“Our true nationality is mankind.”H.G.

“መንግስት ጡት ካለው ያጥባን”


ቆየት ያለች የተስፋዬ ካሳ ቀልድ ነች። እኔ እንኳ አልሰማዃትም ነግረውኝ ነው። በነገሩኝ ላይ ደግሞ ጨማምሬባት…  ህፃናት ተሰብስበው ፣ ተደራጅተው ፣ የተቃውሞ ሰልፍ ወጥተዋል … ኢቲቪ በር ላይ ይሆን የሄዱት ? አላውቅም። ከላይ ፒንክ ፣በመሐል ነጭ፣ ከታች ሰማያዊ ፣የመሐሉ ነጭ መደብ ላይ የወርቃማ ጡጦ ምልክት ያለበት ባንዲራም ይዘው ይሆናል … ትርጓሜውም ፒንኩ ሴት ህፃናትን፣ ሰማያዊው ደግሞ ወንድ ህፃናትን፣ መካከል ላይ ያለው ነጩ ምግባቸው ወተትን ወይም መፀዳጃቸው ዳይፐርን ጡጦው ደግሞ ያው ጦጧቸውን ይወክላሉ ። ጥያቄአቸውም በአጭሩ “እናቶቻችን ወደስራ በሚሄዱበት ጊዜ ሞግዚቶቻችን ጡጧችንን እየጠቡብን ፤ ምግባችንን ሴሪፋምና ሴሪላክ እየበሉብን ስለሆነ ተራብን። በዚህም ሳቢያ በምግብ እጥረት ለሚመጣ በሽታ ተጋልጠናል። ይኸም የአንድ ትውልድ የማኮሰስ የማቀጨጭና ብሎም የማጥፋት ስራ ስለሆነ ሊቆም ይገባል።” ነው።
“ይገባል!”
“ይገባል!”
ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው አካል የሴቶች እና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ መጥቶ አነጋገራቸው …
“ልጆች ጥያቄአችሁን ሰምተናል፣ችግራችሁን ተረድተናል። አትንጫጩ (ልጆቹኮ አልተንጫጩም እንዲሁ ህፃን ሲያይ ጆሮው ላይ የሚጮህበት አይነት ሰው ሆኖ ነው) በወኪላችሁ በኩል ጥያቄአችሁን አቅርቡ ምን እንዲደረግላችሁ ነው የምትፈልጉት?” ሲል… የ6 ወሩ ማርኮናል ዳዴ እያለ ወደፊት ቀረበና…(አዲስ አበባ ውስጥ ከሶስት ወንድ ህፃናት የሁለቱ ስም ማርኮናል ነው ብዬ በመገመት)
“እኛ ሌላ ምንም አንጠይቅም ብቻ እናቶቻችን ስራ በሚሄዱበት ወቅት መንግስት ጡት ካለው ያጥባን!”
“ያጥባን!”
“ያጥባን!”
ኃላፊው የጥያቄውን ተገቢነት ተገንዝቦ የሚከተለውን ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያ አወጣ
የስራ መደቡ መጠሪያ :- ጡት ማጥባት
ፆታ:- ሴት
የወሊድ ሁኔታ:- ከወለደች 6ወር ያላለፋት
.
.
.
ከእነዚህ ህፃናት ያልተለየ ሐሳብና ድርጊት ያላቸው “አዋቂዎች” በየቀበሌው ጠዋት ጠዋት “ጥያቄአቸውን” ይዘው እየተሰለፉ ነው። የሰልፉ ተቃዋሚ ደግሞ ከሰአት በኋላ ይሰለፋል። ለምሳሌ የማንትስ ወረዳ በሙቀጫ መውቀጥ እና በድንጋይ ወፍጮ የመፍጨት ቀን በተከበረበት ቀን ላይ በተነሳ ግጭት በተወረወረ ዘነዘና አምስት ሰዎች ሲፈነከቱ … ይሄንን ያክሉ ደሞ በመጅ ተፈጭተዋል። የግጭቱ መንስኤ “የተቀረው አለም በኤሌክትሪክ እየፈጨ፤ በማሽን እየወቀጠ እኛ ኋላቀር የእጅ መሳሪያዎችን አናበረታታም” ያሉ ከተማ ቀመስ የአካባቢው ተወላጆች የበዓሉን መከበር በመቃወማቸው ነበር። 


gonfa.jpg.
ትናንት እንደ እኔ ሰሜን አዲስአበባ የተገኘ ሰው ከተሜ ቀመስ ሰው ባህላዊ የመስሪያ ቁሳቁሶችን እንጂ ባህላዊ የጦርነት ቁሳቁሶችን ከመጠቀም ወደኋላ እንደማይል ነው። ቆጮ መፈቅፈቂያ ገጀራ፣ መሬት መኮትኮቻ ፣ የስጋቤ አጥንት መከትከቻ መጥረቢያ(ስጋ የማልበላው በምክንያት ነው) የመሳሰሉ የልማት መሳሪያዎችን ይዘው መሐል ጎዳና ላይ የሚንጎራደዱ ‘ልማታዊ’ ሰዎችን አይቻለሁ። እንግዳ በመጣ ቁጥር እየተንገዳገድን…
በነፃነት ስም መረንነት
በአንድነት ስም አንድአይነትነት
በመደመር ስም መከመር
በእኩልነት ስም እኩያነት
እዚህም እዚያም ተንሰራፍቷል ።ከስጋት ወደሌላ ስጋት ከግጭት ወደግጭት ስንንከባለል አለን። ደጉን ቀን ያምጣልን!ልቦና ይስጠን!
.
በቀጣይ “ከባንዲራች ላይ ፈረንጅ የሰራው ጡጦ ስለማይወክለን የጡጦው ምልክት ተነስቶ ተፈጥሮአዊው የእናቶቻችን ሁለት ጡት ይደረግልን” ያሉ ህፃናት ያነሱትን ተቃውሞ እነግራችኋለሁ። በርግጥ አባቶቻቸውም ደግፈዋቸዋል።

Teym Tsigereda Gonfa

ፎቶ ዝግጅት ክፍሉ የመፈናከቻ ቁሳቁስ ለማሳየት ብቻ ታስቦ የተደረገና ከጸሃፊዋ ሃሳብ ጋር የማይዛመድ

0Shares
0