“Our true nationality is mankind.”H.G.

ከቡራዩ ብኋላ…

የአቶ ለማ መገርሳን ቡድን አይነት ሰፊና እውነተኛ ህዝባው ድጋፍ ያለው አመራር በሃገራችን ታሪክ ላለፉት አርባ አመታት ታይቶ አይታወቅም ። ለምን እንደዚህ ሆነ ለሚለው የተለያዩ ምክንያቶች ሊቀርቡ ይችላሉ ዋናው ግን በጎሳ ተበጣጥሳ ጫፍ  የደረሰችው  ሀገራችን  መጨረሻዋ  እንደማያምር      ተገንዝበው  ከእነ ልይነታችን በእኩልነት ለሁሉም የምትሆን ኢትዮጵያን መገንባት እንችላለን ብቸኛው አማራጭም እሱ ነው ስላሉ ነው. ይህም ሆኖ ግን ጥቅማቸው የጎደላባቸው (ምንም እንኳን ከእነ ሙሉ ወንጀላቸውና የዘረፉት ንብረት ምህረት ቢደረግላቸውም ) ህወሃቶቸና ለውጡ እነሱ ብቻ በፈለጉት  ጠባብ መንገድ መሄድ አለበት ብለው ከሚታበዩ እክራሪ የኦሮሞ ልሂቃን የማያቋርጥ ተቃውሞ ገና ከለውጡ መባቻ ጀምሮ ገጥሞታል. አሁን እየተካሄደ ያለው በአንድም ሆነ በሌላ በኩል የዚህ ቀጥይ ክፍል ነው። ምናልባት አንድ የተለየ ነገር ቢኖር የግንቦት ሰባት ወደ ሃገር ቤት መመለስና  ህዝቡም ያሳየው  ድጋፍ  የፈጠረው መደናገጥ ነው።

ህወሃትና ሌሎች አክራሪ ብሄርተኞች ግንቦት ሰባትን በስም  ብቻ የሚኖር ምንም ድጋፍ የሌለው አድርገው ነበር  የሚመለከቱት.  ለአቀባበላቸው  የተደረገው  ነገርና ለህዝቡ እያቀረቡ ያሉት ሃሳብ ግን አስደንግጧቸዋል

። አሁንም ግን መገንዘብ ያቃታቸው ያሁሉ ለግንቦት ሰባት አቀባበል የወጣ በሙሉ የግንቦት ሰባት ደጋፊ ሳይሆን ኢትዮጵያውነትን ደግፎ የወጣ ነው. ሃገራችንን ለ 27 ዓመታት  ቁልቁለት የወሰዳት ደርጅት ውስጥ እስከ ሚኒስተርነት ያገለገለውን አብይን የደገፈውም ለዚህ ነው። አዲስ አበባ ደግሞ ለጎሰኞች እንደማትመች ደግማ ደጋግማ አሳይታለች። አዲስ አበባ ራሷ ኢትዮጵያ ናት። ባለፉት ሶስት አመታት አገሪቱ ከእያቅጣጫው ስትናጥ ምንም ያላልቸው ሸገር የለማ ቡድን ኢትዮጵያዊነትን ሲያነሳ ቀድማ ተሰለፈች። ልቧን መግዛት ያልቻሉ ጎሰኞች ግን መንገድና አጥርን ቀለም በመቅባት ሊያሸማቅቋት ሞከሩ።

የዳው  ኢብሳው   ኦነግ  ከግንቦት  ሰባት  በፊት  ቢመጣ   ኖሮ     የዚህን   የሩብ   ሩብ   እንኳን አቀባበል አይደረግለትም ነበር። የጃዋር ቡድንና ምናልባትም ህውሃት ገንዘብ በማቀበል ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመው የአብይን አስተዳደር ቀውስ  ውስጥ  ለመክተት  ጠንከርው እየሰሩ ነው።   አሁን የሚፈለገው አብይን ገፋፍቶ ደጋፊዎቻቸው ላይ የሃይል እርምጃ እንዲወስድና በህዝብ ዘንድ ያለውን ድጋፍ እንዲያጣ ነው. ከዚያ የተለመደችውን የተጎጅነት ቅስቀሳ ይዞ ጉዞ ወደ ስልጣን ማሳደድ። እነ ጃዋር እሰከ አሁንም የታገሱት ያለው ህዝባው ደጋፍ በመፍራትና   ምናልባትም  ህወሃት  ተመልሳ  ልትመጣ  ትችላለች  የሚል ስጋት   ስላላቸው   ነው።   እስከ   አሁን   በነበራቸው ሂሳብ    ለውጡን ያመጣነው እኛ ነን   እንደፈለግን እናድርጋለን የሚል ነበር.  የግንቦት ሰባት መከሰት  ግን  ቢያንስ  የከተማውን ፖለቲካ እንደማያስቀምሳቸው ሲረዱ ወደተለምደው የብጥበጣ ፖለቲካ ዞሩ።

ከቡራዩ የዘር ማጽዳት ዘመቻ ምን ተማርን ?

  1. በብሄር ፖለቲካ በኩል ወደ ዴሞክራሲ የሚውሰ ምንም መንገድ የለም. ሰውን በስሜት ለማሰባሰብና ለማታገል ለጊዜው ቀላሉ መንገድ ሊሆን ይችላል። መጨረሻው ግን አይደለም ለሃገር እወክለዋለሁ ለሚለው ብሄር እንኳን እንደማይጠቅም በዚች አጭር ጊዜ ከበቂ በላይ ምልቶችን አይተናል. የብሄር ፖለቲካ ሰውን ከሰውነት አውርዶ ከእንስሳ ተራ  የሚያሰልፍ  እንደሆነ  በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች ማንነት ላይ ያነጣጠሩ አሰቃቂ ግድያዎች ቁልጭ አድርገው አሳይተውናል.  አጥፊዎች የኔ ብሄር አባል ናቸው ብሎ ያሰበ ብሄርተኛ ምን ያክል ቢማር ፣ ቢያቅውና ቢሸመግል  በንጽሃን ላይ የሚደርስን ጥቃት የማውገዝ  ወኔ እንደማይኖረው ደግመን ደጋርመን አይተናል። መዲናችን ውስጥ ብዙ የአይን እማኞችና የምስል  ማስረጃ ያለውን ጉዳይ አንዳንድ  ወገኖቻችን  የሌለ ነገር ላይ ለመለጠፍ ሲሞክሩ ስታይ  በብሄርተኝነት በኩል  አይደለም እኩልነትና ፍትህ  ሰባዊነትም አይኖርም። ይሄ ሁሉ ብሄርን መሰርት ያደረገ ጥቃት ከግለሰቦች አልፎ የ ሃገርን ህልውና አደጋ ውስጥ እያስገባ አሁንም የብሄር ፖለቲካ ላይ የሙጥኝ ማለት የረጅም ጊዜ አላማው ሃገርን ማፍረስ ካልሆነ  እንቆቅልሽ  ነው።   የህዝቡ  ለአመታት የቆየ የአብሮነት በሃል ነው እንጅ ያተረፈን ከዚህም የባስ እንዲሆን አሁንም ፍላጎት አለ።
  2. የጸጥታ አስከባሪዎች አደረጃጀትና የመንግስት ሃላፊነት

በተለያዩ ማንነት ተኮር ጥቃቶች  ጋር በተያያዘ ደጋግመን ያየነው የክልል የጸጥታ አስከባሪዎች ዋና ተዋናዮቸ እንደነበሩ ነው።  ይሄም ብሄርተኝነት የሚያስከትለው ‘እኛ’ እና ‘እነሱ’ የሚል አመለካከት ነው።    የቡራዩ የዘር ማጽዳት ወንጀል  ውስጥ መለዩአቸውን እንኳን ለመቀየር ያልሞከሩ ፖሊሲች የድርጊቱ ተካፋይ ነበሩ። መቀሌ ለተደበቁ ሌቦችና አብዲ ኢሌን ለመያዝ የተከፈለው መስዋትነት የክልል ፖሊሶች ከፌደራል መንግስት ቁጥጥር ውጭ መሆን ውጤት ነው። ፖለቲካውን ከብሄር  ለማጽዳት   ብዙ  ጊዜ  የሚጠይቅ  ስራ  ነው። ለጊዜው  ግን  ቅድሚያ   ሊሰጥው  የሚገባ  የዜጎችን  ደህንነት  ማስጠበቅ  ነው።   ለዚህም  የክልል  የጸጥታ መዋቅርን በፌደራል መንግስት ስር አድርጎ ልክ እንደ መከላክያ ሰራዊቱ ህብረብሄራዊ መልክ እንዲይዝ ማድረግ ያስፈልጋል። ከፖለቲካ ሳይሆን ከብሄር አድሎ ያልጸዳ የጸጥታ መዋቅር በጣም አደገኛ ነው።

መንግስት  ከድርጊት  ፈጻሚዎች  ባልተናነሰ  አቀናባሪዎች  ላይ  ጠንካራ  እርምጃ  ካልወሰደ  ከዘመናት በኋላ የተገኘን ድጋፍ ባገኘበት ፍጥነት ሊያጣው እንደሚችል ከቡራዩ በኋላ በህዝቡ ላይ የተፈጠረው ስሜት ግልጽ አድርጓል።   የቡራዩ ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት አይደለም በጸጥታ ስራ ላይ የተሰማሩ የመንግስት አካላት ይቅርና ተራው ዜጋ እንኳን ስጋቱ እንዳለ እያስጠነቀቀ ነበር።    ይህን አፍንጫቸው ስር የተከሰተ ዘግናኝ ጭፍጨፋ አለመመከት ለህዝቡ የሚያስተላልፈው  መልክት በቀላል የሚታይ አይደለም. ህዝቡ ህግ አስከባሪ ሲጠፋ ህጉን ወደ ራሱ ይወስዳል. ከዘራፊዎችና አረመኔዎች ራሱን ለመጠበቅ መደራጀት ጀምሯል።

  1. አዲስ አበቤ ከእንቅልፉ ነቃ

የአዲስ አበባ ህዝብ በጽንፈኛ የኦሮሞ ብሄርተኞች መጤና ሰፋሪ እየተባለ ለዓመታት ያለማቋረጥ የዘረኝነት ቅስቀሳ ሲካሄድበት በንቀት አልፎት ነበር። ዜጎች በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች በማንነታቸው ምክንያት ሲፈናቀሉም ከማዘን ያለፈ ምንም ማድረግ አልቻለም ነበር።   አሁን በራቸው ላይ የተካሄደው አረመኔያው ግድያ ዝርፊያና ውድመት ከፈተኛ የህልውና ጥያቄ እንዲነሳ አስገድዷል. በዚህም ምክንያት የተጎዱ ወገኖችን ከመርዳት ጎን ለጎን በእየ አከባቢው እንዴት መደራጀት እንዳለበት ከመነጋገ አልፎ በተለያዩ ቡድኖች የመደራጀት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። ብሄርተኞች ምን ያክል በጥፋት መንገድ ሊሄዱ እንደሚችሉ ከምንጊዜውም በላይ ግልጽ ሆኗል. እንደ ወያኔ አለሳልሰው በዱልዱም ከሚያርዱን   እንደዚህ   ቀድመው ማንነታቸው  ካሳዩን   የመዘናጊያ   ጊዜ አይኖርም። ይህ እንቅስቃሴ ያስፈራቸው ብሄርተኞች ከ አሁኑ ለማሸማቀቅ ወጣቱን እያፈሱ ማሰረር ጀምረዋል. ጥረቱን ያረዝመው ይሆናል እንጅ አያቆመውም።

  1. ግንቦት ሰባት በጎሰኞች ጥርስ ውስጥ

ግንቦት ሰባት እስከ አሁን እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ አንድ በሰለጠነ ፖለቲካ ከሚያምን ቡድን የሚጠበቅ ነው።   ያም ሆኖ ግን  ብቸኛ ተፎካካሪ  ይሆና  በሚል  ብቻ ምንም አይነት ግንኙነት በሌላቸው ጉዳዮች በሙሉ ግንቦት ሰባት አለበት ለማለት ከእየ አቅጣጫው እየተሮጠ ነው። አንዳንድ አባላቶቹም እንደታሰሩ ተሰምቷል። ብሄርተኞች የኢትዮጵያን ስም የጠራ በሙሉ እንደ ጠላት ከመፈረጅ አይመለሱም። ምንም እንኳን ለውጡ እንዳይደናቀፍ ነገሮችን በጥንቃቄ መያዛቸው ጥሩ ቢሆንም እንደ ብቸኛ የዜግነት ፖላቲካ አራማጅ ድርጅት  የሚያምኑባቸውን ጉዳዮች ጠንከርና ግልጽ አድርገው ማቅረብ አለባቸው።   የእነሱ ያልሆኑ ሃሳቦች በእነሱ ላይ   ሲጫን በዝምታ ማለፍ ሃሳቡን እንደመቀበል ይቆጠራል. ለምሳሌ በፌደራሊዝም እንደማያምኑና አህዳዊ ስርዓት ለመመስረት እንደሚታገሉና በአሁኑ ውቅት የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም  እንደሚፈልጉ  የሚነገረውን  ውሽት  መጥቅስ  ይቻላል።    ብሄርተኞችን መለማመጥ ሳይሆን የራስን ደጋፊዎችን ማጠናከረ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። አሁን ጭራሽ በመፈንቅለ መንግስትም እንደሚጠረጠሩ ማስወራት ተጀምሯ።  በአሁነ ሰዓት መፈንቅለ መንግስት ተሞክሯል ቢባል እንኳን ግንቦት ሰባት የመጨረሻው ተጠርጣሪ  ነው የሚሆነው። መልክቱ ግን ግልጽ ነው. ግንቦት ሰባትን አዲስ  አበባ  ውስጥ  በምርጫ  ማሽነፍ   ለብሄርተኞች   ከባድ እንደሆነ ገብቷቸዋል ስለዚህ ከዚያ በፊት እንደምንም ብሎ ማባረር ነው።

  1. አሁንም አብን መደገፍ ያስፈልጋል

ነግሮች በፍጥነት እየተለዋወጡ ነው. የቡራዩ ፍጅትና በአዲስ አበባ የቀጠለው የወጣቶች አፈሳ አብዛኛውን የአብይ ደጋፊ ግራ አጋብቷል። የ አሜሪካ ኢምባሲ የስጋት መግለጫ፤ የፖሊስ ያልተጠራን ሰልፍ እንዳትውጡ ብሎ መናገር ፤ የቡራዩን ፍጅት ለመሸፋፈን እየተሄደበት ያለው እርቀት፤ የአዲስ አበብ ወጣቶችን በጅምላ ማፈስና አሁን ደግሞ የመፈንቅለ መንግስት ወሬ። እነዚህ ነገሮች ሲደማመሩ ወደ ተሻለ መረጋጋት እያመራ

የነበረው የአብይ  አስተዳደር በአዲስ መልክ ጫና እየተፈጠረበት እንዳለ ያሳያል።  ህወሃትና አክራሪ አሮሞ ብሄርተኞች የአብይን ቡድን ከደጋፊዎቻቸው ጋር ለማጋጨትና ድጋፋቸውን ላማሳጣት እየተሞከረ ነው. በቅርቡ ከሚካሄደው የኢህአዴግ ጉባኤ በፊት ተመሳሳይ ሙከራዎች በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ሊካሄዱ እንደሚችሉ ም ከልምድ እንዳየነው መገመት ይቻላል።    እነ አብይ ይዘውት   የመጡት የለውጥ መንገድ የተሻለ እንደሆነ ገና ስልጣን እንኳን ያልያዙ ተቀናቅኞቻቸው የሚያደርጉትን ማየት ከበቂ በላይ ነው።  በእነሱ ተስፋ ከመቁረጥና ህወሃትን ጨምሮ ለሌሎች አክራሪ ብሄርተኞች በር ከመክፈት ይልቅ ስህተቶችን እየነቀፉ ራስን ለመከላከል ከመንደር እስክ ፓርቲ ድረስ እየተደራጁ የእነ አብይን የለውጥ መንገድ መደገፍ ያሰፈልጋል።

ማጠቃለያ

የጎሰኝነት ፖለቲካ ሊያመጣቸው ይችላሉ የተባሉትን አደጋዎች አንድ በአንድ እያየናቸው ነው. ከዚህም የባሰ ሊከስት እንደሚችል ለመገምት አያዳግትም. ምንም ያክል ጥሩ መሪ ብናገኝ እንኳን ህገመንግስታዊ ማዕቀፍ የተሰጠው የጎሳ ፖለቲካ ለህዝባችንና ለሃገራችን ትልቅ አደጋ ሆኖ ይቀጥላል. ዋናው መፍትሄ ህገመንግስቱን በዜግነት ፖለቲካ መቅረጽ ቢሆንም ለጊዜው ግን ራሳቸውን እንደቻሉ ሃገራት እየሆኑ ያሉ ክልሎችን አቅም ቀስበቀስ መቀነስና የፌደራል መንግስቱን ማጠናከር. ከዚያም ወደ ፕሬዝደንታዊ የአስተዳደር መቀየር።

በበቀለ ደገፋ (bekeledegefa5@gmail.com)

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሕዝብን ማን ይሰራዋል?
0Shares
0