ቁጭ ብድግ አልኩ። ትንፋሼ ሊያንቀኝ ይታገለኛል። የማልውቀው እንግዳ ስሜት ነብሴን ወጥሮ ያዘልለኛል። ልቤ በሃሴት ሰከረች። ያለ አንዳች ማጋነን እንዲህ ያለ ስሜት ተሰምቶኝ አያውቅም። የመንፈስ ልዕልና ሲያበራ አየሁ። ብርሃኑም ሲጎመራ ተሰማኝ። በርካቶች ሲደኑና ፈውስን ሲያውጁ ሳልኳቸው። ይህ ሁሉ የሚሆነው በተቀመጥኩበት ነው። ለምን ይሆን? ምን ተገኝቶ? 

ክፉ ዘርን በሚዘሩ፣ ክፋትን በጀት መድበው በሚስብኩ፣ ቂምን በጀት መድበው በሚግቱ፣ ክፉዎች አንደበት ስንታረድ መኖሬን አየሁና አዘንኩ። ያን ዘመን አሰብኩና አፈርኩ። በዚሁ የክፋት ዘር የደረሰውን ክስረት አሰላሁና ውስጤ ተቆጣ። በክፋት ባቡር ጭነውን በፈለጉበት ፌርማታ ሲያንጠባጥቡንና ሲረጩን የኖርነውን ኑሮ ሳስበው የኪሳራችን መጠን የማይለካ ተራራ ሆነብኝ። ይህም ስሜት የተሰማኝ እዛው በተቀመጥኩበት ነው።

በአንድ ወቅት አንድ ባልደረባዬ ቤት ስሄድ እሳሎኑ ውስጥ የገተረውን ቲቪ ፊቱን ወደ ግድግዳ አዙሮት አየሁ። ” ምነው” ብዬ ምክንያቱን ጠየኩት። ” ምን የሚሰማ ነገር አለ። እንዳልጥለው እንደ እኔው ዘመን ይጠብቅ ብዬ ነው። ለሰው እንዳልሰጠው እኔ የጠላሁትን ያ ሰው ምን ፈርዶበት” ሲል መለሰልኝ።

አንድ ትልቅ ሰው በአንድ ወቅት እቢሯቸው ሄጄ ስናወራ ” ልጆች ከተኙ በሁዋላ ነው ቲቪ የምንከፍተው” አሉኝ። ምክንያቱን ሲያስረዱኝ ሃዘን እየተናነቃቸው ነበር። እሳቸው እንዳሉት መሪዎቹ ንግግራቸው ሁሉ ስድብ ነው። አንዳንዱ ለመስማት ይቀፋል። “ገምተናል፣ በስብሰናል፣ ሸተናል…” ሰዎችንም ሲያሳቅቁ የሚጠቀሙት ስድብ ነው። ከዚህም በላይ ውሽት… እናም ልጆቻቸው እሳቸው እየሰሙና እያዩ ይህንን እንዳይማሩ ቲቪ አያዩም። 

ይህ ሁሉ የሃሳብ መተራመስ እንዲሁ አልመጣም። መነሻው ለማ መገርሳ የሚባሉት የኦሮሚያ ርዕሰ መስተዳድር የዓመቱ የበጎ ሰው ተሸላሚ መሆናቸውን ተከትሎ ያደረጉትን ንግግር እያዳመጥኩ ነበር። ” ራስን መሆን” አሉ ” ራስን መሆን እስክሞት የማልረሳው የአባቴ ውርስ ነው” ልብን በሃሴት የሚያስጋልብ ” የተፍተነ ” ንግግር። 

ይህ ብቻ አይደለም። የአግራችንን ፖለቲካ ” ሸር የተሞላበት፣ ክፋት የተሞላበት፣ በርካታ ንጽህ ኢትዮጵያዊያንን የበላ፣ ያመከነ መሆኑን ዛሬ ላይ ሆነን መታዘብ በምንችለው መጠን ሲናገሩ የንግግራቸው ቀለሃ አናት የሚበሳ ነበር። ራስን ባለመሆን ችግር ወንድም ወንድሙን በላ። ጓደኛ ጓደኛውን በላ። ዘመድ ዘመዱን በላ። እርስ በርስ ተበላላ። ራስን መሆን ባለመቻል ሁሉም “ተልዕኮ ” አስፈጻሚ ሆኖ የራሱን እጅ ቆርጦ ሲጥልና ነብስን ሲቀጭ … 

ይህ ቁልጭ ብሎ የሚታየን የፖለቲካ ባህላችን እንደሆነ ለማ ሲናገሩ ታዳሚዎቹ ለምን እንደሚያጨበጭቡ ባይገባኝም፣ የተነኩ ስለመኖራቸው ግን ጥርጥር የለውም። ” በመበላላት መኖር እርግማን ነው” ሲሉ ለለማ ጭብጨባ ያስፈለገበት ምክንያት ግራ ቢያጋባኝም / ቢቻል ደረት እየመቱ ማልቀስ እንጂ/ ታላቅ ዘር እንደዘሩ ምስክሮች ብዙ ናቸው።

በዚህ እርስ በርስ የመበላላት የሸፍጥ ፖለቲካችን እስከመቼ እንደምንዘልቅ ክቡር ለማ መገርሳ ለመገመት ያዳገታቸውና፣ ስጋት የገባቸው መስለውኛል። ከውራት በፊት ” ያገኝነውን ነጻነት መሸከም የምንችል አልመሰለኝም” ሲሉ ልብ ላላቸው ሰፊ ሃሳብ ያስተላለፉት አቶ ለማ፣ ዛሬም መስቀለኛ መንገድ ላይ ስለመገኘታችን አብስረዋል።

እርስ በርስ ሲያጨራርሰን የነበረውንና ተሸክመነው የኖርነውን የሸር ፖለቲካ ከመቅበር ይልቅ እሱን የመናፈቅና የተገኘውን ለውጥ አጥብቆ ያለመያዝ ችግር መኖሩን ጠቁመዋል። እሳቸው ባይሉትም መሳከር የሚታይበትን አካሄድ በጥሞና መርምሮ ወደፊት እንደመራመድ በደም ለመጨማለቅ የመረጡ፣ የታዘዙ ወይም የደነገጡ ፣ ወይም ለውጡ ያልገባቸው አካላት ጉዳይ ይመስለኛል መንገዱን መስቀለኛ ያደረገው።

ሌላው ምንም ይሁን ምን ይህንን ክፉ፣ የሸር መንገድ አሽቀንጥረን በመጣል በዚህ ትውልድ ታሪክ መስራት የሚያስችል ጅማሮ መኖሩ ትልቅ ተስፋ የመሆኑ ጉዳይ ነው። ይህንኑ ተስፋ ነው አቶ ለማ ተቃዋሚም ሆነ ተወዳዳሪ፣ ምህራንና ፖለቲከኞች እንዲሁም ሁሉም ዜጎች ተባብረው እንዲጠብቁት አደራ ያሉት።

በግል ለወረደላቸው ምስጋና ” እኔ ለዚህ አልመጥንም” ያሉት አቶ ለማ ” የሰራሁት ጥቂት ነገር የዜግነት ግዴታዬ ነው። ለዚህም ምስጋና አያስፈልገኝም። ጥቂቶች ከፊት ብንሆንም ዜጎች መስዋእት ሆነውበታል” ሲሉም ድሉ የህዝብ መሆኑንን አመላክተዋል።

ዛሬ የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ የሚደመጡ መሪዎች ተገኝተዋል። የተመረጡ ቀላል ቃላትን የሚናገሩ፣ ለህዝብ ክብር የሚሰጡ፣ አገራቸውን አጉልተው የሚያሳዩ፣ የተራውን ህዝብ ኑሮ ታች ወርደው የሚያዩ፣ የተረሱትን የሚያስታውሱ እኒህ መሪዎች እገዛ ሊደረግላቸው የሚገባውን ያህል ግን እየታገዙ አይመስልም። በጅምላ ጭብጨባና በጋጋታ የሚደረገው ድጋፍ ካልሰከነ የስካሩን አዋራ ስለማያበርደው ጥንቃቄ ያሻዋል። 

በጅምላ መንጫጫት፣ ድግስና ዝላይ ላይ ማተኮሩም ቢሆን ሊበቃ ይገባል። ለአገራቸው ባለውለታ የሆኑትን ማክበርና የሚገባቸውን ስፍራ መስጠት አግባብ ቢሆንም፣ መንገድ እየተዘጋ የኑሮ መስተጋብር የሚስተጓጎልበት አግባብ ግን ሊቆም ይገባል። ወይም መንገድ ሊዘጋና እንቅስቃሴ ሊስትጓጎል በማይችልበት መልኩ ቢሆን የተሻለ ይሆናል።

በአንድ ወቅት አንዲት ወላድን የጫነ አምቡላንስ ማለፊያ አጥቶ ከፍተኛ ችግር እንደተፈጠረ አስታውሳለሁ። እናም በየጊዜው መንገድ እየዘጉ መደነስ ገደብ ሊጣልበት የሚገባ ይመስለኛል። አለያም ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ይልቅ አቀባበሉን ወደ ሌላ ቦታ ማዘዋወር የሚቻልበትና እንግዶቹ እዛ ቦታ እንዲገኙ ማድርገ እንደ አንድ አማራጭ ቢታይ የሚል ሃሳብ አለኝ። ለምሳሌ ጃንሜዳ፣ ስታዲየም፣ መቻሬ ሚዳ… 

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ካቢኔዎቻቸውን ሲያሰለጥኑ ” እኛ በገባን በወጣን ቁጥር መንገድ የሚዘጋበት ምክንያት መላ ሊፈለግለት ይገባል” ማለታቸውን በሰማንበት አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ክልል ከተሞች ድረስ የሚደረገው መተራመስ ባልጠራው የሸፍጥ ፖለቲካ ውስጥ ሌላም ችግር ሊያስከትል ይችላልና መጠንቀቁ ክፋት የለውም። ሻሻመኔ የሆነው ይህ ነው። 

ራሳቸው ፖለቲከኞቹም ሆኑ ድርጅቶች ያልተንዛዛ፣ ቀላልና፣ ሰላማዊውን እንቅስቃሴ የማያውክ መርሃ ግብር ቢያዘጋጁና መንግስትን ቢያግዙት ተገቢና አንድ ልዩ አማርጫ ይሆናል። 

ከዚህ ሌላ ሳልገልጽ ማለፍ የማልፈልገው አንድ ታላቅ ጉዳይ ቢኖር፣ መሪ ቀንድ ነውና እንከተለው። አሁን በአንዳንድ ሚዲያዎች የሚታየው አካሄድ ፱፯ ዓ ም የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ ሚዲያዎች ከዘጋቢነት ስራቸው ወጥተው የመሪነት ሚና መጫወታቸው ምን ያህል ጉዳት እንዳደረሰ የምናውቅ እናውቃለንና ያ ታሪክ እንዳይደገም ማሳሰቡ አግባብ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። 

የሚዲያው መሪዎችም ሆኑ ባለቤቶች እዚህ ላይ ጥንቃቄ ካልወሰዱና ሚዲያ መሪ ሆኖ፣ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ተመሪ ከሆኑ፣ ያ- ኔ ድምሩ አስዛኝ ይሆናል። ስም መጥራት አስፈላጊ ባይሆንም በሁሉም አቅጣጫ በማህበራዊ ገጾች ከሚሰራጨው ቅስቀሳ በተጨማሪ የአንዳንድ ክልል ሚዲያዎችን ጨምሮ አቶ ለማ እንዳሉት የ”ሸር፣ የተንኮል” አካሄድ ይታይባቸዋል። ጉዳዩ ዞሮ ዞሮ ሁሉንም ስለሚጎዳ ስክኖ ማሰብ አስፈላጊ ይሆናል።

አለያ ግን ዛሬ ይቀበራል የተባለው የእርስ በእርስ መጨራረስ ፖለቲካ መዳፍ ላይ ተመልሶ ከመውደቅ ውጪ ሌላ ፋይዳ አያስገኝም። ኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ የምናፍርባቸውና ቅድሚያ ልንሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች ስላሉ እዛ ላይ ትኩረት ቢደረግ መልካም ነው። አቶ ለማ እንዳሉት ይህንነርግማን የሆነውን የመጠፋፋት ፖለቲካ በዚህ ትውልድ ለመቅበር!!

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ኢትዮጵያና የዓለም ባንክ የ200 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ተፈራረሙ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *