የአርበኞች ግንቦት 7 አቀባበል ኮሚቴ አባል የሆነው ወጣቱ ፖለቲከኛ ብርሃኑ ተክለያሬድን ጨምሮ በአዲስ አበባ እና በአዲስ አበባ ዙሪያ ሁከት እንዲፈጠር ረድተዋል በሚል የተጠረጠሩ ፍርድ ቤት ቀረቡ።

ፖሊስ ምርመራውን ለማጠናቀቅ የጠየቀው የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮም ተፈቅዶለታል።

በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ምድብ ችሎት የቀረቡት ተጠርጣሪዎች በበኩላቸው ሰብዓዊ መብትን የሚጥስ አያያዝ እየተተገበረባቸው እንደ ሆነ ለፍርድቤቱ ተናግረዋል።

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ የሆኑት ሄኖክ አክሊሉ ደንበኞቻቸው በጨለማ እና ቀዝቃዛ ክፍል እንዲታሰሩ መደረጋቸውን፣ ከህገ-መንግስቱ በተፃራሪ ፍርድ ቤት የቀረቡት ከ48 ሰዓታት በኋላ መሆኑን እንዲሁም ወጣት ብርሃኑ ተክለ ያሬድ በተለይ «የአዕይምሮ ህመም አለበት» ተብሎ ከሚጠረጠር ሰው ጋር እንዲታሰር መደረጉ ለህይወቱ አስጊ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ማስረዳታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል። ፍርድ ቤቱም ተጠርጣሪዎች በተገቢው መንገድ እንዲያዙ ፖሊስን ማሳሰቡንም አክለው ነግረውናል።

ፖሊስ ተጠርጣሪዎች ሁከትን በማስተባበር እና በመፍጠር ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ያሳያሉ ያላቸውን ሰነዶች እና የባንክ ደብተር እንዳሉት ሆኖም ተጨማሪ ማስረጃ ለማሰባሰብ ተጨማሪ ቀን ያስፈልገኛል በማለት የጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል።

ብርሃኑ ተክለያሬድ ከዚህ ቀደም በሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ በነበረው ተሳትፎ ፣ቆየት ብሎ ደግሞ «የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄን ሊቀላቀል ሞክሯል » በሚል ለእስር መዳረጉ አይዘነጋም። ብርሃኑ በቅርቡ ከእስር ከተፈቱ የፖለቲካ እስረኞች መካከል አንዱ ነበር።

BBC Amharic

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *