ከአሁን በኃላ የሚስተዋሉ የህግ ጥሰት እና የስርዓት አልበኝነት ባህሪ ያላቸው ድርጊቶችን አንታገስም ሲሉ የደኢህዴን ሊቀመንበር እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል አስታወቁ።

ወይዘሮ ሙፈሪያት ይህንን መታገስ ማለት የሰዎችን ደህንነት አደጋ ውስጥ መክተት ነው ብለዋል ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ።

ሊቀመንበሯ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ተጎጅዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ መቀጠል ባለበት ሁኔታ ላይ እራሱን የቻለ ኮሚቴ ተዋቅሮ ጉዳዩን በፍጥነት ለመቅረፍና መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ ነው ብለዋል።

የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን አንስተው፥ ጉዳዩም ከብሄር ጋር የሚያገናኘው ነገር ባለመኖሩም በደቡብ ክልል ያሉ ሰዎች ጉዳዩን ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ በትእግስት እንዲጠባበቁ ጥሪ አቅርበዋል።

ሊቀመንበሯ ዴሞክራሲ ያለህግ የበላይነት እንደማይረጋገጥ ጠቅሰው፥ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ የምርጫ ጉዳይ አይደለም ሲሉ ገልጸዋል።

በጥቅሉ የዲሞክራሲ ምህዳር ማስፋት ማለት ነገሮች መረን በለቀቀ መልኩ እንዲሄዱ መፍቀድ ያለመሆኑን ጠቅሰው፥ ከዚህ ጋር በተያያዘ የተዝረከረኩ አስተሳሰቦች መታረም አለባቸው ብለዋል።

በተጨማሪም የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ በበኩላቸው ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ በየትኛውም ወገን ያሉ ወጣቶች ጉዳዩን ሰከን ብለው ማየት እንዳለባቸው አስታወቀዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በቡራዩ አካባቢ የክልሉ ተወላጆች ሞትና እንግልት እንደደረሰባቸው ጠቅሰው፥ ከኦሮሚያ ክልል መንግስትና ከአዲስ አበባ መስተዳድር ጋር ክልሉ በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝ ነው የገለፁት።

ርዕሰ መስተዳድሩ አሁን ከምንም ነገር በላይ መረጋጋት የሚገባን ጊዜ ላይ ነን ከዚህ በላይ ነገሮች መሄድ አይገባቸውም ብለዋል።

በቡራዩና አካባቢው የተከሰተውን ችግር ተከትሎም በአርባ ምንጭ ሀዘናቸውን ለመግለጽ የወጡ ዜጎችም ጉዳት እንደደረሰባቸው አንስተው አሁን ላይ ግን ሁኔታው ረገብ ማለቱንም ጠቅሰዋል።

በርግጥ ችግሩን ከክልሉ መንግስት ጋር ተነጋግረን መፍታት የምንችለው ጉዳይ ነበር እዚህ ድረስ መድረስ አልነበረበትም ሲሉ አንስተዋል።

ችግሩ በደቡብ ክልል ተወላጆች ላይ በስፋት የሚታይ ቢሆንም በጥቅሉ አሁን ካለንበት ምዕራፍ ጋር ተያይዞ የተከሰተ መሆኑን አንስተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አሁን የተከሰተውን ሁኔታ ተወያቶና ተነጋግሮ መፍታት የሚቻሉ ጉዳዮች በመሆናቸው ሰከን ብለን ብናያቸው መልካም ነው ሲሉ አሳስበዋል።

በሌላ በኩልም በጉራጌ ዞን ግጭት መከሰቱን አንስተው ቀበሌዎችን ከማካለል ጋር በተያያዘ የተነሳ መሆኑንም ገልጸዋል።

ይህን ግጭት ተከትሎም የንብረት ውድመትና የሰው ህይወት መጥፋቱንም ነው ያነሱት።

ርዕሰ መስተዳድሩ ግጭቶችን ቀድመው ከመከሰታቸው በፊት የመለየት ችግር ላይ የአመራር ክፍተት መኖሩን የተናገሩ ሲሆን፥ ዛሬ ላይ ፈንድተው የወጡት ችግሮችም ቅጽበታዊ ያለመሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ከዚህ ቀደም የተከመሩ ሳይፈቱ የቀሩ ችግሮችም ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉም ነው የተናገሩት። በደቡብ ክልል የተከሰተው ችግር በአሁኑ ሰዓት በቁጥጥር ስር መዋሉን አንስተው ከኦሮሚያ ክልል ጋር በሁኔታው ላይ በርብርብ እየሰሩ እንደሚገኙም አንስተዋል።

(ኤፍ.ቢ.ሲ)

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   “የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች አለመምጣት የሚያጎለው አንዳችም ነገር የለም፤ እኛም አንጠብቃቸውም” ፕሮፌሰር በየነ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *