የሁሉም ኢትዮጵያዊ ምኞት እኩልነት፣ ወንድማማችነት እና ነፃነት የሰፈነባት ዴሞክራሲያዊት ሀገር እዉን ሆና ማየት ነዉ። ለዚህ ቅዱስ አላማም በርካታ ኢትዮጵያዉያን ብሄር፣ ሃይማኖት፣ ፆታና የፖለቲካ አመለካከት ሳይለያቸዉ ዉድ የሆነ መስዋዕትነት ከፍለዋል። በተከፈለዉ መስዋዕትነትም ዛሬ የነፃነት ጮራ በሀገራችን መፈንጠቅ ጀምራለች።

በተለይም ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ አመራርነት ከመጡ ጊዜ አንስቶ የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ሁሉም የፖለቲካ ሀሳብ ልዩነቶች ያለምንም ገደብ በሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ አግባብ እንዲንፀባረቁ፣ አፋኝ የሆኑ ህጎች እንዲስተካከሉ፣ በእስር የነበሩ የፖለቲካ ድርጅት አመራሮች እና ፖለቲከኞች እንዲፈቱ፣ ትናንት በነበረዉ ችግር የትጥቅ ትግል ለማድረግ ተገደዉ የነበሩ ወንድም እና እህቶቻችንም በሰላም ወደ ሀገራቸዉ ተመልሰዉ በሀገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የበኩላቸዉን ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ በመደረግ ላይ ይገኛል። ይህ ሂደት ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያስደሰተ ወደ ዲሞክራሲ እና ነፃነት የምናደርገዉን ሽግግር ከማፋጠን አኳያ ጉልህ ሚና እንደሚኖረዉም አያጠያይቅም።

በድምሩ ሲታይ የሀገራችን ፖለቲካ ወደ ጠንካራ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሽግግር ላይ ናት ብሎ መዉሰድ ይቻላል። የሽግግር ወቅት ፖለቲካ ደግሞ በዉጣዉረዶች የተሞላ በመሆኑ በትልቅ ማስተዋል እና ትዕግስት እንዲሁም በጥበብ መሻገርን ይጠይቃል። ነገሮች ወደ ተፈለገዉ ግብ በፍጥነት እንዲሄዱ ሁሉም ተደጋግፎ የልዩነት ነጥቦቹን በይደር አቆይቶ አንድ የሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ አትኩሮ ካልተረባረበ የሽግግር ዘመኑ ከሚገመተዉ በላይ ሊረዝም ይችላል። በጥቃቅን የልዩነት ነጥቦች ላይ ንትርክ እና ግጭት ከተጀመረ ለነፃነት ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር የተደረገዉ ትግል ወደ ስርዓት አለበኝነት እና ሀገርን ወደ ማፍረስ ሊያመራ ይችላል።

ሁሉም ሰዉ ነፃነትን ይመኛል። ሁሉም ሰዉ ኢትዮጵያ ሰላም እንድትሆን ዴሞክራሲ የሰፈነባት፣ ዜጎች በእኩልነት የተሻለ ኑሮ የሚኖሩባት ሀገር እንድትሆን ታግሏል። ትግሉም ፍሬ ማፍራት ጀምሯል። የትግሉ ፍሬ ጎምርቶ እንዲበላ ግን አሁንም ቀሪ የቤት ስራዎች አሉብን። መታረም እና መስተካከል ያለባቸዉ ጉዳዮች ብዙ ናቸዉ።

እዉነተኛ ነፃነት ማለት ስርዓት አልበኝነት ማለት አይደለም። እዉነተኛ ነፃነት የህግ የበላይነትን በማክበር፣ የማይወዱትን ቢሆን የሌላን ሀሳብ በማክበር ዉስጥ ይገኛል። ስርዓት አለበኝነት ፍፁም ባርነት ነዉ! ዴሞክራሲ ማለት የማንቀበለዉ እንኳ ቢሆን የሌሎችን ሀሳብ ማክበር፣ ሀሳብን በሀሳብ ብቻ ለማሸነፍ መጣር ነዉ። ከዚህ ባለፈ በሃሳብ ልዩነት ወይም በባንዲራ እና በአርማ ልዩነት ስሜታዊ ሆነን ለንትርክ እና ፀብ የምንጋበዝ ከሆነ ትከሻችን ዴሞክራሲን ለመሸከም ብቁ አልሆነም ማለት ነዉ። በዴሞክራሲና ነፃነት ጥማት ታግለን መስዋዕትነትን ከፍለን ስናበቃ የአርማ እና የባንዲራ ልዩነቶችን ለማስተናገድ ዝግጁ አለመሆን፣ ልዩነቶችን በሰከነ ዉይይት ከመፍታት ይልቅ ለፀብ የምንጋበዝ እና በስሜት የምንጋልብ ከሆነ ዴሞክራሲን ለማረጋገጥ የፈለገዉን ያህል ምቹ ሁኔታ ቢኖር ዴሞክራሲን ማምጣት ከባድ ይሆናል። ነፃነት እና እዉነተኛ ዴሞክራሲ ሊሸከማችዉ ዝግጁ የሆነ የህዝብ ትከሻ ይሻሉ። ነፃነት እና ዴሞክራሲ በሽግግር ፖለቲካ ዉስጥ እንደ እንቁላል ናቸው። በግልብ ስሜታዊነት፣ ልዩነትን ማስተናገድ ባለመቻል በሚፈጠሩ ንትርኮች በቀላሉ ለመጠገን በማይቻል ደረጃ ሊሰበሩ ይችላሉ። ስለሆነም ለዴሞክራሲ እና ለነፃነት የከፈልነዉን ዋጋ እያሰብን አስፈላጊዉን ጥንቃቄ ማድረግ ግድ ይላል። ካልሆነ ግን ስሜታዊነት ከሚፈጥረዉ ልዩነት፣ ንትርክ እና ከመገዳደል ጥቅም እና የፖለቲካ ትርፍ የለመዱ ወንድማማች ህዝቦችን እሳት እና ጭድ አድርገዉ የሚስሉ ህዝቦች መካከል ምንም የግጭት ሳይፈጠር ግጭት የተፈጠረ አስመስለዉ እያሟሟቁ ነዉ። አሁን ባለንበት የትግል ምዕራፍ ነቅተን አንድነታችንን ካልጠበቅን በተፈጠረ አጋጣሚ ሁሉ የግጭት እሳት ለኩሰዉ እሳቱን የሚሞቁ የግጭት ነጋዴዎች ሲሳይ መሆናችን አይቀርሬ ይሆናል።

በመጨረሻም ወደ ሰሞነኛዉ የባንዲራ እና የአርማ ዉዝግብ ስመለስ ማንኛዉም ግለሰብ ከሀገር ዉጭ ለሚገቡ የፖለቲካ ድርጅቶች የፈለገዉን አርማ እና ባንዲራ ይዞ አቀባበል የማድረግ መብት አለዉ። በነገዉ ዕለት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር አመራሮች ወደ ሀገራችዉ ሲመለሱም የድርጅቱ ደጋፊዎች እና አድናቂዎች የድርጅቱን አርማ እና ባንዲራ ይዘዉ እንደሚወጡ ይጠበቃል። ከድርጅቱ አርማና ባንዲራ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያ ሪፐብሊክ ባንዲራ እና የክልል መንግስታት ባንዲራዎች በስፋት እንደሚያዙ እየሰማን ነዉ። ይህ አካሄድ የሚደነቅ እና ብስለት የተሞላዉ አካሄድ ነዉ። በነገዉ የአቀባበል ስርዓት ተሳታፊዎች በህብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓቱ ላይ እና ሁሉም የኢትዮጵያ ወንድም ህዝቦች ጋር በወንድማማችነትና በእኩልነት ለመኖር ያላቸዉን ፅኑ ፍላጎት ያሳያል።

ቸር እንሰንብት! – 

Addisu Arega Kitessa

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   “ጣልያኖችም ሆኑ እንግሊዞች ቅኝ ግዛትን ለማስቀጠል ህዝቡን በዘር መከፋፈልን እንደ አንድ ስልት ይጠቀሙ ነበር” -አቶ ታቦር ገረሱ ዱኪ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *