“Our true nationality is mankind.”H.G.

“የኦሮሞ ወጣት ስማኝ – እኔን የሰሩ እነሱ ናቸው” አብረሃም ወልዴ (ባላገሩ)

ተወልጄ ያደኩት ሰላሌ አውራጃ ፍቼ ከተማ ውስጥ ነው:: እኔ የተሰራሁት በደገኞቹ ደግ ኦሮሞዎች በቆለኞቹ ብልህ አማሮችና በወይናደጋው ስብጥር የፍቅር ማህበረሰብ ጥበብ ነው:: እኔን የሰሩ እነሱ ናቸው:: ኦሮሞ ሲነካ ያመኛል:: ኦሮሞ ሲታማ ይሰማኛል:: የትኛውም የፍቼ ልጅ የኔን ሃሳብ ይጋራል:: ምክንያቱም እኛ እንደ አንድ ቤት ልጆች ነው ያደግነው::

ኦሮሞ ፍቅር ነው:: ኦሮሞ ፍፁም ኢትዮጵያዊ ነው:: በእርግጥ እንደ ኦሮሞ የተበደለ ህዝብ ያለ አይመስለኝም:: የኦሮሞ ህዝብ የማይገባውንም መከራ ያልዘራውንም ያጨደ ህዝብ ነው:: ስርዓቶች በድለውታል::

አየለ፣ በቀለ፣ አበበ፣ ከበደ፣ እሸቱ፣ ተሰማ፣ ግርማ፣ ስሜ እና ታደሰ…. እነዚህ የስም ስያሜዎች በይበልጥ የኦሮሞ የሆኑበትን ታሪክ ብቻ ማወቅ በቂ ነው:: ነገር ግን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ አገዛዞቹን ሁሉ ሲታገል የኖረው ከዚህ አይነቱ የጭቆና ደዌ ለመላቀቅ መሆኑን የኦሮሞው ማህበረሰብ ያውቃል ብዬ አምናለሁ:: ከዚህ ወዲያ የኦሮሞን ችግርንም በደልንም ማየት አንፈልግም:: ምንም እንኩዋን በጥቂቶች ጥፋት ሁሉም መወቀስ ባይሆንም ቀሪው ክፍል ኦሮሞን ሲያመሰግን የኦሮሞን ጨዋነት ሲሰብክ ባህልና ቁዋንቁዋውን ሲያጠናና ለጋብቻ ዝምድና ደጅ ሲጠናው እንጂ እንደ ሃገር አፍራሽ እያየው ስጋት ሲሆነው ከማይ ብሞት ይሻለኛል::

ዛሬ በርካሽ ጥቅም የተደለሉ ግለሰቦች በድረ- ገፅ ፅሁፎቻቸው ተቆርቆሪ መስለው የኦሮሞን ወጣት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እያሸከሙ ለቁጣ የሚያነሳሱት ሰይጣን ስለሆኑና ደም ስለሚጠማቸው ብቻ ነው:: የኦሮሞ ወጣት ስማኝ… እኔ በጣም ከሚወዳችሁ ስታነቡ ከሚያነቡት ውስጥ አንዱ ነኝ:: ከዚህ በህዋላ ግጭት ከዚህ በህዋላ ጥል ለእናንተ አይገባም:: እናንተ ከዚህ በህዋላ እየተመሰገናችሁ እየተመረቃችሁ ባህላችሁን ፍቅራችሁን ጥበባችሁን ቁዋንቁዋችሁን የምታሳዩበትና የምታስተምሩበት ግዜያችሁ ነው:: በትንሽ ነገር እልህ አትያያዙ:: አነካኪዎችን ብለጥዋቸው:: ዘመኑን ሊቀምዋችሁ ከሚልከሰከሱ ውሾች ተጠበቁ:: ከፍ በሉ እንጂ ዝቅ እንዳትሉ::

ከፍፁም ፍቅርና ከፍፁም ተቆርቁዋሪነት የመነጨ ምክሬን ስሙ:: የምትወዱትን ባንዲራ ከፍ አርጉት እንጂ ዝቅ አታድርጉት:: ነገር ሲቆይ ተረት ነው የሚሆነው:: እንዴት ሰው በተረት ይጣላል?:: የኦሮሞና የአማራ ወጣቶች ማህበር ከሲዳማና ከወላይታ ወጣቶች ማህበር ጋር የሃረሪና የኦሮምያ ወጣቶች ማህበር ከሶማሌና ከአፋር ወጣቶች ማህበር ጋር በመተባበር ስለተሰራ የበጎ ስራ ዜና መስማት እንጂ መርዶማ የሰለቸን ነገር ነው:: ያውም በዚህ ዘመን?! እኔ የማውቀውን ውድ ማንነታችሁን ሌላውም እንዲያውቀው እመኛለሁ:: የውስጣችሁን አውጡት:: ስለማቃችሁ ነው:: እዛ ውስጥ ደግነትና ፍቅር ሞልትዋል:: አውጡት!!!

source –Inዐበይት ጉዳዮች

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0