ኦሮምኛ እየተናገሩ ኦሮሞዎችንም ጎድተዋል። ኦሮምኛ በማነጋገር ከፖሊሶች ጋርም ይግባቡ ነበር። ቄሮ ናቸው። ከየትኛው የቄሮ መዋቅር እና ሴል እንዳፈነገጡ፣ ወይም መመሪያ እንደሚሰጣቸው ግራ ያጋባል። የቄሮ አደረጃጀት ባለቤት ነን የሚሉ በተደጋጋሚ ይህ አይነቱ ድርጊት አይወክለንም ብለዋል። ከዚህ አንጻር እነዚህ አካላት በቀላሉ ” ዘራፊ” በሚል የሚጠሩ ሳይሆን ዓላማና ግብ ያለው የህቡዕ አደረጃጀት አላቸው። ይህ አደረጃጀት በውስጥም በውጭም በኮድ የታሰሩ መመሪያዎች ይደርሳቸዋል። የበታች መንግስታዊ መዋቅርን አይፈሩም። እናም ብሄርን ከብሄር እንዲያጋጩ የተገዙ ተራ ሌቦች ሳይሆኑ በዓላማ የሚሰማሩ ” የተመረዙ ናቸው” የሚል አቋም በቡራዩ ነዋሪዎች ዘንድ አለ። ቦታ እየቀያየረ ሊከሰት የሚችልም እንደሆነ ይሰጋሉ

መግቢያ 

ይህ ሪፖርታዥ የተዘጋጀው የቡራዩ ነዋሪ የሆኑ ወጣቶችንና የሚመለክታቸውን አካላት በማነጋገር በተገኙ መረጃዎች መነሻነት ነው። ሪፖርቱ በአገሪቱ የተጀመረውን አዲስ አስተሳሰብና አመራር ከጅምሩ የሕዝብ ተአማኒነት ለማሳጣት በዓለም አቀፍና በአገር ደረጃ ሲካሄድ ከነበረው ቅስቀሳና ዘመቻ ጋር ያለውንም ግንኙነት ይዳስሳል። በዚህ ዳሰሳ እንደ ማሳየነት የሚካተቱት ሃሳቦች በሙሉ ከተለያዩ አካላት የተገኙና በቀጥታ ከተደረገ ቃለ ምልልስ የተገኙ ናቸው። ሪፖርታዡን ማደራጅት የተፈለገው ሁሉም ወገኖች በጥሞና ነገሮችን ያስተውሉ ዘንድ ስለታመነበት ነው። በሪፖርቱ “ያኮረፉ” የሚለው ሃረግ አዲሱን የለውጥ ሃሳብ የማይደግፉ፣ የሚቃወሙና ያደፈጡትን ግለሰቦች፣ ድርጅቶች፣ የማህበራዊ ገጽ ተቀናቃኞችና አዝማቾች የሚያመለክት ነው። 

ዋና ሃሳብ

ኢህአዴግ የሚባለው ድርጅት አገሪቱን ሲመራ በቆየበት ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ሰፊ መፈናቀል፣ ግድያ፣ ዝርፊያ፣ እንዲሁም ጎራ ለይቶ መላተም በስፋት የተስተዋለው ባለፉት አምስትና ስድስት ወራት ጊዜ ነው። ድርጅቱ መሪዎችን ቀየረ እንጂ መንግስት አልተገለበጠም። በኦፊሳል የታወጀ አዲስ ጉዳይ የለም። ሲስተሙ የድሮው አይነት ነው። በፌደራል ደረጃም ሆነ በክልል ደረጃ የሚመሩት ዋና ድርጅቶች ኢህአዴግና የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ናቸው። 

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ በድርጅቱ ህገ ደንብ መሰረት የተካሄደውን ለውጡን ተከትሎ ወዲያውኑ የተነሱት የህግ ይከበርና የህገ መንግስት ተሸረሸረ ጥያቄዎች መነሻቸው ህዝብን ግራ ያጋቡና ህዝብ ላይ የተጫኑ የጥቂት አመራሮች የግልጽነትና የኩርፊያ ውጤት ለመሆኑ አያጠራጥርም። ሰሞኑንን በተካሄደው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ለውጡን ተከትሎ የተካሄዱት ማናቸውን ተግባራት ህግን የተከተሉ መሆናቸውን ገምግሞ ይሁንታ እንደሰጠ በመገለጫ ተጠቁሟል። 

