“Our true nationality is mankind.”H.G.

እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ

ADDIS ABABA, ETHIOPIA - MAY 24: A woman casts her vote for Ethiopian Parliamentary Election in Addis Ababa, Ethiopia, on May 24, 2015. (Photo by Minasse Wondimu Hailu/Anadolu Agency/Getty Images)

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ቀጣዩ ምርጫ በእውነተኛ ዴሞክራሲ ላይ ተመስርቶ የሚካሄድ እንደሚሆን በቅርቡ አረጋግጠዋል፡፡ የፖለቲካ ተንታኞችም እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን በማስገንዘብ ዋጋ የሚያስከፍልና መራራ ውጤትንም ሊያስጎነጭ እንደሚችል ይናገራሉ፡፡

የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሙሼ ሰሙ እንደሚሉት፤ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሲባል ነጻ፣ ፍትሃዊና ገለልተኛ የሆነ ማለት ነው፡፡ ከተለያዩ ጣልቃ ገብ ተቋማት ነጻ መሆን የግድ ነው፡፡ ለምሳሌ ከመንግሥት ተቋማት፣ ከደህንነት፣ ከፖሊስና ከመሳሰሉት ተቋማት ጣልቃ ገብነት ነጻ መሆን አለበት፡፡ የዴሞክራሲ ተቋማትም ገለልተኛ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ምርጫ እውነተኛ ስለመሆኑ ተዓማኒ መሆን ይጠበቅበታል፤ እንዲህም ሲባል ተዓማኒነት የሚመነጨው ነጻና ገለልተኛ ከሚባሉ ነገሮች ነው፡፡

ምርጫ ቦርድን ምርጫውን የሚያካሂደው ምርጫ ቦርድ ከፓርቲዎች ምዝገባ ጀምሮ በዕጩ ምልመላ፣በምርጫ ዘመቻ፣ ቆጠራ፣ ታዛቢዎችን በመመዝገብና ከምርጫው ጋር የሚያያዙትን በጥቅል የሚያስፈጽመው አካል መሆኑን ለአብነት በመጥቀስ፣ከማንኛውም ፓርቲም ሆነ መንግሥታዊ ተቋም እንዲሁም የውጭ አገር ተጽዕኖ ነጻ መሆን እንደሚጠበቅበት ያብራራሉ፡፡

እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ይካሄዳል ከተባለ በምርጫው የሚሳተፉ ፓርቲዎች የምርጫው አካል ለመሆንና ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ነው ብለው ለማመን መድረክ ማግኘት መቻል አለባቸው የሚሉት አቶ ሙሼ፣ዕጩ ተወዳዳሪዎቻቸውን ለመመልመል የሚያስችል ምቹ ሁኔታዎችም መኖር አለባቸው ይላሉ፡፡

በፓርቲዎቹ አባላት ላይ የሥራ ማፈናቀል አለማድረስ፣ እስር አለመፈጸም፣ በመንግሥት አማካይነት የሚያገኟቸውን ጥቅሞች ለምሳሌ በኑሮ ደረጃቸው ተደጓሚ የሚሆኑ የማኀበረሰብ አባላት ከሆኑ ከወረዳም ሆነ ከቀበሌ የሚያገኙትን ጥቅማቅሞች አለመከልከል እንደሚገባ ያመለክታሉ፡፡ በጥቅሉ አንድ ምርጫ ነጻ፣ ገለልተኛ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒነት ያለው ነው የሚያስበለው መስፈርት እነዚህ ናቸው ይላሉ፡፡

አቶ ሙሼ፣‹‹ገለልተኛ ሲባል ተቋማቱ ገለልተኛ መሆን አለባቸው ነው፡፡ ነጻ ነው ሲባል ደግሞ ከማንም ጣልቃ ገብነት ነጻ መሆን ሲችሉ ነው፡፡ የመገናኛ ብዙኃኑም ለሁሉም እኩል መሆን ይጠበቅባቸዋል›› ሲሉም ያብራራሉ፡፡

‹‹ከዚህ በፊት እንከን የለሽ ምርጫ ነው ሲባል ነበር፡፡ይህ ብዙም አሳማኝ አይደለም፤ ምክንያቱም የሰው ሥራ እንከን አያጣውም ››ያሉት አቶ ሙሼ ፣ እንከኑ ያልተገኘው ታስቦና ታቅዶ ነው ወይስ በሰዎች እውቀት ማነስ ነው? ችግር ሲኖር ለማረም ዝግጁነቱ አለ ወይ? ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡

ከምርጫው ዋና ዋና ዓላማዎች አንዱ ዜጎች የተለያዩ አማራጮችንና የፖለቲካ ፍልስፍናዎችን በማግኘት የተሻለ የሚሉትን የመምረጥ መብታቸውን ማክበር መሆኑን ጠቅሰው፣ሁለተኛው ደግሞ ይህንኑ አቋምና አስተሳሰብ ይዘው የመጡ ኃይሎች አማራጭ ሃሳባቸውን ለህዝቡ እንዲያቀርቡ መፍቀድና መብታቸውን ማክበር ነው ይላሉ፡፡ ‹‹የሰው ልጅ በአንድ ዓይነት አስተሳሰብ ውስጥ ሊካተት አይችልም፡፡ የተለያዩ አማራጮችን ይፈልጋል›› በማለት ይናገራሉ፡፡

ተንታኙ የህዝብን ሙሉ ጉልበት፣አቅምና ዝግጁነት መጠቀም የሚቻለው ይሁንታውን ሲሰጥ ብቻ መሆኑን ጠቅሰው፣ህዝብ ካልተባበረ የትም መድረስ እንደማይቻል ያመለክታሉ፡፡

‹‹ይችላሉ፤ያልተፈለገ ውጤት ሊመጣና እነዚህ ነገሮች መራራ ውጤት ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡›› የሚሉት ተንታኙ፣ ወደ ገዥው ፓርቲ ሲመጣ ምናልባት ወደ ስልጣን የተመጣው ከፍተኛ መስዋዕትነት ተከፍሎ ሊሆን ይችላል፤እውነተኛ ዴሞክራሲ ሲመጣ ግን ውጤቱ መራራ ሊሆን ይችላልና ለመቀበል ዝግጁ መሆንን ይጠይቃል፡፡›› ሲሉ ያስገነዝባሉ።

‹‹በትጥቅ ትግል፣ በአመጽ፣ በመፈንቅለ መንግሥትና በህገ ወጥ መንገድ ወደ ስልጣን የመጡ አካላት ሊሸነፉ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ኢህአዴግ ነጻ አወጣናችሁ ይላል፤ በትግል ወቅት ከፍተኛ መስዋዕትነትም እንደከፈለ በየአጋጣሚው በመናገር ለዚህም እኔ መምራት አለብኝ ብሎ ያምናል፡፡ ሁሌ በካሳ መልክ ስልጣኑን ይዞ መኖር ይፈልጋል፡፡››ያሉት አቶ ሙሼ፣ ከዚህ በኋላ ግን አገሪቱን ወደተሻለ ደረጃ የሚያደርሳት እገሌ ነው፤ እገሊት ናት የሚል ህዝብ ሊኖር እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡

‹‹ይህ ማለት መራራ ዋጋ ያስከፍላል ማለት ነው›› ሲሉም ያስገነዝባሉ፡፡ ስለዚህ ነጻ ማለት ሰዎች አማራጫቸውን እንዲወስዱ መፍቀድ ነው፤ ይህን ማድረግ ግን ብዙ ጊዜ ሲተናነቅ ይስተዋላል ይላሉ፡፡

ተንታኙ አቶ ሙሼ እንደሚናገሩት፤ቀጣዩን ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ ስልጣን ላይ ያለው አካል ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ ምርጫውን ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ለመንግሥትም ይጠቅማል፡፡ ዕድሜ ልክ የህዝብ አመጽና ቁጣ ሰው በመግደል፣ በማሰርና በማስፈራራት ሊፈታ አይችልም፤ታጥቆና እንቅልፍ አጥቶ ከሚያድር ምርጫውን ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊና ገለልተኛ ቢያደርግ በሰላም እንቅልፍ ተኝቶ ሊያድር ይችላል፤መድፍ፣ በመትረየስና በታንክ ተጠብቆ ከሚኖር ከህዝብ ጋር ታርቆ ውጤቱን ተቀብሎ በሰላም መኖሩ ይመረጣል፡፡ ከተሸነፈም ለቀጣዩ ምርጫ ተዘጋጅቶ መቅረብ ይሻላል፡፡

የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ግደይ ደገፉ እውነተኛ ዴሞክራሲ አንጻራዊ ነው ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ ለአብነትም ሲጠቅሱ፤ከሊበራል፣ ከሶሻሊስት አሊያም ከኮሚኒስት አኳያ ዴሞክራሲ ሲታይ የየራሳቸው መርሆዎችና እሴቶች እንዳላቸው ያመለክታሉ ፡፡

እንደ እርሳቸው አነጋገር፤ በነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ከምዝገባ ጀምሮ የምርጫው ውጤት ይፋ እስከሚሆን ድረስ ያለው ሂደት ነጻ፣ ፍትሃዊ እና መራጮች በነጻነት የመመረጥ መብታቸው የተጠበቀበት መሆን አለበት፡፡ ውጤቱ ከተገለጸ በኋላም አሸናፊም ሆነ ተሸናፊ በነጻነት ውጤታቸውን መቀበል መቻል አለባቸው፡፡ እዚህ ላይ ውጤቱ መራራ ሊሆንም ይችላል በማለት የአቶ ሙሼን ሃሳብ ያጠናክራሉ፡፡

‹‹የምርጫ ነጻነት ማለት መራጮች ከመመዝገብ ጀምሮ እስከ ምርጫ ቀን ያለው ሂደት ሰላማዊ የሚሆንበት ነው›› የሚሉት አቶ ግደይ፣መራጩም ሆነ ተመራጩ ማስፈራሪያና ዛቻ የሚደርስባቸው ከሆነ በተለይ ደግሞ መራጩ ከሥራ የሚባረር፣ እከሌን ካልመረጥክ ጉድህ ፈላ የሚባል ከሆነ፣ መገናኛ ብዙኃን ፍትሃዊ ካልሆኑ ምርጫው ፍትሃዊ አልሆነም ማለት ነው›› ሲሉም ያብራራሉ፡፡

ተንታኞቹ እንደሚሉት፤በአፍሪካ ምርጫ ሙሉ ለሙሉ ዴሞክራሲያዊ አይደለም ማለት አይቻልም፤ለምሳሌ በኬንያ የቅርቡን ማስታወስ ከተፈለገ የምርጫውን ውጤት እስከማስለወጥ መድረስ ተችሏል፡፡ ጋና፣ ናሚቢያና ቦትስዋና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማካሄድ የሚያደርጉት ጥረት በአፍሪካ ደረጃ የተሻለ ነው፡፡

የይስሙላ ዴሞክራሲ ከሚያካሂዱት አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን ጠቅሰው፣ ‹‹በአገሪቱ ውስጥ እንከን የለሽ ምርጫ ቀርቶ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ራሱ አልተካሄደም፡፡እንከን የለሽ ሲጀመር በሰው አዕምሮ የማይቻል መለኮታዊ ነገር ነው›› ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡ ምርጫውን ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ በህዝቡ ዘንድ ተዓማኒነትን ማትረፍ ያልቻለው የምርጫ ቦርድ መስተካከል አለበት ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያ ከ1983 ወዲህ ብቻ አምስት ጊዜ ምርጫ ማካሄዷ ይታወቃል፡፡ምርጫዎቹም ነጻ፣ዴሞክራሲያዊ፣ፍትሃዊ እና ተአማኒ መባላቸውም ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ በተያያዘችው አዲስ የለውጥ ጎዳና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እየተሰራ ሲሆን፣በሀገሪቱ «እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ›› እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡ ምርጫ ቦርድ ፣ የፍትህ ተቋማት፣ መገናኛ ብዙሃን እና ተመሳሳይ ተቋማት ይህን ምርጫ ለማስተናገድ የሚችል ቁመና ኢንዲላበሱ ማድረግም በመንግሥት በኩል ይጠበቃል፡፡ 
የፖለቲካ ፓርቲዎች ለእውነተኛው ዴሞክ ራሲያዊ ምርጫ ከወዲሁ ራሳቸውን በማዘ ጋጀት ይህ ዕድል እንዳያመልጥ በትኩረት መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

መንግሥትም ተፎካካሪ ፓርቲዎቹን ለውጡን በመጠበቅና በማስቀጠል ያለፈውን የምርጫ ታሪክ መቀየር ይኖርባቸዋል፡፡

አዲስ ዘመን ጋዜጣ ነሐሴ 29 ቀን 2010 ዓም
በአስቴር ኤልያስ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ኤፒ ለቅጥፈቱ ይቅርታ አልጠየቀም – ምርጫ ተራዘመ፤ለምን?
0Shares
0