“Our true nationality is mankind.”H.G.

የበረከት ትምክህትና እና ሴራዎች ሲጋለጡ (በናዝራዊ)

የአቶ በረከት ወሬ ሰሞኑን መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ሰውዬው በትእቢት ተወጥረው ባለፉት 28 አመታት ምንም ችግር እንዳልፈጠሩ በግልባጩ ለአማራና ለኢትዮጵያ ህዝብ ልማትና ዲሞክራሲን እንደጉድ ያዥጎደጎዱልን አድርገው እራሳቸውን ክበው አስቀምጠዋል፡፡ አቶ በረከት ሰሞኑን ደጋግመው አንባቢ ነኝ፣ በመጽሃፍ ውስጥ መሽገው እንደኖሩ ወደፊትም ጸሃፊ/ደራሲ እንደሚሆኑ ነግረውናል፡፡

ዋናው ጥያቄ ማንበብዎና ማወቅዎ ባለፉት 27 አመታት ምን ይዞልን መጣ? የሚለው ወሳኝ ነው፡፡ ማንበብ ለምን ይጠቅማል ከተባለ ለራስ ለማወቅ፣ ሌሎችን ለማሳወቅ፣ ስለሰውና ተፈጥሮ ያለንን አመለካከት ለመለወጥ፣ የህብረተሰቡን ችግሮች ተገንዝቦ መፍትሄዎችን በማበጀት ተጨባጭ የሆነ ሰውኛ ለውጥ ማምጣት ነው ወይም ማሳደግ ነው፡፡ እርስዎ ከዚህ አኳያ ማንበብዎ ምን ጠቀመዎ? ለኛስ ምን አስገኘልን? ዜጋን ለማሸማቀቅ፣ ለማፈን፣ ለማግለል፣ ለማሰር፣ ለመግደል፣ ከአገር ለማሳደድ፣ ከሚኖርበት ስፍራ ለማፈናቀል ወይንስ በግልባጩ?

ላለፉት 40 አመታት ለአማራ/ለኢትዮጵያ ህዝብ ሲታገሉ  እንደኖሩ ደጋግመው ሲነግሩን ነበር፡፡ በዚህም ትግልዎ በርካታ ለውጦችን ለክልሉና ለኢትዮጵያ ህዝብ ያስገኙ እነደሆነ ሳይታክቱ በየሚዲያው ሲናገሩ ሰምተናል፡፡ ለውጥ የሚባለው ከርስ ተኮር ወይንስ ሰዋዊ (ሰው ተኮር)ከግብረበላዎች ጋር በመሆን ዶ/ር በድሉ እንዳሉት፣”ለእግራችን መመላለሻ መንገድ አብጅተው ይሆናል እንጂ ለሃሳባችን መረማመጃ” የሚሆን አንድም ድልድይ ማለትም መድረክም ሆነ ሚዲያ ሲከፍቱ አላየንም፡፡  በተቃራኒው የአፈና መዋቅሮችን ሲዘረጉ እንደነበር የ27 አመት ልምዳችን ይነግረናል፡፡ ያ የእርስዎ የግፍና የመከራ ዘመን፣ ያ ህጻናትን ያለአባት/እናት ያለያየ፣ በጠኔ ሲቆላ የነበረ ዘመን፣ ያ በሰዎች መሰቃየት ሲዘባበት የነበሩበት ዘመን፣ ያ ነገሩን ወደኋላ ሄደው ሲያስቡት የሚያስለቅስ ዘግናኝ ዘመን፡፡ ዛሬ በተሸለ አርነት ወጥናል እርስዎም በፈለጉት ሚዲያ ሃሳብዎን መግለጽ ዲሞክራሲያዊ መብት ተጎናጽፈዋል፡፡

እስቲ ቆሜለታለሁ ስለሚሉት የአማራ ክልል ህዝብ ምሬት/ብሶትና በደል ወደኋላ መለስ ብለን እንመልከት፡፡ ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ አማራ ከብዙ ስፍራዎች ሰርቶ ሲኖርበት ቀዬ ሲፈናቀል የት ነበሩ? እኔ መንገድ ወይም ህንጻ ሰርተው ከሚገትሩብኝ ሰርቼ የመኖር መብቴን ቢያስጠበቁልኝ እመርጥ ነበር፡፡ ዜጋው እንኳን ሰርቶ ለምኖ መኖር በማይችልበት ሁኔታ ላይ እንደነበር እናስታውሳለን ( ከአመታት በፊት አይነ ስውራንን ጨምሮ በርካታ “መጤ” የኔብጤዎች ከሃረር ከተማ ውጡ ተብለው እየተጎተቱ ተግዘዋል) ይህን አሳዛኝ ክስተት በፍጹም አንረሳውም፡፡ በዋናነት እነዚህ የኛ አይደሉም ከሌላ አከባቢ የመጡ ናቸው በሚል ዲያቢሎሳዊ ሰው ጠል አባዜ በተለከፉ ሰዎች አማካኝነት አማራው ከአርሲ አርባጉጉ፣ ከደቡብ ጉራፈርዳ፣ ከቤኒሻንጉል፣ ከጋምቤላ፣ ከሃረር፣ ከኢሉባቡር፣ ከጂማ፣ እና ከሌሎችም በ100 ሺዎች ተፈናቅለዋል፣ ተገለዋል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ እስቲ ይተንፍሱልን

ዛሬ የአማራ ክልል የሚባለው (የክልል ሽንሸናው አስተዳደራዊ መሆኑ ቀርቶ የክልል ባለቤትነትን ለህዝቡ ሳይሆን ለብሄር የሰጠ አከላለልን ባልስማማበትም) ኢህአዴግ እራሱ ባወጣው ፌዴራሊዝም መሰረት የክልሉ ወሰን በተገቢው መንገድ ያልተቋጨ፣ በርካታ የክልሉ ቦታዎች ወደ ትግራይ ክልል የተጠቃለሉበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ዛሬ እጅግ አወዛጋቢ የሆነው ይህ ክልላዊ ወሰን ይገባኛል ጥያቄ ማባሪያው መቼ እንደሆነ ወደማይታወቅበት መስመር ይዞን እየሄደ እንደሆነ ይተወቃል፡፡ ጉምቱው ፕሮፌሰር እንደተናገሩት ሹፌሩም ተሳፋሪውም ግራ ተጋብተው ሁሉም ዋይታ ላይ ነው ያለው፣ ባቡሩ መንጉዱን ስቶ ወደ ገደል እየሄደ ነውና፡፡ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂ ከሚሆኑት ቀዳሚ የኢህአዴግ አመራሮች አንዱ እንደሆኑ ከካዱ ማን ሊሆን እንደሚገባው ሊነግሩን ግድ ይሎዎታል፡፡ አለበለዚያ ውሃ ወቀጣ መሆኑ ነው፡፡ እርስዎና ጓደኞችዎ ታወራላቸሁ እኛም እናላዝናለን፡፡ ግን ህዝብ በላጭ ስለሆነ ጆሯችሁን ይዘን መጠየቂያ ጊዜያችን ላይ ደርሰናል፡፡

ኦሮሞ ጠ/ሚኒስትር እንዲሆን ስታገል ነበር ይሉናል፡፡ በዚህ ደረጃ ያለ አንድ መሪ የነበረ ሰው ስልጣንን በችሎታ ሳይሆን በዘር ሲያከፋፍሉ እንደነበር ማሳያ ሰጥተውናል፡፡ ገራሚ ነው፡፡ በሌላ አጋጣሚ አንድ ሰው እንዴት ወደ ስልጣን መምጣት አለበት ቢባሉ በዋናነት በብቃት/በእውቀት መሆን አለበት እንደሚሉን ነው፡፡ እንዘጭ እንቦጭ

ቀሪ ጊዜዎን ባህዳርና ጎንደር ማሳለፍ ቢሹም እንደማይሆን ሲረዱ ተከርብተው ኦሮሚያ ኦሮሚያ በማለት አዳማ ወይ ጅማ ሊሄዱ በተዘዋዋሪ እየተማጸኑ እንደሆነ ፍላጎትዎ ያሳብቃል፡፡ ሌላው አላማዎ እየጠበቀ የመጣውን የአማራውንና የኦሮሞውን ማህበረሰብ አብሮነት ለመከፋፈል፣ ብዥታ በመፍጠር በለመዱት የሴረኝነት ትብተባ ህዝቡን ወደማያባራ ጸብ ውስጥ ለመክተት እንደሆነ ሁሉም ገብቶታል፡፡ ሙከራዎ ሁሉ ድምጽ አለባ ከሆነ ተራ ኳኳታ የተለየ አይደለምና ከሰሞኑ ሌላ ሴራ ይዘው ብቅ ቢሉ ይሻላል፡፡ ያለፈው 27 አመት ሲያገጫጩን የነበሩበት አንሶ ዛሬም እርስ በርስ በጎሪጥ እንድንተያይ፣ ከፋፋይ ሴራ ህዝቡ እንደሚገነዘብ የታወቀ ነው፡፡ ብአዴንና በውስጡ ያለውን የለውጥ አመራር እጎዳ ብለው እየሰሩት ያለው በየሚዲያው ጩሀቴን ቀሙኝ አይነት ንዝነዛ ህዝቡን በባሰ ሁኔታ እልህና ብስጭት ውስጥ እንዳይከቱት ያሰጋል፡፡

ያለፈው ጥቃትዎ ሳያንስ የአማራን ክልል ህዝብ ከሱዳን፣ ከትግራይ፣ ከአፋር ህዝብ ጋር በማቃቃር ውጥንቅጡ የወጣ አካባቢ፣ በአጎራባቾቹ ሁሉ የአማራ ክልል ህዝብ በጥርጣሬ እና በጎንታይነት እንዲታይ ለማድረግ እቅድ መንደፍ ለአንድ በጡረታ ላይ ላለ የቀድሞ ሚኒስትር አሳዛኝም አሳፋሪም ነው፡፡

