Opinion -ከሐይለገብርኤል


ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ እዚህ መድረስ የኦሮሞው  ወገናችን  ድርሻ  ቀላል አይደለም:: ዘመን ከባተ ፊደል መቁጠር ሲጀመር ከስልጣኔ ጋር ሰይጣናዊ የጥላቻ እርዕዮተ ዓለም የተጋቱት የመጀመሪያዎቹ የኦሮሞ ታጋይ ድርጅቶች ያመጡት ፈተና ይህው ለዛሬው ትውልድ ተርፏል:: ጠባብና ጨለምተኛ የሆኑት አንዳንድ አክቲቪስቶችና የፖለቲካ መሪዎች ትውልዱን በዛገ የታሪክ እግረሙቅ ጠፍረው የተጨቋኝነት  ትርክታቸውን  እየተጋተ በበታችነት ደዌ ተጠቅቶ ከዘመኑ ጋር እንዳይራመድ ወደጋርዯሽ ዘመን እየወሰዱት ይገኛል::

በዚ ባለንበት የስልጣኔ ዘመን አውሮፓና አሜሪካ ኖረው የቆንጨራ አያያዝን የሚያስተምሩና ያጡትን የዘረፋ ስልጣን ለማስመለስ እየተጉ ነው። እነዚህ ሃይሎች ተጋግዘው ትውልዱን በጥላቻ ቅስቀሳ አስክረው ለደም ማፍሠስ የሚያዘምቱ የቀን ጅብ ጭራቆች ገፋፊነት በአዲስ አበባ ዙሪያ በንጹሃን ወገኖቻችን ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ተፈጽሟል::

ይህን አይነት ድርጊት በዚህ ዘመን ያሳፍራል:: ከምዕራቡ ዓለም የስልጣኔና የነጻነት ሃገር ሄዶ ሽብርና ሁከትን ማስፉፉት  ያስደነግጣል::  የነጻነት  ሕይወት አጥቶ መከራውን ሲያይ በኖረ ሕዝብ ትከሻ ላይ ዝናና ስልጣንን ለማግኘት መሞከር ከፍ ያለ ዋጋም ያስከፍላል:: የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘሌቄታዊ የለውጥና የዲሞክራሲ ስርአት ለማሸጋገር መድከም ሲገባ ብጥብጥና ሁከት ማንገስ ለማናችንም የማይጠቅም ሃገር አፍራሽ ድርጊት ተቆጥቦ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም ወገን ቆም ብሎ ሊይስብበት ይገባል::

የኦሮሞ ወንድሞቻችን በዘመነ ወያኔ አስከፊ መከራ ሲፈጽምባቸው ቆይቷል:: የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር (ሕወሃት) የኦሮሞን ሕዝብ እያሰረና እየገደለ በላዪ ላይ የሚፈልገውን እየሾመ ለ27 አመታት ያደረሰው መከራ ጠባሳው በግልጽ የሚታይ  ነው::  እውነታው  ይህ  በመሆኑ  ለ27 አመታት ጸንቶ የኖረውን የሕወሃት የባሪያ አሳዳሪ አገዛዝ ለመገርሰስ ላለፋት 3 አመታት የኦሮሞ ወጣቶች (ቄሮ) መራር ትግል በማድረግ ከሌሎች የኢትዮጵያ የትግል ሃይሎች ጋር በጣምራ አሁን የሚታየው ለውጥ መጥቷል::

በትግሬ ወያኔዎች አዝማችነት :  የኦሮሞ ወጣት በየጥሻው እየተገደለ ጥፍሩ እየተነቀለና ብልቱ እየተኮላሸ የደረሰበት መከራ አንረሳውም:: እናት በልጇ አስከሬን  ላይ የተቀመጠችበት ዜና  በእግሩ ተራምዶ የገባው  እግሩ  ተቆርጦ የወጣው ሕያው ምስክር በሕይወት እያለ ጨለምተኞቹ    አክቲቪስትና     አንዳንድ መሪ ነን ባዮች ምዕተ ዓመት ያለፈውን የታሪክ መቃብር ሲቆፍሩና ከእኛ አልፎ የዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት አርማ በሆነው ባንዲራ ላይ ሲዘባበቱ እናያለን::

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ የብሄር ፖለቲካው ድንበሩን አልፎ ትልቁን የኦሮሞ ሕዝብ አሳነሰው  ያሉት  ከዚህ  አንጻር  ይመስለኛል::  ታሪክ የሰራው ቄሮ በሴረኞች ተጠልፎ በሽብር   ስሙ   እየጎደፈ   ነው::    የለውጡ   ሃዋርያ   ቄሮ የቀልባሾችም ደቀመዝሙር እንዳይሆን የሚሰጋ ቢኖር አይፈረድበትም::   የኦሮሞ ልጆችን በገፍ ሲያድገድልና ደም ሲመጥ የኖረው ስብሃት ነጋ የኦነግ ወዳጅና ተቀባይ  መስሎ  መታየቱ ከጀርባው ሴራ ቢኖር ብሎ ቢጠረጠር አይገርምም::

የኦሮሞ ልሂቃንና ሽማግሌዎች ጥላቻና መለያየትን የሚሰብኩት የትግሉ መሪ ነን የሚሉትን የስደት ተመላሽ ወጠጤዎች አደብ ሊያስገዙና ሊመክሩ ይገባል:: ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ ለማንም የማይበጅ በሶሪያና በየመን የታዩትን ጥፉቶች የሚያስከትል ድባብ ውስጥ መሆናችን መዘንጋት የለበትም::

የሕዝባችን መብት እንዲረጋገጥ እኩልነትና ነጻነት እንዲሰፍን ባለፋት አመታት በኦሮሞ የፖለቲካ ሃይሎች ተፈጽሟል የሚባለውን  ጥቃት  ለታሪክ  በመተው ነገን የተሻለ ለማድረግ አብረን ታግለናል:: በዚህም በተለይ የአማራ ተቆርቋሪ ነን ባይ ጠባቦች ብዙ የስም ማጥፋት ዘመቻም ደርሶብናል:: ነገር ግን አሁን የምናየው ሁኔታ እንዳይፈጠር በግዜ ለመመከት ብዙ ጥረት አድርገናል ::

ከምርጫ 97 ጀምሮ በዶር መራራ መሪነት በህብረቱ ውስጥ ከኦብኮ ጋር ሰርቻለው :: በሗላም ከቀድሞው ኦነግ መስራቾች የአሁኑ ኦዴግ ጋር በቅርብ አብሬ ተንቀሳቅሻለው::    በዚህ   ሁሉ   እንቅስቃሴ የተዋወኳቸው የኦሮሞ ፖለቲከኞች ብዙ ተምሬያለሁ ብዙም ወዳጆች አግኝቻለሁ :: ይህን የመሰል እድል በማግኘቴም የኦሮሞን ጉዳይ ከራሴ ጉዳይ ነጥዬ እንዳልመለከት አድርጎኛል::

ከኦሮሞ ወጣቶች ጋር አድገናል :: ለኔ በግሌ የቅርብ ጏደኞቼና ሚዜዎቼ ጭምር ኦሮሞዎች  ናቸው::   በኦሮሞነታቸው  የሚኮሩ  :   በኢትዮጵያዊነታቸው የሚደሰቱ የምኮራባቸው ወንድሞቼ ብዙ   ናቸው::   በተለይ   በተለይ   መቼም የማልረሳው በቅርቡ የተለየን ውድ ወንድሜ ጏዴና  መካሪዬ   የምለው ምርጡ የአምቦ ልጅ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር አመራር ዘውዴ ጉደታን ልገልጽበት የምችልበት ቃል የለኝም::

ኦሮሞ አቃፊ የሆነ የጉዲፈቻ ምርጥ ባህልያለው ማህበረሰብ እንጂ አንዳንድ አፍራሾች እንደሚያራግቡት የአግላይነት ልማድ  የለውም::   የኦሮሞ የአማራውና የሌሎች ኢትዮጵያውያን ብሄሮች በመከባበር ላይ የተመሰረተ ስርዐት ከመገንባት ውጪ ምንም አይነት አማራጭ የለንም :: ይህ በመሆኑም ሰሞኑን የታየው አይነት ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት መፈጸሙ ሁሉም ሊያወግዘው ይገባል:: ሌላው የአዲስ አበባ ሕዝብ ሕልውና በእጃችን ነው የሚለው የልጆች ቅስቀሳና ለውጡን እኛ ነን ያመጣንው የሚለው መሰረት የለሽ ትምክህት ገደብ አድርጎ የተገኘውን የለውጥ ጭላጭል ወደ ሰፊ ብርሃን ለማሸጋገር ተደጋግፈን ብንቆም አትራፊ ያደርገናል;

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *