የሰንቀሌ የፖሊስ ማሰልጠኛ ማዕከል ሰልጣኞች የሆኑ ወደ 3 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች የጤና እክል እንደገጠማቸው ተገለጸ። ሰልጣኞቹ ከትላንት ምሽት ጀምሮ በአቅራቢያቸው ወደሚገኙ የህክምና መስጫዎች አቅንተዋል።

ህክምና ከተሰጠባቸው ሆስፒታሎች አንዱ የሆነው የአምቦ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ጎንፋ ሞቲ ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ ሰልጣኞቹ የገጠማቸው የጤና እክል መነሻው የምግብ መመረዝ አልያም የተበላሸ ምግብ መብላት ሊሆን ይችላል። ሰልጣኞቹ ከተመገቡት ምግብና ከመጠጣቸው ናሙና ተወስዶ ለምርመራ ወደ አዲስ አበባ መላኩንና ውጤቱን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን አክለዋል።

ዶክተሩ እንደገጹት ሰልጣኞቹ ትላንት ምሽት ከ3:30 ጀምሮ ወደሆስፒታሉ ሄደዋል። ከመካከላቸው በጣም ተዳክመው የነበሩም ይገኙበታል። እስከ ለሊቱ 8:30 ድረስም ለሰልጣኞቹ ህክምና ተደርጓል። ከታካሚዎቹ መካከል ለህይወት የሚያሰጋ የጤና እክል የደረሰባቸው እንደሌሉ ዶክተር ጎንፋ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ወደ አምቦ ሪፈራል ሆስፒታል የሄዱት ሰልጣኞች ወደ 2,000 የሚጠጉ ሲሆን፤ በአምቦ አጠቃላይ ሆስፒታልና በጉደር ሆስፒታል ህክምና ያገኙም አሉ። ከሰልጣኞቹ መካከል ህክምና አግኝተው ወደ ስልጠና ማዕከሉ የተመለሱና ህክምና በመከታተል ላይ ያሉም ይገኙበታል።

ሰንቀሌ የፖሊስ ማሰልጠኛ ማዕከል ከአምቦ በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛል።

BBC Amharic

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *