በማደሩ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።  የዓለም ባንክ እና ሌሎች ተቋማት በመንግሥት እና በተቃዋሚዎች መካከል ከፈጠረው የ1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ ለኢትዮጵያ የሚያደርጉትን የበጀት ድጋፍ አቋርጠው ነበር።

የኢትዮጵያ ብሔራዊምርጫ ቦርድ በገዢው ግንባር እና በተቃዋሚዎች ዘንድ ተዓማኒነት እንዲኖረው አድርጎ የማደራጀት ሥራ በ2011 ዓ.ም. እንደሚከወን ጠቅላይ ምኒስትሩ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ አድርገዋል። መንግሥታቸው የምርጫ ሒደትን በኤሌክትሮኒክ ቴክኖሎጂ የማካሔድ ውጥን እንዳለውም ገልጸዋል። “እኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ ማገልገል የምፈልገው በሚቀጥለው ምርጫ ካሸነፍኩ ብቻ ነው” ያሉት ጠቅላይ ምኒስትር የለውጥ ያሉትን ጊዜ የመግፋት ሐሳብ እርሳቸውም ሆኑ የሚመሩት ኢሕአዴግ እንደሌላቸው አስረድተዋል።

የዶይቼ ቬለ የአዲስ አበባ ወኪል ዮሐንስ ገብረ እግዚዓብሔር እንደዘገበው ጠቅላይ ምኒስትሩ ስልጣን ከያዙ የመጀመሪያ በሆነ ጋዜጣዊ መግለጫቸው በኤኮኖሚያዊ እና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ መንግሥቱ ኃይለማርያም፣የሼክ መሀመድ አል አሙዲ እና የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አብዲ መሀመድ ዑመር እጣ ፈንታን የተመለከቱ ጉዳዮች ተነስተዋል።

ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ የቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ምኅረት እንደማያገኙ ገልጸዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ በዛሬው ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “አዋጅ ከህገ-መንግሥት በታች የሆነ ሕግ ነው። ህገ-መንግሥቱ በምኅረት አዋጅ የቀይ ሽብር ጉዳይ እንደማይካተት በግልፅ ያስቀምጣል። ስለዚህ አሁን ባለው ሁኔታ ኮሎኔል መንግሥቱ በምኅረት ወደ ኢትዮጵያ አይመጡም” ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል።

በስደት ዚምባብዌ የሚኖሩት ኮሎኔል መንግሥቱ ምኅረት ሊያገኙ የሚችልበት ዕድል ሊኖር እንደሚችል ግን ፍንጭ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ምኒስትር አብይ “ሕገ-መንግሥቱ ይኸን አንቀፅ አሻሽሎ እንደዚህ አይነት ወንጀሎች የሚያካትትበት ዕድል ወደ ፊት ካጋጠመ እሳቸውም ሊካተቱ ይችላሉ። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ሕገ-መንግሥቱ በግልፅ በቀይ ሽብር የተሳተፉ ኃይሎችን በምኅረት አዋጅ ማስተናገድ እንደማይቻል ስለሚገልፅ እና አዋጅ ከሕገ-መንግሥቱ በታች ስለሆነ ከአጭር ጊዜ አይጠበቅም” ብለዋል።

ጠቅላይ ምኒስትሩ የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ገልጸዋል። “እሳቸውም ሌሎችም ሥልጣናቸውን በአግባቡ ያልተጠቀሙ ሰዎች በሕግ ይጠየቃሉ”ያሉት ጠቅላይ ምኒስትር አብይ “እንዴት፣ መቼ እና በማን የሚለው ጉዳይ በጋራ እንከታተላለን” ብለዋል።

በሳዑዲ አረቢያ በእስር ላይ የሚገኙት የሼክ ሙሐመድ አል-አሙዲ የተወሳሰበ እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ምኒስትር አብይ “ጉዳያቸውን እየተከታተልን ነው። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እያነሳን ነው። በቅርቡም ከተሳካ እናያቸዋለን ብለን እናስባለን” ሲሉ ተናግረዋል። ጉዳያቸው በፍጥነት እንዲያልቅ ጫና ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉም አስረድተዋል።

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር – እሸቴ በቀለ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *