• ‹‹ፖሊስ የፖለቲካ ቅጥረኛ አይደለም ፡፡ፖሊስ ፍትህን ለማሰከበር የቆመ ባለሙያ ነው ፡፡ፖሊስ ስለፖለቲካ አይመለከተውም፡፡የምርጦች ስብስብ መሆን አለበት››ዶክተር ኮማንደር ደመላሽ

ባሕር ዳር፡06/2010 ዓ.ም(አብመድ) የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሰት ፖሊስ ኮሚሽን ላለፉት ቀናት በየዘርፉ የሚገኙ የፖሊስ መኮንኖችን ሃገሪቱ የጀመረችውን ለውጥ ሊያሰቀጥል የሚችል የፖሊስ ሃይል ለመገንባት ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷል፡፡
ስልጠናው በአለፉት ዓመታት ሲታዩ የነበሩ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ጊዜ ወስዶ ያየ እንደነበር እና ለወደፊትም ነጻ እና ገለልተኛ የሆነ የፖሊስ አባል ለመገንባት ስምምነት የተደረሰበት እንደሆነ የፖሊስ አባላቱ ተናግረዋል፡፡
ምክትል ኮማንደር አለባቸው ይማም ስልጠናው ለማህበረሰቡ ስንሰጠው የነበረውን የህግ ስርአት እና እኛም ከማህበረሰቡ ስናገኘው የነበረውን አሉታዊ ምላሽ ያየንበት ነው ፡፡እስካሁን ድረስ የነበረው የፖሊስ ስርአት በፖለቲካ ማእቀፍ ውስጥ የነበረ እና ህዝቡ በሚፈልገው ደረጃ መሄድ ያልቻለ እንደነበር በጥልቀት አይተንበታል ብለዋል ፡፡ 
ሌላኛው ተሳታፊ ኮማንደር ሽመልስ አበራ ስልጠናው ችግሮቻችንን በሚገባ ያየንበት ሲሆን ከዚህ በኋላ ችግሮቻችን በደንብ እንድንመለከት እና የክልሉን ብሎም የሃገሪቱን ሰላም መረጋገጥ ለማስከበር የምንችለበትን አቋም እንድንይዝ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
በስልጠናው የመዝጊያ ስነ-ስርእት የክልሉ የፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም የተገኙ ሲሆን ስልጠናው አሁን የጀመርነውን ለውጥ ሊያስቀጥል የሚችል እና ለለውጡ የሚመጥን የፖሊስ አካል ለመፍጠር ታልሞ የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡ 
ኮሚሽነሩ የፖሊስ የመኖር ትርጉም ህግን ለማሰከበር እና ሰላምን ለማሰጠበቅ ነው፡፡ በመሆኑም በአንድነት በግለጸኝነት እና በገለልተኛነት የማህበረሰቡን ሰላም እና ደህንነት መረጋገጥ የፖሊስ ኃለፊነትም ግዴታም አለበት ብለዋል፡፡
ፖሊስ በእያንዳንዱ የህግ ማሰከበር ተልዕኮ ውስጥ ህዝብን ያማከለ መሆን መቻል አለበት፤ የሚፈጠረውን ችግር በአፋጣኝ ምላሽ መስጠት አለበት ነው ያሉት ኮሞሽነሩ ፡፡
ከዚህም ባለፈ የተጀመረውን ለውጥ ለማሰቀጠል ይረዳ ዘንድ ህዝቡ እንደጠላት የሚያየውን ፖሊስ ከማህበረሰቡ ጋር ለማቀራረብ እና ትስስራዊ የሆነ ሰላም ለመፍጠር እሰከ ቀበሌ ድረስ የፖሊስ አጀንዳዎችን በመቅረጽ ማህበረሰቡ ጋር አወንታዊ የሆነ ግንኙነት ለመፍጠር እንሰራልን ብለዋል፡፡
ማህበረሰቡ ፖሊስ በስርዓት አልበኝነት እና ህግን ባለማክበር የሰብዓዊ መብት እና ሌሎች ጥፋቶችን ሲያደርስበት ስለነበር ጠልቶት ቆይቷል፡፡ አሁን ግን ይህ አሰራር ሙሉ ለሙሉ ይቆማል ብለዋል፡፡
በመሆኑም አንድነታችን ጠብቀን የነበሩንን ችግሮች ለመቅረፍ ከዛሬ ጀምሮ ወደስራ መግባት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ለአለፉት ቀናት ስልጠና ሲሰጡ የነበሩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል ወርክ መምህር እና ተመራማሪ ዶክተር ኮማንደር ደመላሽ ካሳዬ “ፖሊስ የፖለቲካ ቅጥረኛ አይደለም ፡፡ፖሊስ ፍትህን ለማሰከበር የቆመ ባለሙያ ነው ፡፡ፖሊስ ስለፖለቲካ አይመለከተውም፡፡ ፖሊስ ስለልማታዊ ዴሞክረሲ ወይም ስለመንግሰታዊ ምርጫ የሚሰበክ ባለሙያ አይደለም ፡፡ 
ፖሊስ ከማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነጻ እና ገለልተኛ ሆኖ ለማህበረሰብ ሰላም እና ህግ ማስከበር ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል የሚሰራ ባለሙያ ነው ብለዋል፡፡
ዶክተር ኮማንደር ደመላሽ እሰካሁን የነበረውን የፖለቲካ እስረኛ ፖሊስ ሳይንሳዊ እና ማህበራዊ በሆነ ዘዴ ብቁ በማድረግ ፖሊሱን ለማህበረሰቡ ተቆርቋሪ ማድርግ መቻል አለበት ብለዋል ፡፡ከዚህም በተጨማሪ ፖሊስ ከደሞዝ ከፈላ ጀምሮ ብቃት ያለው እና የምርጦች ስብስብ መሆን መቻል አለበት ነው ያሉት፡፡
ህዝባዊ ወገንተኝነታችንን ጠብቀን ለክልሉ ሰላም መረጋገጥ እንተጋለን በሚል መሪ ሃሳብ ከነሀሴ 22/2010ዓ.ም እሰከ መስከረም 06 /2011ዓ.ም ሲካሄድ የነበረው የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን የመኮንኖች ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል፡፡
ዘጋቢ፡-ታርቆ ክንዴ

amara massmedia

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *