“Our true nationality is mankind.”H.G.

ም/ከንቲባ ታከለ ኡማ ጸጥታ የሚያደፈርሱ አካላትን በትዕግስት አናይም አሉ። ቂሮና የአዲስ አበባ ወጣቶች በጋራ ለመስራት ተስማሙ

ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት እና የከተማዋን ጸጥታ ለማደፍረስ የሚንቀሳቀስ ማንኛውንም ኃይል የከተማ አስተዳደሩ እንደማይታገስ አስታወቁ፡፡ የአዲስ አበባ ወጣቶችና የቄሮ  አመራሮች ከከንቲባው ጋር ከተወያይዩ በሁዋላ እንደተለመደው አብረው እንደሚሰሩ አረጋገጠዋል።

ምክትል ከንቲባው የነገው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራር አቀባበል ካለምንም ችግር እንዲጠናቀቅ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት ጋር ተወያይተዋል፡፡

ምክትል ከንቲባው በውይይታቸው ከመከላከያ ሰራዊት፣ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን እና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮምሽን ጋር እንዲሁም ከእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መቆጣጠርና መከላከል ባለስልጣን፣ ከጸጥታና ደህንነት፣ ከአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ጋር ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡

ውይይቱን ተከትሎም በሰጡት መግለጫ የከተማው አስተዳደር የመዲናዋን ጸጥታ ለማስከበር ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ህብረተሰቡ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች እራሱን መጠበቅ እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡ ምክትል ከንቲባው ሰሞኑን እየታዩ የሚገኙ የፀጥታ ችግሮች የህብረተሰቡን ክፍል የሚወክሉ አይደሉም ብለዋል፡፡

አቀባበሉንና ሰንደቅ አላማን ምክንያት በማድረግ በህዝቦች መካከል አላስፈላጊ ግጭት እንዲፈጠር እያደረጉ ያሉ አካላት ላይም አስተዳደሩ ህጋዊ እርምጃ እንደሚውሰድ አሳስበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ነዋሪም የኦነግ አመራሮችን ለመቀበል ከኦሮሚያ ክልል የሚመጡ ወንድሞቹን በእንግዳ ተቀባይነት ስሜትና በፍቅር ተቀብሎ እንዲያሰተናገዳቸው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

አቀባበሉ የተሳካና ሰላማዊ እንዲሆን መላው የከተማዋ ህዝብ የበኩሉን ድርሻ እንዲውጣም ምክትል ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ምክትል ከንቲባ ከመግለጫው መጠናቀቅ በኋላም ከቄሮ እና ከአዲስ አበባ ወጣት ተወካዮች ጋርም መክረዋል፡፡

ወጣቶቹ አሁን የተፈጠረውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ ፈተው ወንድማማችነታቸውን እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል። ወጣቶቹ ከምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ጋር ከተወያዩ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰንደቅ አላማን ምክንያት በማድረግ የተፈጠረውን አላስፈላጊ ግጭት አውግዘዋል።

ነገ የሚደረገው አቀባበል በሰላማዊ እና በደመቀ ሁኔታ እንዲከናወን በትብብር ለመስራት መስማማታቸውንም ገልፀዋል። በኤርትራ የሚገኘው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራር በነገው ዕለት መስከረም አምስት 2011 ዓመተ ምህረት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገባ ይጠበቃል፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በውጭ ሀገር ለሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ በርካታ ግለሰቦችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ቤት በመመለስ ላይ ይገኛሉ፡፡ 

ፋና – ፎቶ ፋና

0Shares
0