በዚሁ መሰረት ኩርፊያ ወያም ያኮረፉ ቢኖሩም በድምጽ ብልጫም ቢሆን በፓርቲ ደረጃ ” ትክክል ነው ህግን የተከተለ አሰራር ተግባራዊ ተደርጓል” ከተባለ፣ አሁን በመሪነት ደረጃ ያሉት ወገኖች ስራቸውን በአግባቡ እየሰሩ መሆኑንና የጣሱት ህግ እንደሌለ አመላካች ይሆናል። ታዲያ አካሄዱ በዚህ መልኩና ቀደም ሲል መሪ በነበሩት ሰዎች ሲደረግ እንደነበረው ከሆነ ዛሬ ምን አዲስ ነገር ተፈጠረ የሚለው ጉዳይ ከላይ በመነሻ የተጠቆመውን አብይ ጉዳይ ለማየት መነሻ ሆኖ ይወሰዳል። ምክንያቱም ይህ ሁሉ ቀውስ ያለ ምክንያት የተከናወነ፣ ያለ ምክንያት በጀት የተቆረጠለት፣ ያለ ምክንያት የህቡዕ አደረጃጀትና የማህበራዊ ገጾች አቀጣጣይ ነዳጅ እንዲደራጅለት አልተደረገምና!!

ቀውሱ የመነሻ ዓላማ እና መድረሻው  

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ወደ አመራር መምጣት ለውጡ እንዲደረግ በተለያየ መልኩ ከተደረገው ትግል ጋር በተያያዘ ኢህአዴግ ውስጥ ያልተገመተ በድርጅት ውስጥ ሌላ ድርጅታዊ ስራ የተሰራበት ነው። በአዴንና ኦህዴድ በዋናነት እንዲሁም ደህዴን በከፊል በፈጠሩት መተጋገዝ አብይ አህመድን ባልታሰበና ባልተገመተ ሁኔታ የድርጅቱ ሊቀመንበር እንዲሆኑ አስቻለ። በዚህም የተነሳ ህወሃት ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የተቀመጠበትን ወንበር ተነጠቀ።

ቀደም ሲል ድርጅቱ ባደረገው ተከታታይ ግምገማ የስልጣን ክፍፍል ፍትሃዊነት፣ የእኩል ተጠቃሚነት፣ የሚሊታሪና የደህንነት ሃይል ውስጥ የተመጣጠነ የሃላፊነት ድርሻ ላይ ቀደም ሲል የነበረው አሰራር አግባብ ስላልነበር እንዲስተካከል ስምምነት ላይ ተደርሶ እንደነበር የአራቱም ድርጅት መሪዎች ህዝብ ፊት በህብረት ቀርበው ይፋ አድርገው ነበር። በዚሁ መሰረት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የማመጣኑን ስራ በሪፎርም ደረጃ ጀመሩ።

ይህ አካሄድ ህወሃትን ቅር ስላሰኘው ተቃውሞውን በመግለጫ በተከታታይ አሰማ።  በሃላፊዎች ምደባና ብወዛ፣ እንዲሁም እድሜያቸው የገፉ በመቀነሳቸው ቅሬታው ከጀርባው አነሳሽ አገኘ። ህወሃት እነዚህኑ ” ታጋዮች በክብር ይሸኙልኝ” ሲል ሙግት ገባ። እነ አብይ ጥሪው አይሰማም ሲሉ ጥያቄውን ዘለሉት። ይህ ብቻ አልነበረም የመንግስትና የድርጅት ሚዲያዎች ባለተለመደ መልኩ በአገሪቱ ሲፈጸም የቆየውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ይዘከዝኩ ጀመር። ሙስናውን ገሃድ ያወጡ ገቡ። በተለይም የግፍ ሰለባ የሆኑትን ቀርበው የተቆረጠውን አካላቸውን፣ የተኮላሸውን ብልታቸውን፣ የመከነውን ተስፋቸውን፣ የተጎዳውን ሰነ ልቦናቸውን ሲናገሩ የጣላቻውና የኩርፊያው መጠን እየጋለ ሄደ። 

በዚህ መልኩ የተጀመረው አዲሱ ኢህአዴግ “አሸናፊና ተሸናፊ ብሎ ነገር የለም” ሲል ህዝብ የድሎች ሁሉ ባለቤት መሆኑን በይፋ ሲናገር ” ተራራውን አንቀጥቀጥ፣ የጦርነት ሰሪና ፈጣሪ፣ የትውልድ ሁሉ ጀግና” ተደርጎ በከፍተኛ በጀት ሆን ተብሎ የተገነባው ስነ ልቦና ተደረመሰ። በከተሞችና በተቋማት ላይ በግድ የተጫኑ ስያሜዎች ሳይቀሩ በነዋሪዎች ተሻሩ። ባነሮች ተወገዱ። ይህ ቁጭቱንና ኩርፊያውን አጋለው። ጉዳዩ ወደ ትክክለኛው ፌደራሊዝም የማምራት በመሆኑ ለአባላጫዎች መገዛት በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ፌደራሊዝም አግባብ እንደሆነ ለሚሰብከው ህወሃት እሬት ሆነበት።

በለውጡ ማግስት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ የተለያዩ ግዝቶች ያካሄዱት ስብሰባ ላይ ለሚቀርብላቸው ጥያቄ ሲሰጡ የነብረው ምላሻ እጅግ የከረረ ቅሬታ በፈጠረባቸው ክፍሎች አማካይነት ” ውይይትህን አቋርጠህ ተመለስ” የሚል ጥሪ እንደተላከላቸው የሪፖርቱ አቅራቢ በቂ መረጃ አለው። ይህ ሁሉ የሚያሳየው ለውጡ የህዝብን ልብ በደስታ እንዳላቀለጠ ሁሉ በተቃራኒው የበቀል እሳት እንዲጎርሱ ያደረጋቸው መኖራቸውን ነው። ደግሞም እውነት ነው።

ከዚህ ሁሉ ጎን ለጎን ግን አንድ ትልቅ ዘመቻ ነበር። ዘመቻውም ዶከተር አብይን በሰላማዊ መንገድ ማውረድ። በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ ሰላምና ማረጋጋት የሚችሉት፣ ልምዱም ያላቸው እነሱ በመሆናቸው በሰላማዊ መንገድ አብይን ለማሰናበት ለአሜሪካ መንግስት ጥያቄ ይቀርብ ነበር። በዚህ መረጃ በትክክል እነማን በስብሰባው ላይ እንደተገኙ በዝርዝር መናገር ባይቻልም፣ ጉዳዩ ቀርቦ ” አታስቡት” የሚል መልስ እንደተሰጠ ታማኝ ዜናዎችን በማቅረብ የሚታወቀውና የጠራ የዲፕሎማቶች ምንጭ ያለው ጎልጉል የድረ ገጽ ጋዜጣ  በስፋት ዘርዝሮታል። ካልይ በመነሻው እንደተባለው የዚህ ሁሉ ቀውስ መዳረሻ ፊርማታ አዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር ኢትዮጵያን በሰላም የማስተዳደር አቅም የለውም ወደሚለው ድምዳሜ መደረስ እንደሆነ የበርካቶች ስምምነት ነው።

ግጭት – እና የፖለቲካ ንግድ ከሶማሌ ክልል – ቡራዩ – ከዛም …

ባጭሩ በስማሌ ክልል የፈሰሰው ደም፣ የወደመው ንብረት፣ ያለፈው ህይወት፣ የደረሰው ስቃይና መፈናቀል ሊታመን የሚችል አይደለም። ገና አስከሬን ተለቅሞ ያላለቀበት ጭፍጨፋ፣ የታረዱት ብዛት የማይታወቅበት፣ በአንድ መቃብር ውስጥ እንዲጣሉ የተደረጉ ወገኖች ጉዳይ ገና ምርመራው ያልተጠናቀቀበት አረመኔነት የተሞላበት ድርጊት ሲያደራጅና መመሪያ ሲሰጥ የነበረ መሪ ” ለምን ታሰረ፣ የተያዘው ከመኖሪያ ቤቱ አይደለም፣ ተገኙ የተባሉት መሳሪያዎች የሱ አይደሉም፣ መብቱ ተረግጧል” በማለት ሲጮሁ የነበሩና እየጮሁ ያሉ ክፍሎች እነማን እንደሆኑ ለተመለከተ ጉዳዩ ብዙም ድብቅ አይሆንም።

የሰው ልጅ መሰየፉ፣ መገደሉ፣ መቁሰሉና መፈናቀሉ እንዲሁም የእናቶች፣ የአዛውንቶች፣ የእመጫቶችና የህጻናት ዋይታ እርፍት ሊነሳቸው ሲገባ ለአንድ ቦዘኔ፣ ገንዝብ ሜዳ ላይ እየረጨ ለሚሞላፈጥ፣ ከሰውነት ደረጃ ወርዶ ሴት እህቶችን የሚደፍር፣ እስረኞችን አንዱ የሌላውን ብልት እየዛዘ በስለፍ እንዲሄዱ የሚያደርግ፣ ጨፍጫፊ መብቱ ተነካ ብሎ ማላዘን፣ እሱ ቤተ መንግስት ደጅ ሆኖ ” ሰላም ነው፣ የክልሉ ልዩ ሃይል መከላከያንና የፌደራል ፖሊስን ድል በመንሳት ከከተማው አስወጥቷል፣ የመከላከያ ጣልቃ ገብነት ድባቅ ገብቷል…” እያሉ ሲዘፍኑ የነሩትን እድሜ በራሳቸው ሰዎች አድናቂነት በማህበራዊ ገጾች መመለከት ከሚሰጠው ግንዛቤ በላይ ምንም የሚባል ነገር አይኖርም።

ለሶማሌ ክልል ወሮበላ መሪ የክልሉ ምሁሮች የተናገሩት በቂ ስለሚሆን ብዙ ማለት ባያስፈልገም፣ የድጋፉና የእገዛው መነሻው ዛሬ ሳይሆን ቀድሞ የታሰበበት፣ በንግድና በግለሰቦች ጥቅም ላይ የተመሰረተ መሆኑ ይፋ መሆኑ ዛሬም ቢሆን ይፋ መሆኑ በአግባቡ ማሰብ ለሚችሉ በግራ መጋባት እንዳይመሽባቸው አስፈላጊ ነው።

ይህ እጅግ ዘግናኝ ጭፍጨፋ በቁትጥር ስር ሲውል፣ እንደታሰበው ውደ ሃረርና ደሬደዋ ገብቶ እንደተፈለገው የማተራመስ አደጋ ሳያደርስ በቁጥትር ስር መዋሉ ሲታወቅ፣ ወደ ደቡብ ክልል ተዛወረ። ደቡብ ክልል ሃዋሳ ላይ የሚያሳፍር ድርጊት ተፈጸመ። ድርጊቱ አሳፋሪ ከመሆኑ ባሻገር የገንዘብ ድጋፍ የተደረገለትና የብሄር የርስ በርስ ግጭት ለማቀጣጠል የታሰበ መሆኑ ይፋ ሆነ። እነማን ናቸው? ለሚለው ግልጽ ያለ መልስ ባይሰጥም፣ ገንዘብ ያላቸው የለኮሱት ዓላማ ያለው የውክልና እልቂት እንደነበር ሚዲያዎች ይፋ አድርገዋል። ሶዶም ተመሳሳይ ነበር። የሻሸመኔውም ይጠቀሳል።

ቡራዩ ዙሪያ

በግልጽ ከመንግስት ሃላፊዎች የተነገረው በቡራዩ ዙሪያ የተፈጸመውን አስነዋሪ ግድያ፣ ዘረፋና የአስገድዶ መድፈር፣ እንዲሁም የንብረት ማውደም ተግባር የፈጸሙት የተደራጁ ናቸው። እነዚህ የተደራጁ ቡድኖች በኦነግ መሪ አቀባበል ላይ ከተገኙ በሁዋላ ሌሎች  ጉዳያቸውን ፈጽመው ወደመጡበት ሲመለሱ ወደ ተፈጠሩበት ዓላማ /ግድያ/ የተሰማሩ ናቸው።

የቡራዩ ኦሮሞ ወጣቶች እንደሚሉት አንዳቸውም የአካባቢው ነዋሪ አይደሉም። አንዳቸውም አይታወቁም። ሲጠየቁም ይህንን ስለማድረጋቸው ምክንያት አያቀርቡም። ዓላማቸው ብሄርን ከብሄር ለማጫረስ እየተዘዋወሩ ጥቃት ማድረስ ነው። በደንብ የተደራጁና መሳሪያም ያላቸው ናቸው።

እነዚህ የኦሮምኛ ቋንቋ የሚናገሩ በወጉ የተደራጁ ቡድኖች ከሆለታ ማዶ የተነሱ እንደሆነ የቡራዩ ወጣቶ ች ይናገራሉ። የቡራዩ አካባቢ ነወጣቶች  አብሮ አደግ ጓደኞቻቸውን በመጠለያ ውስጥ ብመሄድ እያለቀሱ ጎብኝተዋል። ምሳ አዘጋጅተው አብልተዋል። እነሱ እንደሚሉት ካሁን በሁዋላ ትዕግስታቸው አልቋል። ተደራጅተው ከስልሳ እስከ ሰባ በመሆን ከተማቸውንና አካባቢያቸውን መጠበቅ ጀምረዋል። በአንድ ቀን ብቻ ከአራት መቶ በላይ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለመጠበቅ በራስ ተነሳሽነት ተመዝግበዋል።

ከቡራዩ ያገኘነው መረጃ አሁን ይህ ድርጊት ከመፈጸሙ በፊት ሰዎች ሞተው ይገኙ ነበር። ገዳያቸው ግን አይታወቅም። ህዝብ ፍርሃቻ እንዳለው ለፖሊስ አስቀድሞ ያሳውቅ ነበር። እነሱ እንደሚሉት ኦህዴድ የፖሊስ፣ የቀበሌና የበታች አመራሩ ጤነኛ አይደለም። ህዝብ በዚህ ጉዳይ ትዕግስቱ እያለቀ ነው። የቲም ለማ ደጋፊ የሆኑ ኦሮሞዎች እንዲሁም ሌሎች በታችኛው እርከን ባለው አመራር እምነት የላቸውም። እንዲያውም የታችኛው አመራር ካኮረፉት ወገኖች ጋር ግንኙነት እንዳለው ግምታቸው ሰፊ ነው።

እነዚህ ቄሮ መሆናቸውን የሚገልጹ፣ ቄሮ የሚል ሸሚዝ የሚያጠልቁ የተደራጁ ወንበዴዎች ዓላማቸው ተራ ዝርፊያ ባለመሆኑ ከስያሜያቸው ጀምሮ የሚገለጹበት አግባብ ትክክል አለመሆኑንን የቡራዩ እና አካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ። ” የተመረዙ” ይመስላኡ የሚሉዋቸው እነዚህ የቡድኑ አባላት በአንድ በውል በማይታወቅ ሃይል የተጋቱትና እንደሰው እንዳያስቡ የሚያደርጋቸው ነገር አለ። ጋሞዎችን፣ ስልጤዎችንና፣ ጉራጌዎችን ነጥለው ሲያጠቁ የሚያቀርቡት ምክንያት ተራና ተልካሻ ነው። 

አዲስ አበባ ላይ ጋሞዎች እንደፈነከቱዋቸው ከመግለጽ ውጪ ምንም የሚሉት ሌላ ነገር የለም። ግን አጠቃላይ ሁኔታቸው የሚቅበዘበዙና ጤና ያላቸው አይመስሉም። የብር ሽግር እንደሌለባቸው ይናገራሉ። ለዚህም ይመስላል ንብረት ማቃጠል ምርጫቸው ነው። የሪፖርቱ አቅራቢ ከጀርባቸው ስላለው ሃይል ጠይቆ ነበር። ሁሉም የሚሉት ” ድረስበት የሚታወቅ ነው” የሚል ነው። ስም አይጠቅሱም ነገር ግን ዓላማው በመላው አገሪቱ የብሄር እርስ በርስ ግጭት ለመለኮስ ያቀደ ነው።

እንደ ወጣቶቹ ከሆነ በትናንትናው እለት ብቻ ከሁለት መቶ በላይ የተደራጁ ሃይሎች ተያዘዋል። የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ አላማው ተራ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እንደሆነ አስታውቀዋል። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ፖሊስ ቸልተኛ ሆኗል በሚል የቀረበውን አቤቱታ አስተባብለው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መታሰራቸውንና አሰሳው መቀጠሉን፣ ካሁን በሁዋላ በአካባቢው ፖሊስ ሃላፊነት እንደሚወስድ አመልክተዋል። 

አንዳንዶች አካባቢው ወጣ ገባ ብመሆኑ ለፖሊስ ስራ አዳጋች መሆኑንን መጠቆማቸውን ቢተቹም አካባቢውን የሚያውቁ ግን ለተደራጀው ቡድን አባላት ተሸሽጎ ለማጥቃት የቦታው ወጣገባነት እርዳታ ያደርጋል። ያም ሆኖ ግን ፖሊስ ቀደም ሲል አቤቱታና ስጋት ቢቀርብለትም  ዳተኛ እነደነበር ግን ያምናሉ።

ማጠቃለያ

ሲጀመር የጠ/ሚኒስትር አብይ አመራር አገሪቱን በሰላማዊ መንገድ አይመራም የሚል ዘመቻ ነበር። ዘመቻው ዛሬ ዜጎች ጥርጣሬ ላይ እንዲወድቁ በየደረጃው በተግባር ተደግፎ እየሰራ እዚህ ደርሷል። እናም እነ ዶክተር አብይ ማስተዳደር አቅቷቸዋልና ማን ይምጣና ቤት ለቤት እየዞረ የአገሪቱን ህዝብ ሰላም ይጠብቅ? ያስጠብቅ?

በፕሮጀክት ደረጃ እንደ ዶከተር አብይን ለመብላት፣ እነ ለማ መገርሳን በኦነግ ጫማ ለመቀየር የሚደረገው ሩጫ እዚህ ላይ ደርሷል። ኦነግ እንዲህ ያለውን ወሬ አቁሙ ሲል የአስመራውን ሰምምነት ተግራዊ ለማድረግ እንደሚሰራ ይፋ አድርጓል። ቄሮ የሚባለውን ሃይሉን በአዲስ አስተሳሰብ እንደሚያሰለጥን፣ እንደሚያንጽ፣ ይፋ አድርጓል። ሌሎች ህብረ ብሄር የፖለቲካ ደርጅቶች ከደጋፊዎች ስሜታዊ ጫጫታና የስሜት ዲስኩር በዘለለ ጫናቸው እጅግ ነው ባይናልም ሊረባረቡ እንደሚገባ ይጠበቃል። 

ህዝብ በተደጋጋሚ በርጋታ ርሱን፣ አካባቢውን፣ እንዲሁም ለውጡን እንዲጠብቅ ተነግሮታል። ሁሉም ነገር ያለው በመረጋጋት ውስጥ ብቻ ነው። የቡራዩ ወጣቶች እነዚህ ከዝርፊያ የዘለለ ዓላማ ያላቸው የተደራጁ ሃይሎች ለክፋት እንደተደራጁ ሁሉ ሌሎች ለመልካም ነገር አለመደራጀታቸው ጉዳት አለው። ቢያንስ አካባቢን ነቅቶ ለመጠበቅ መደራጀት ግድ ነው። አገሪቱ ያገኘችውን መላካም አጋጣሚ አሽቀንጥሮ መጣል ዋይታው ለዘላለም ይሆናልና። እናም የማሳጣቱ ዘመቻ እዚህ ደርሷል። 

ፈቃደኛ ሪፖርተር ለዛጎል ከአዲስ አበባ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ኢትዮጵያና የዓለም ባንክ የ200 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ተፈራረሙ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *