ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

‹‹ሕዝቡ የፈለገውን ባንዲራና አርማ በመያዝ መደገፍ የዲሞክራሲ ምህዳሩ መስፋት ውጤት ነው›› አቶ ለማ መገርሳ

‹‹ማንም የፈለገውን ባንዲራና አርማ በመያዝ ድጋፍ መውጣት የዲሞክራሲያዊ ምህዳሩ መስፋት ውጤት መሆኑን በመገንዘብ በዚህ ምክንያት የሚነሳ ግጭት መቆም አለበት›› ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ አሳሰቡ፡፡
አቶ ለማ መገርሳ በአዲስ አበባ ባንዲራን ምክንያት አድርጎ የተከሰተውን ግጭት አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ በሀገሪቱ ለብዙ ዓመታት ሠፍኖ የቆየውን አፈና እና ግድያ ለማስቀረት፣ የዲሞክራሲ ምህዳሩ እንዲሰፋ ብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሀገር እየገቡ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
የዲሞክራሲ ምህዳር መስፋት የሚለካው ደግሞ ‹‹በመቻቻል፣በመደማመጥ እና በመተጋገዝ ነው፡፡ይህ ሲሆን አንዱ በሌላው ላይ ከመጫን አሠራር እንወጣለን›› ብለዋል፡፡
‹‹ማንም የራሱን ባንዲራና አርማ ይዞ ወደ አደባባይ ቢወጣ ወንጀል አይደለም፤ አንዱን ለመግፋት የአንዱን ደግሞ ለማንሳት አልታገልንም፡፡ ሁሉም በእኩልነት ነው መታየት ያለበት›› ብለዋል አቶ ለማ መገርሳ፡፡
‹‹የሰዎችን መብት እስካልጣሰ ድረስ ተመቸንም አልተመቸንም ማንም ቡድን የራሱን ባንዲራ ይዞ ሲወጣ መብቱን ማክበር አለብን›› ብለዋል
‹‹ሰላምና ዕድገት ለማምጣት የምንሠራው ሥራ ወደ ኋላ ሊመልሰን አይገባም፡፡ለሀገሪቱ የሚሆን ባንዲራ የሚወሰነው በሕዝቦች ፍላጎት እና ፈቃድ እንጂ ቡድንን በመጫን አይደለም›› ነው ያሉት፡፡
በአንድነት የምንኖርበት ስርዓት ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ-መስተዳደር ለማ ‹‹ሁሉም ሕዝብ መታገስ አለበት፡፡ የኦሮሞን ባንዲራ መምረጥ የሚችለው ኦሮሞ ነው፡፡ ኦሮሞ ይዞ የወጣውን ባንዲራ መጥላትና መግፋት የማንም መብት አይደለም፤ ኦሮሞም ባንዲራውን ሌላ ብሔር ላይ መጫን አይችልም፡፡›› ብለዋል
‹‹በባንዲራ ምክንያት አላስፈላጊ እልህ ውስጥ ገበተን ይህን እድል ተጠቅሞ እኛን ወደኋላ ለመመለስ ለሚፈልግ ቡድን መንገድ መክፈት የለብንም›› ብለዋል፡፡
‹‹ይህን ጉዳይ የሚመሩ የፖለቲካ ድርጅቶችና ወጣቶች ኃላፊነት መውሰድ አለባቸው፡፡ መብታችን ሲገፋ መጠየቅ ያለብን በሕግ ነው›› ያሉት ፕሬዝዳንት ለማ ‹‹የምናከናውነው ተግባር ከስሜት የፀዳ መሆን አለበት›› ብለዋል፡፡
ጋዲሳ አብዳና

Related stories   ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ መግለጫ