“Our true nationality is mankind.”H.G.

አሁንስ እኔም ወደ አገሬ የምገባበት ጊዜ ናፈቀኝ! (ይነጋል በላቸው)


ሆ! ከመኖሪያ ቤቴ 10 ኪሎ ሜትሮችን ያህል በሚርቀው ቤተ መንግሥቴ  እየተካሄደ ያለው የለውጥ ማዕበል የዘመናት የራስ ምታቴን እያሻለው ከመምጣቱም ባሻገር እኔም ወደ ሀገሬ ለመግባት እንዳኮበኩብ አድርጎኛል (ወይ ጊዜ! ‹ቤተ መንግሥቴ› ለማለትም በቃሁ አይደል? ጌታ ይክበር፤ ይመስገን፡፡ በቀረችኝ ጥንጥዬ የሕይወት ዘመኔ ይሄን የመሰለ ለጊዜውም ቢሆን የሲዖልን ኑሮ የሚያስረሳ የእፎይታ ጊዜ አያለሁ ብዬ በጭራሽ አስቤው አላውቅም ነበር )፡፡ እየታዬ ያለው ነገር እኮ እኮ ትንግርት ነው፡፡ መንጌ አንድ ወቅት ንግግር ሲያደርግ በስሜት ተውጦ “እኛ እኮ እኮ …” ሲል ስለሰማሁ ያኔ የያዝኳት ይቺን “እኮ እኮ” እስካሁን አለቀቅኋትም፡፡ “አድሃሪያን እኮ እኮ ንቀውናል! ተዋርደናል ጓዶች!…” ሲል ያዳመጥኩት መሰለኝ፡፡ ወይ ዘመን – ስንቱን ያሳየናል!

አሁን አሁን ደስ ይላል፡፡ … ዓለምፀሐይ ወዳጆና ጓደኞቿ ትናንትና ገቡ፤ ደስ ይላል፡፡ ጃዋር መሀመድ እንኳን ገባ አይደል? ይህም ደስ ይላል፡፡ ግን ግን ዐቢይና ቡድኑ ይህን የኛን ልጅና ሰሞኑን የገባውን የኔኛውን ሙሉቀን ተስፋውን ቢሮው ጠርቶ ትንሽ ይሞርዳቸው፡፡ ካልተሞረዱ የዋልንበትን ሁሉ አረም ባረም የሚያደርጉ በአንድ ወይ በሌላ ምክንያት በኅብረተሰቡ ዘንድ ተሰሚነታቸው ከፍተኛ የሆኑ ውድ ዜጎቻችን በሀገር ቤትም በውጪም አሉና ችግሮቻችን ከመቀረፍ ይልቅ እየተባባሱ የመሄድ ዕድላቸው የጎላ ነው፡፡ አንድ ዝነኛ ዜጋ የተንሻፈፈ አስተሳሰብና አመለካከት ካለው ብዙ ሰው ይዞብን ይጠፋልና ቀድመን እሱን ነው ማከምና ቀጥ ብሎ እንዲጓዝ ማረቅ፡፡ አንድ አፈኛ ነበረ አሉ፡፡ ያ አፈኛ ሰው ራሱ በእግዚአብሔር አያምንም – ግን ሚሊዮኖችን በእግዚአብየር እንዲያምኑ ከተለያዩ ባዕድ አምልኮቶችና እምነቶች እንዲሁም ከኢ-አማኒነት(ኤቲይዝም) ይስባቸው ነበር አሉ፡፡ አንደበት ቀላል አይደለም፡፡ ቃል እሳት ነው፡፡ ቃል ያድናል፤ ይገድልማል፡፡ እንኳንስ የነጃዋርን የመሰለ ትንታግ ምላስ የኔን መሰሉ ጎልዳፋ አንደበት ራሱ በየ“ማታው ትምህርት ቤት” ስንቱን እንደሚያፈዝ የሩቅና የቅርብ ትዝታየ ምሥክር ነው፡፡

ባልጀመርኩበት መስመር ሄድኩና ጠፋሁ – በደስታ ስካር፡፡  እናላችሁ እኔም ወደ አገሬ ግባ ግባ የሚል መንፈስ ሽው ይልብኛል፡፡ ልገባ ነው፡፡ ሁላችንም እንግባና በየአቅማችንና በየችሎታችን ተረባርበን ሀገራችንን ከሞት እናንሳት፤ ያ ወሮበላ እስራኤል ዳንሳ የሚሉት የዲያብሎስ ሎሌ እንደሆነ መለስን እንጂ ኢትዮጵያን ከሞት ለማንሳት ጥሪ አላቀረበም፡፡

እርግጥ ነው – ብዙ ነገሮች ገና ናቸው – የተረጋጉ ስለመሆናቸው እርግጠኛ መሆን ይቸግራል፡፡ ብዙ ነገሮችን ስናይ ደግሞ ለውጡ መሬት የረገጠ ይመስላል፡፡ ግራ ገባኝ፤ “እባብን ያዬ በልጥ በረዬ” እንዲሉ ሆኖብኝ እኔማ የወያኔው አሰቃቂ ዘመን የፈጠረብኝ ድንጋጤ (shock) ገና በእውኔ ሳይቀር እያስበረገገኝ አንዳንዴ የገዛ ጥላየን ጭምር እየፈራሁ ነው የምራመደው – ቀላል ቀጠቀጡን እንዴ! ያን የመሰለ ዘግናኝ ሕይወት ያሳለፈ ዜጋ የወያኔን ዐረመኔያዊ አገዛዝ ገና ለመጪዎቹ ሃያና ሠላሣ ዓመታት ቢፈራና ተኝቶ እንኳን ቢቃዥ አይፈረድበትም፡፡ አንዳንድ ትግሬዎች ታዲያን ይገርሙኛል፡፡ ወደሩብ ሩብ ቢሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ እግሩ ሥር አንበርክኮ ሲረጋግጥ የነበረን ያን የመሰለ የጥቁር አፓርታይድ ሥርዓት እንዲቀጥል መፈለጋቸውና ካልቀጠለ ደግሞ – በሕወሓት የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በመጠለፍ  – እንደተበደሉና መብታቸው እንደተጓደለ የሚቆጥሩ፣ በዚያም ሳቢያ ለውጡን አጥብቀው የሚታገሉ መሆናቸውን ሲገልጡ ሳይ ይደንቀኛል፡፡ “ያንተ ልጅ የኔን ልጅ መትቶት ከሆነ ምች ይምታው፤ የኔ ልጅ ያንተን ልጅ መትቶት ከሆነ ግን መቼም…” አለ አሉ አንዱ – እርግማኑ ወደርሱ ልጅ ሲሆን “ምች ይምታው” ለማለት አንጀቱ አልችል ብሎ፡፡ ፍርድ ለራስ ነው፤ ፍርድ ከራስም ነው፡፡ በአድልዖና በዘረኝነት ዱላ ቀጥቅጦ ከሚገዛ የጫካ ዐውሬ “በፍቅርና በፍትህ ሁሉን አስማምቼ ላስተዳድር” ወደሚል አስተዋይ አመራር መሸጋገር በአንዳንድ ተጋሩ የሚጠላ ከሆነ ምን ማለት እንደሚቻልና ምንስ ዓይነት ትርጉም ሊሰጠው እንደሚችል  አላውቅም፡፡ “ኢይጥዕም መዐር ለአድግ ዘእንበለ እንጉስታር” ይለዋል ግዕዙ ይህን መሰሉን ፍች-አልባ ኹነት፡፡ ለነገሩ ባልተነሳሁበት ነጥብ ከዚህ በላይ መራመድ ስህተት ነው፡፡

እናላችሁ “ወዳገሬ ብገባ የሚተናኮለኝ ይኖር ይሆን?” እልና ደግሞ እጨነቃለሁ፡፡ እጅግ በጣም ፈሪ ነኝ – ከዘር ይሁን ከአስተዳደግ አላውቅም የለዬለት ንዴት ውስጥ ካልገባሁ በስተቀር ክፉ ቃል እንኳን ማውጣት ይከብደኛል –  እጄን ወደ ቃታ መሰንዘር ይቅርና ማለቴ ነው፡፡ ዕድሜ ለፍርሀቴ አንድም አካሌ ሳይጎድል፣ ለአንዲትም ቀን ሳልታሰርና ከመንጋው የተለዬ ችግርም ሳይደርስብኝ አሁን ላይ ደርሻለሁ፡፡ “ፈሪ ለናቱ ያገለግላል፤ ምጎጎ ስ’ጥድ ሙግድ ያቀብላል” ይባላል፡፡ ፈሪ ለዘርም ቢሆን ይተርፋል፡፡ እናም በፍርሀቴ ምክንያት ለዛሬና ለዘሬ ተርፌያለሁ፡፡ ስለዚህ ወዳገሬ ልገባ ነው፡፡ ምን ትሉኛላችሁ? ልግባ ወይንስ ባለሁበት ጥቂት ልቆይ? እስኪ ሃሳባችሁን ስጡኝ፡፡ yinegal3@gmail.com  (ነሐሴ 23/ 2010)

የትም ሳልሰደድ ሳይራመድ እግሬ    

አገሬ ላይ ሆኜ ናፈቀኝ አገሬ

ሕዝባዊ ሥነ ቃል

ECADF

0Shares
0