“Our true nationality is mankind.”H.G.

ቻይና – አፍሪካ ትብብር በቁጥር

የቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም በትናንትናው ዕለት በሚኒስትሮች ደረጃ ተካሂዷል። ከዛ ጎን ለጎንም የየሃገራት መሪዎች በተናጥል የተለያዩ ውይይቶችን አድርገው፥ ዛሬ በመሪዎች ደረጃ ተጀምሯል።

ቻይና እና አፍሪካ ባለፉት ሶስት አመታት በርካታ ስራዎችን የሰሩ ሲሆን፥ በዚህም የቻይና – አፍሪካን ግንኙነት ማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

ቻይናም ከአፍሪካ ጋር በሚኖራት ትብብር፥ የጋራ፣ ጠንካራና ጥብቅ፣ የአረንጓዴ ልማት ተኮር፣ አስተማማኝ እና ለሁሉም ክፍት የሆነ ልማትን ታሳቢ አድርጋ እንደምትሰራ የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ በ7ኛው የቻይና አፍሪካ የሚኒስትሮች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር በጆሃንስበርግ የፎካክ ጉባኤ የተደረሰው የመግባቢያ ስምምነት ትልቅ ውጤት ማስገኘቱንም አንስተዋል።

በወቅቱ የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ የቻይና አፍሪካ ግንኙነት አካታች ወደሆነ ስትራቴጂካዊ የትብብር አጋርነት ማደጉን መግለጻቸው ይታወሳል።

ከዚያን ጊዜ ወዲህም በቻይና እና በአፍሪካ ሃገራት መካከል በርካታ ስምምነቶች ተደርሰው ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸው ይነገራል።

ፕሬዚዳንቱ የአፍሪካ ሃገራት መሪዎችም በፖለቲካዊ መስክ እኩልነትን ማረጋገጥና የጋራ መተማመንን መፍጠር፣ የኢኮኖሚ ትብብሩን በጋራ ተጠቃሚነት ላይ መመስረት፣ የባህል ልውውጥን ማጎልበት፣ በፀጥታና ደህንነት መደጋገፍ እንዲሁም በዓለም አቀፉ የፖለቲካ መድረክ አንድነትና ትብብርን ሊተገብሩ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከዚህ ባለፈም ዢ ከሃገራት መሪዎች ጋር በኢንደስትሪያላይዜሽን፣ ግብርናን በማዘመን፣ በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ በፋይናንስ አገልግሎት፣ በአረንጓዴ ልማት፣ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በድህነት ቅነሳና ማህበረሰብ ደህንነት፣ በማህበረሰብ ጤና፣ በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ እንዲሁም በፀጥታና ደህንነት ዙሪያ በጋራ መስራት በሚቻልበት አግባብ ላይም ስምምነት ደርሰዋል።

የጆሃንስበርጉ የፎካክ ስምምነት ከተደረሰ ሶስት አመታት አልፈውታል፤ ከዚህ አንጻር የቻይና አፍሪካ ግንኙነት አጠቃላይ ገጽታም በቁጥሮች ይገለጻል።

በፖለቲካዊ መስክ፦ 27 የቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲ መሪዎችና ግዛት አስተዳዳሪዎች አፍሪካን ጎብኝተዋል፣ በአፍሪካ በኩል ደግሞ 30 የየሃገራት መሪዎችና ከፍተኛ ባለስልጣናት በቻይና ጉብኝት አድርገዋል።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደግሞ ስምንት ጊዜ ወደ አፍሪካ ጉዞ አድርገው 22 የአፍሪካ ሃገራትን ሲጎበኙ፥ በአንጻሩ 33 የአፍሪካ ሃገራት መሪዎችን በቻይና ተቀብለዋል።

53 የአፍሪካ ሃገራት ደግሞ ከቤጂንግ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አላቸው።

በኢኮኖሚው መስክ፦ በቻይና የተጀመረው ዋን ቤልት ዋን ሮድ ማዕቀፍ በርካታ ውጤቶች የተገኙበት ሲሆን፥ ናይሮቢን ከሞምባሳ በባቡር መስመር በማገናኘት የጉዞ ሰዓቱን በግማሽ በመቀነስ ለ46 ሺህ ሰዎች የስራ እድል ፈጥሯል።

ከዚህ ባለፈም ፕሬዚዳንት ዥ በፎካክ ጉባኤ ላይ ከአፍሪካ ሃገራት ጋር የደረሷቸው 10 የትብብር ስምምነቶች በጥሩ መንገድ እየተጓዙ ነው።

በባህል ልውውጥ ዘርፍ፦ ቻይና ለ180 ሺህ አፍሪካውያን በተለያዩ ሃገራት ስልጠና ሰጥታለች።

የቻይናዊው የፍልስፍና ሊቅ ኮንፊሺየስ አስተምህሮ የሚዘከርባቸው 55 የፍልስፍና ተቋማት እና 30 ማስተማሪያ ክፍሎችም በተለያዩ 42 የአፍሪካ ሃገራት እንዲቋቋሙ ተደርጓል።

የቻይና ብሄራዊ ቋንቋ የሆነው ማንዳሪን ቋንቋ በ11 የአፍሪካ ሃገራት በስርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተት ሆኗል።

በቻይናና አፍሪካ ሃገራት መካከል 133 እህትማማች ከተሞች ሲመሰረቱ፥ 30 የአፍሪካ ሃገራት ደግሞ በቻይናውያን ጎብኝዎች የተመረጡ መዳረሻዎች ሆነዋል።

በፀጥታና ደህንነት፦ በፈረንጆቹ 2017 የቻይና ባህር ሃይል ሆስፒታል መርከብ በሰባት የአፍሪካ ሃገራት ጉብኝት በማድረግ ለዜጎች ነጻ የህክምና አገልግሎት አዳርሷል።

2 ሺህ የቻይና ሰላም አስከባሪ ወታደሮች በአምስት የአፍሪካ ሀገራት ሲሰማሩ፥ ከ6 ሺህ በላይ የቻይናና የሌሎች ሃገራትን የጦር መርከቦች ያካተተ የባህር ሃይል ወደ ኤደን ባህረ ሰላጤና በሶማሊያ የባህር ክልል ተልኳል።

በአለም አቀፉ መድረክ የፖለቲካ መስክ፦ ቻይና እና አፍሪካ በአለም አቀፉ የፖለቲካ መድረክ በፀጥታና ደህንነት፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በደቡብ ደቡብ ትብብር በቅርበት መስራት ችለዋል።

ከዚህ ባለፈም በፖለቲካው መድረክ የሚኖር የበላይነትንና አግላይ አካሄድን እንዲሁም በኢኮኖሚው መስክ ከፍተኛ ቀረጥ በመጣል ምርቶችን እንዳይገቡ የማድረግ አካሄድን በአንድ ድምጽ ተቃውመዋል።

ሁለቱም አካላት በመንግስታቱ ድርጅት ስር በሚገኙ ተቋማት በተካሄዱና እንደ አለም ጤና ድርጅትና የተመድ የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ማዕከል (ዩኔስኮ) በተደረጉ ምርጫዎች አንዳቸው ለአንዳቸው ድጋፍ አድርገዋል።

ምንጭ፦ ሲ ጂ ቲ ኤን FBC

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ
0Shares
0