እራስን የማኮፈስና ሌሎች የድርጅቱን መሪዎች ማንኳሰስ የአቶ በረከት ነጥሮ የወጣ ትምክህት ሌላው ትዝብት ላይ የጣላቸው አመለካከታቸው ነው፡፡ ብአዴን ዛሬ ለአማራው ህዝብ በነጻነት እታገላለሁ ሲል ለምን ቆጨዎትእንደቀድምዎ የወያኔ አሽከር፣ ተላላኪ ሆኜ አልቀጥልም ብሏል፡፡ እርስዎ ግን ወያኔ ጉያ ውስጥ ሆኖ ለመቀጠል ፈልገዋል፣ የግል ውሳኔዎ ስለሆነ መንገዱን ጨርቅ ያርግልዎ፡፡ ከዚህ ቀደም ብአዴንን በመካብ እራሱን በእውቀትና በቁርጠኝነት፣ በዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ወደ ላቀ ደረጃ እያሸጋገረ፣ መሰረቱን የማይናጋ እራይ የሰነቀ፣ ወደፊትን አሳቢ እነደሆነ ድርጅት መሆኑን ሲነግሩን ነበር፡፡ ዛሬ ይህ ሁሉ ደምስሰው እኔ ብቻ ነበርኩ አስተማሪ/አሰልጣኝ፣ ለውጥ ቀማሪ፣ ሰላም ዘማሪ ሌሎች ግን መጽሃፍ ጠልና እራሳቸውን በእውቀት መገንባት ያልቻሉ፣ ለውጥ ጠል እንደነበሩ ሲያወጉን ምን ያህል አምባጋነን እና በትምክህት እንደተዋጡ አመላካች ነው፡፡ ብአዴኖች ይሄን ሰው ይህን ሁሉ አመት ይህን ትምክህት እንዴት ተሸክመው ኖሩ-ቻይ ናቸው፡፡

አቶ በረከት እጅግ ሲበዛ ሴረኛ እንደሆነ እንኳን አዋቂዎች ህጻናት ጭምር ያውቁታል፡፡ ሰሞኑን ከጀመሩት አርፎ ያለመቀመጥ አባዜ ይዞ ሊመጣበት የሚችለውን ጣጣ የተገነዘቡ አይመስለኝም፡፡ ይህ ህዝብ መሃሪ ስለሆነ እንጂ ሰብስቦ እስር ቤት ሊያሰገባን ይችል ነበር ብለዋል ዶ/ር  አብይ በአንድ የተወካዮች ም/ቤት ስበሰባ ላይ፡፡ ይህ ሰው አርፎ ካልተቀመጠ፣ ይቅርታ ካልጠየቀ፣ በወንጀል የማይጠየቅበት ምን ህጋዊ መሰረት አለው፡፡ ኢህአዴግ በዶ/ር አብይ አማካኝነት ይቅርታ ህዝቡን ቢጠይቁም የበረከት አይነቱ ይቅርታ የምንጠይቀው እና ከለውጡ ጎን አንቆምም፣ አንደመርም ካሉ ዝም ሊባሉ ከቻለ ሌሎችንም ሊያበረታታና ለውጡንም ሊያደናቅፉ ስለሚችል ችላ መባል አይኖርበትም፡፡ ይህ እጅግ ሲበዛ አደገኛ አካሄድ ነው፡፡

የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እባካችሁ የድርጅታችሁን ጉዳይ እዛው እንደለመዳችሁት ጓዳ ውስጥ ተነታረኩ፡፡ ዛሬ ሴራው ሲነቃባችሁ እኛን የጨዋታው አካል የምታደርጉት ማጣፊያው ሲያጥራችሁ መሆን የለበትም፡፡ አቶ በረከት ብአዴን ከማእከላዊ ኮሚቴነት ሲያነሳው ድሮ ያልነገረንን እሱ ከ2002 ጀምሮ(መለስም ሳይሞት) የለውጡ መሃንዲስ፣ ሌሎች ደግሞ አደናቃፊ እንደነበሩ የሚነግረን እኛን ለማቄል አስበህ ከሆነ ተሳስተሀል፡፡ ሽረባ አይገባቸውም በሚል እሳቤ እራሱን መጽሃፍ አንባቢ፣ ለውጥ ተያቢ፣ አገርና ህዝብ ገንቢ ከቶ ለማድረግ መሻት ከትምክህት የዘለለ አይደለምና በረከት ሆይ አንሰማህም፡፡ የአማራ ክልልን ከሱዳን፣ ከትግራይና ከአፋር ህዝብ ጋር ለማላተም የዘየደው ሚጢጢ ሴራ ደግሞ ሲበዛ ሁሉንም ሰውዬው ምን ያህል በጥባጭ እንደነበር ማሳያ ነው፡፡ አይመሰልህ እኛ ነቄ ብለናል፡፡

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሕዝብን ማን ይሰራዋል?
0Shares
0