“Our true nationality is mankind.”H.G.

ጠ/ሚ አብይ “ኦሮሞ ወላዋይ አይፈልግም፤ በህዝቡ የምትነግዱ ለራሳችሁም፤ ለኦሮሞ ህዝብም አትሆኑም፤ ጠዋት እዚህ፤ ከሰዓት ደግሞ እዚያ አትቁሙ”

ዶር አብይ በጅማ እየተካሄደ ባለው የኦህዴድ 9ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ ከተናገሩት የተወሰዱ ዋና ዋና ነጥቦች

. ኢትዮጵያን እንገነባለን፣ አፍሪካን እንገነባለን፣ ማንም ኃይል ደግሞ ከዚህ ሊያቆመን አይችልም፡፡

. ኦሮሞ ማቀፍን፣ እናት የሌላቸውን ልጆች ማሳደግን ነው ያስተማረን፣ ኦሮሞ ከተዋጋ ያሸንፋል እንጂ ሰውን መግደልን አላስተማረንም፡፡

. የዚህ አገር አንድነት ለማስጠበቅ ኦሮሞ ኃላፊነት አለበት፡፡

. ኢትዮጵያ ከጠላት ጋር ባደረገችው ጦርነቶች ውስጥ ኦሮሞ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

. አባጅፋር ለኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም ጭምር አርቀው የሚያስቡ ነበሩ፡፡

. አሁን ባለንበት ዘመን በትናንትናው ስልት ማሸነፍ አይቻልም፡፡

. ኦሮሞ አገር መምራት አይችልም የሚሉን አሉ፤ ኦሮሞ አገር መምራት ብቻ ሳይሆን አገር መገንባት ይችላል፤ ኦሮሞ ገዳን ለዓለም እንደ ሰጠ ሁሉ፣ ኦሮሞ በቅርቡ አዲስ ፍልስፍና ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ሰጥቶ ሊያሳያቸው ይፈልጋል፡፡

. የሚዲያ ጦርነት፣ የጦር ሜዳ ጦርነት፣ የኢኮኖሚ ጦርነት ማድረግ ስለምንችል ጠላቶቻችን ሁለት ሶስቴ ማሰብ አላባችሁ እንላለን፡፡

. ከጠላት ጋር ሆናችሁ የኦሮሞ ትግልን ወደኋላ ለመመለስ ያሰባችሁ ካላችሁ ከጠላት ለይተን አናያችሁም፡፡

. የህግ የበላይነት የማስከበር ኃላፊነት ለማንም አሳልፈን አንሰጥም፡፡

. ከዚህ በኋላ በኦሮሞ ስም መነገድ አይቻልም፡፡

. አስራ አምስት፣ ሃያ ሆኖ ለኦሮሞ መታገል አያስፈልግም፤ ከበዛ ሁለት ሶስት ፓርቲዎች ለኦሮሞ በቂ ናቸው፡፡

. አብሮ መቆም ማለት ጠዋት ጠዋት እዚህ መቆም ከሰዓት፣ ከሰዓት ደግሞ እዚያ መቆም ማለት አይደለም፡፡

. ከሁሉም ኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በጋራ በአንድነት ተባብረን መስራት አለብን፡፡

. ኦሮሞነት በርካታ ነገሮችን አስተምሮናል ፤ በገዳ ስርዓት መሰረት ብሔር ብሔረሰቦችን አቅፈን በጋራ መስራት ይጠበቅብናል፡፡

. ዋናው መልዕክት አሸናፊን ሀሳብ መያዝ ነው –  EBC


ኤፍ ቢ ሲ – ወደተሻለ አሸናፊነት ለመሸጋገር ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦችን በማቀፍ በጋራ ልንሰራ ይገባል አሉ የኦህዴድ/ኢህአዴግ ሊቀመንበር እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ።

ዶክተር አብይ አህመድ በ9ኛው የኦህዴድ ድርጅታዊ ጉባኤ መክፈቻ ስነ ሰርዓት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ከመበታተን ወጥተን በአሸናፊነት መንፈስ ሀገሪቷን ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ልንረባረብ ይገባል ብለዋል።

የኦሮሞ ህዝብ ከዚህ በፊት በነበሩት የጭቆና ስርዓቶች ባርነትን እሺ ብሎ ተቀብሎ ተሸንፎ አያውቅም፤ ሲታገልም ኖሯል ነው ያሉት።

አባቶቻችን የገነቡልንን ሀገር ከሌሎች ብሄሮች ብሄረሰቦች ጋር በመተባበር ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመቀናጀት ምስራቅ አፍሪካን ለመገንባት እንነሳም ብለዋል።

የኦሮሞ ህዝብ በስሙ ከተደራጁ እና ከሚታገሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

አባቶቻችን ባወረሱን የገዳ ስርዓት ለአፍሪካ ችግር መፍትሄ መሆን እንችላለን ያሉት ሊቀመንበሩ፥ እንደ አባቶቻችን አሸናፊ መሆን ከፈለገን ምስራቅ አፍሪካን ለመገንባት አንድነታችንን ማጠናከር ይኖርብናል ነው ያሉት።

በ9ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ አዲስ ስያሜና አዲስ አደረጃጀት እንዲሚፀድቅና አዲስ አመራር እንደሚተካ በመግለፅ ሌሎች ድርጅቶችም የትግል ቅብብሎሽን ባህላቸው እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

የህግ የበላይነትን አሳልፈን አንሰጥም ያሉት ዶክተር አብይ፥ ከዚህ በኋላ በህዝቡ ስም መነገድ አይቻልም ብለዋል። የኦሮሞ ፓርቲዎች በመበታተን የህዝቡን አንድነት መበተን እንደሌለባቸው በመግለፅ፥ ቢበዛ ሶስት አልያም ሁለት ሆነው ቢታገሉ ሲሉ መክረዋል።

ኦሮሞ ወላዋይ አይፈልግም፤ በህዝቡ የምትነግዱ ለራሳችሁም፤ ለኦሮሞ ህዝብም አትሆኑም፤ ጠዋት እዚህ፤ ከሰዓት ደግሞ እዚያ አትቁሙ ነው ያሉት።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   “…ለዛሬ ብለን ነገን ከምናበላሽ፣ ለነገ ስንል ዛሬን እንሠዋ” አብይ አህመድ
0Shares
0