የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) በሚያስተዳድረው የአማራ ክልል ባለ ይዞታ ላይ ሰፍረው የሚገኙ የሱዳን ወታደሮች በፍጥነት ለቅቀው እንዲወጡ ጠየቀ። ለ“ህዝቦች መፈናቀልና መሰደድ፣ ለህይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑ” ያላቸው የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች ትኩረት እንዲሰጣቸው እና “በህዝብ ነጻ ተሳትፎ እንዲፈቱ” እንደሚታገል አስታውቋል።

    
Amhara National Democratic Movement (ANDM) logo
Amhara National Democratic Movement (ANDM) Logo von Amhara National Democratic Movement ANDM (ANDM centeral Comittee office)

ብአዴን ይህን ያስታወቀው የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ በዚህ ሳምንት ባካሄደው ስብሰባ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች በዘረዘረበት መግለጫው ነው። በአስራ ነጥቦች የተከፋፈሉት ውሳኔዎች በርከት ያሉ ጠንካራ አቋሞች የተንጸባረቁበት ነው። ከህገ መንግስታዊ ማሻሻያ እስከ የድርጅቱ ስያሜ፣ የፖለቲካ ፕሮግራም እና መተደዳደሪያ ደንብ መቀየር ድረስ ባሉ ጉዳዮች ላይ የተላለፉ ውሳኔዎች በመግለጫው ተካትተዋል።

ብአዴን ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች ውስጥ ተደጋጋሚ ግጭቶችን የሚያስተናግደው እና እስካሁንም እልባት ያላገኘው የኢትዮ ሱዳን የድንበር ጉዳይ አንዱ ነው። በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የድንበር ማካለል ጉዳይ በዘላቂነት እስኪፈታ ድረስ የሁለቱም ወገን አርሶ አደሮች የያዙትን የእርሻና የደን መሬት እንደያዙ እየተጠቀሙ እንዲቆዩ በሁለቱ ሃገራት መንግስታት መካከል ስምምነት መደረሱን መግለጫው አስታውሷል።

በአማራ ክልል በመተማ ወረዳ ልዩ ስሙ ደለሎ የተባለውን አካባቢ በተመለከተ ተላልፎ የነበረው ውሳኔ ግን “የሚመለከታቸ ውን አካላት ያላሳተፈና የጋራ አቋምም ያልተያዘበት ነበር” ሲል ተችቷል። የማዕከላዊ ኮሚቴው መግለጫ “ታሪካዊ ዳራውንና ነባር የይዞታ መብታችንን ያላስጠበቀ” ሲል የጠቀሰው ይህ ውሳኔ “ብአዴንና አመራሮቹ ለረጅም ጊዜ በህዝብ ዘንድ ባልተገባ መልኩ ሲታሙና ሲጠረጠሩ እንዲቆዩ አድርጓል” ብሏል። መግለጫው የውሳኔውን ምንነት በዝርዝር ባያብራራም “በፌደራል መንግስት በኩል አስቸኳይ ማስተካከያ እንዲደረግበት” አሳስቧል።

መግለጫው በአማራ ክልል በቋራ ወረዳ ልዩ ስሙ ነፍስ ገበያ በተባለው አካባቢ ሰፍሮ ስላለው የሱዳን ጦርም አንስቷል። የሱዳን ወታደሮች በአካባቢው እንዲሰፍሩ የተደረገው “ለጋራ የጸጥታ ማሰከበር ስራ ይጠቅማል” በሚል ስምምነት እንደነበር መግለጫው አስታውሶ ሆኖም ጦሩ “ይዞታውን እያሰፋፋና ቋሚ ካምፕ እየገነባ ከያዘው ጊዚያዊ ይዞታ ሳይለቅ መቆየቱ ተገቢ አይደለም” ብሏል። “የካምፑ መኖር የድንበሩን ጉዳይ የበለጠ እያወሳሰበውና የክልሉ አርሶ አደሮችም የእርሻ ስራቸውን በሰላም እንዳያከናውኑ እንቅፋት እየሆነ ይገኛል” መግለጫው አትቷል። የሱዳን ጦር “በፍጥነት ከይዞታችን ለቆ እንዲወጣና የፌደራል መንግሥትም ይህንኑ እንዲያስፈጽምልን እንጠይቃለን” ብሏል የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ በመግለጫው።

ብአዴን ከድንበር ባሻገርም በክልሎች ወሰን ጉዳይ ላይም ያለውን አቋም ይፋ አድርጓል። “ባለፉት ዓመታት ክልላችንን ጨምሮ በመላ ኢትዮጵያ ለህዝቦች መፈናቀልና መሰደድ፣ ለህይወት መጥፋትና ንብረት መውደም ምክንያት የሆኑ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው በህዝብ ነጻ ተሳትፎ እንዲፈቱ” ትግል እንደሚያደርግ ብአዴን አስታውቋል። የኢትዮጵያ የፌደራል መንግስት አባል የሆኑ ክልሎች አከላለል ሕገ መንግስቱን መሰረት ባደረገ መልኩ እንዲፈጸም እንሚታገልም ድርጅቱ ገልጿል። የክልሎች አከላለል “በህዝቦች እውነተኛ ፍላጎትና ንቁ ተሳትፎ፣ ብዝሃነትንና ሃገራዊ አንድነትን በሚያጠናክር አግባብ” መከናወን እንዳለበት ብአዴን አሳስቧል።

የአማራ ክልል በወልቃይት የወሰን ጉዳይ ከትግራይ ክልል ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ የቆየ ሲሆን ጉዳዩ አሁንም ሳይፈታ በእንጥልጥል ላይ እንዳለ ይታወቃል። በክልሉ ከሶስት ዓመት በፊት በቅማንት ማንነት ጥያቄ የተነሳ ግጭት ለበርካቶች መገደል፣ መቁሰል እና የንብረት መውደም መንስኤ መሆኑ ይታወሳል። የክልሉ መንግስት በቅማንት ማህበረሰብ ላይ ለደረሰው ጥፋት ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን የህዝቡን ራስን በራስ የማስተዳደር ተቀብሎ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ማድረጉ ይታወሳል።

 ጀርመን ሬዲዮ ተስፋለም ወልደየስ 

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *