ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

የኦነግ አመራር ቡድን ኢትዮጵያ ገባ፤ ዳውድ ኢብሳ ለውጡ ግቡን እንዲመታ ከመንግስት ጋር እንደሚሰሩ አረጋገጡ፤

የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ የተጀመረው ለውጥ ግቡን እንዲመታ ከአዲሱ የለውጥ ሃይል መንግስት ጋር አብረው እንደሚሰሩ አረጋገጡ። አቶ ዳውድ አዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊይ በደረሱበት ወቅት ይንን ያሉት።

ፍና – የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳወድ ኢብሳን ጨምሮ የግንባሩ ከፍተኛ አመራሮች በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት እና በርከት ያሉ ደጋፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያም አቶ ዳውድ ኢብሳ በሰጡት መግለጫ፥ “ይህን የለውጥ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ወጣቶች፤ ቄሮው በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ተሳትፈዋል ኦነግም የዚህ ለውጥ አካል ነበር፤ በመሆኑም የዚህ ለውጥ አካል በመሆናችን መጥተናል” ብለዋል።

“አሁን ስልጣን ላይ ያለው የለወጥ ሀይል ለውጡ በሰላማዊ መንገድ እንዲከናወን በራፍ በመክፈቱ እና  ከዚህ ሀይል ጋር በመሆን  ለውጡ ግቡን እንዲመታ ለማድረግ፤ የኦነግን ተሳትፎ ሙሉ ለማድረግም ነው ወደ ሀገር ቤት የገባነው” ሲሉም አስረድተዋል።

በአጭር ጊዜ እቅዱም ፓርቲው በሰላማዊ ትግል ዙሪያ ከህዝቡና ከወጣቱ ጋር በመምከር ስልጠና እስከ መስጠት የደረሰ ስራ እንደሚያከናውንም ነው ያመለከቱት።

በፀጥታ እና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ዘርፍ ለውጡ ግቡን እንዲመታ ኦነግ ከመንግስት ጋር እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲገነባ ለብዙ ዓመታት ትግል ተደርጓል ያሉት አቶ ዳውድ፥ በዚህ ውስጥ የኦሮሞ ህዝብ ከፍተኛ መስዋእትነት መክፈሉን አንስተዋል።

ይህ ህዝብ ከላይ እስከታች መሪውን እንዲመረጥ ማስቻል ዋነኛ ስራችንም ነው ብለዋል። የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ካለ ህግ የበላይነት አይመጣም ያሉት አቶ ዳውድ፥ በሀገሪቱ የህግ የበላይነት እንዲሰፍን ህዝቡ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ አቅበዋል።

በአሁኑ ወቅት ከንጋቱ ጀምሮ ከአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ከሚገኙ ከተሞች ቁጥሩ ከፍ ያለ ነዋሪ በተሰባሰበበት መስቀል አደባባይ የአቀባበል ስነ ስርዓት በመከናወን ላይ ይገኛል።

OLF-from-Addis-750x430.jpg

ህዝብ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባውን የኦሮሞ ነጻነት ግምባር ኦነግ አባላትና አመራር ቡድንን ለመቀበል በመስቀል አደባባይ ተሰባስቦ እየጠበቀ ነው። ከንጋቱ ጀምሮ ከአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ከሚገኙ ከተሞች ቁጥሩ ከፍ ያለ ነዋሪ ለአቀባበል ስነ ስርዓቱ መስቀል አደባባይ ተገኝቷል።
 
በኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የፓርቲው ቡድን አዲስ አበባ የገባ ሲሆን፥ አሁን በመስቀል አደባባይ የአቀባበል ስነ ስርዓቱ ላይ ይገኛል።
በአቀባበል ስነ ስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማን ጨምሮ የተለያዩ ፓርቲዎች ተወካዮች እና ታዋቂ ግለሰቦች ይሳተፋሉ።
Related stories   የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ህወሓት” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ ወሰነ