“Our true nationality is mankind.”H.G.

የኦሮሞ ድርጅቶች ኢሳትን ብሄርን ከብሄር በማጋጨት ወንጀል ከሰሱ፣ጸብን ሲዘራ የኖረው የጃዋር ኦ ኤም ኤን አልተካተተም!!

በኦሮሚያ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች በሕብረት ያወጡት መግለጫ አነጋጋሪ ሆኗል። በዚሁ አዲስ አበባ ላይ ተንጠልጥሎ የተሰጠው መግለጫ እጅግ በርካታ በጎ ነገሮችን ያካተተ ቢሆንም ስሜትን የሚቀሰቅስ ሰበዝ ጉዳይም አለበት። ከኢሳት በስተቀር የሌሎችን ስም ሳይጠቅሱ ሚዲያዎችን መክሰሳቸው፣ አንዳንድ ሚዲያዎች ሊወገዙ ቢገባም ክሱ የጃዋርን ኦ ኤም ኤን አለማካተቱ መግለጫውን ሰባራ እንደሚያደርገው እየተገለጸ ነው።

አዲስ አበባን ኦሮሞዎች በወረራ እንደተነጠቁ ያወሳው መግለጫ መነሻው በቡራዩ የተካሄደውን አውሬነት የተሞላው ክፉ ድርጊት ለመኮነንና፣ በአገሪቱ እየተስፋፋ የመጣውን የብሄር ግጭት ለማውገዝ በመሆኑ የሁሉንም ዜጋ ቀልብ ሊስብ ችሏል። በዚሁ መነሻ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ንብረት መሆኗ ሊስተባበል የማይችል፣ ለድርድር የማይቀርብ ሃቅ እንደሆነ አጉልቶ፣ ከተማዋ የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች መኖሪያ ከመሆኗ አንፃር በውስጧ የሚኖሩ ሁሉ የግልም ሆነ የቡድን መብት ያለአንዳች መሸራረፍ እንዲጠበቅ ለማድረግ ድርጅቶቹ የበኩላቸውን እንደሚወጡም አመልክተዋል። 

ድርጅቶች የአዲስ አበባ የባለቤትነት መብት ላይ ተተክለው፣ ለመብት መከበር ዘርን ሳይለዩ እንደሚሰሩ መናገራቸው ግን መግለጫውን ተከትሎ ነቀፌታ እንዲሰነዘርባቸው ሆኗል። ከአምስት ሚሊዮን ሕዝብ በላይ አጭቃ የያዘችው አዲስ አበባ የራሷን ከንቲባና አስተዳደር የመሰየም ባለ ሙሉ መብት የፌደራል ከተማ ሆና ሳለ ድርጅቶቹ ባለቤትነት ላይ ቆመውና ጸንተው ለሌሎች መብት እንደሚሰሩ ማወጃቸው ብዙም አልተወደደላቸውም።

ኦሮሚያ ላይ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች አዲስ አበባ ላይ የያዙት የጀብደኝነት አቋም ብዙም እንደማያስኬዳቸውና ይልቁኑም ወደሚፈለገው የመቻቻል ሃሳብ እንደማያመራቸው ግንዛቤ አለመውሰዳቸው ጥቂት የማይባሉ ዜጎችን አሳዝኗል። በተለይም አገርን ይመራሉ፣ ያረጋጋሉ፣ ለሃላፊነት ይበቃሉ የተባሉ ጉምቱ ፖለቲከኞች በእዚህ ትርምስ ወቅት ጃዋር መሐመድን ሆነው መታየታቸው ሃዘኑንን ከረር አድርጎታል። የተሰጠውን መግለጫ በስጋት የማየቱን ጉዳይ እንዲያጎላው አድርጎታል።

አዲስ አበባ ላይ ጥቅም መጠየቅ አግባብ ሆኖ ሳለ፣ የአዲስ አበባ ባለቤት ነን በሚል ሌሎች በከተማዋ እንዲኖሩ ፈቃጅና ከልካይ መስሎ መቅረቡ ምን አልባትም እናከብረዋለን የሚሉትን፣ ከተነካ በኦሮሞ ህልውና ላይ የተቃጣ አደጋ ተደርጎ የመውሰድ ያህል የሚምሉበትን ህገ መንግስት በደቦ የመናድ ያህል አድርገው የወሰዱ አሉ።

አዲስ አበባ የፌደራል ዋና ከተማ ሆና፣ በራስዋ መሪዎቿን የምትሰይም፣ የዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ከተማ ሆና ሳለ፣ ልዩ ጥቅምን በድርድር መጠየቅ እየተቻለ ድርጅቶቹ በዚህ ደረጃ ቀረርቶ ማሰማታቸው ሌሎችን የሚያነቃና እምነታቸውን የሚሸረሽር እንደሆነ አስተያየት የሰጡ በርካታ ናቸው። ይህ አካሄድ ምን አልባትም ወደፊት ይደረጋል በተባለው ፍትሃዊ ምርጫ አዲስ አበባ ላይ ሊመዘግብ የሚችለውን ውጤት አምኖ ያለመቀበል ምልክትም ተደርጎ ሊታይ እንደሚችል ፍርሃቻቸውንም የሚገልጹ አሉ።

መግለጫው በቡራዩ የተፈጸመውን እጅግ የሚዘገንን ተግባር ሲኮንን በቪዲዮ የታዩትን የኦሮሚያ ፖሊስ አባላትን፣ የጸጥታ ሃላፊዎችን፣ ሰለባዎች በግልጽ የተናገሩትን ከግምት በማስገባት አፉን ሞልቶ አላወገዘም። በህግ እንዲጠየቁ በስም ጠርቶ አልኮነናቸውም። ይልቁኑም ትኩረት የሰጠው ሙያዊ ግዴታቸውን አልተወጡም ሚዲያዎችን በማውገዝ ነው።

“አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ከሙያ ስነ ምግባሩ ያፈነገጠ እና ሚዛናዊነት በጎደለው መልኩ እየዘገቡ ነው” የሚለው የፓርቲዎቹ በመግለጫ፣ኢሳትን ስም ጠርቶ ሲያወግዝ አቶ ጃዋር መሐመድ የሚመሩት የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ዎርክ በዚህ ጉዳይ ከደሙ የጸዳ ማድረጉ የድርጅቶቹን ወገንተኛነት ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል። ኢሳትን ላይ ያነጣጠረው መግለጫ ሌሎች ሚዲያዎች በሃላፊነት እንዲዘግቡ ማሳሰቡና በታሪክና በህግ ሊጠየቁ እንደሚገባ ማስታወሱ አግባብ ቢሆንም በዚህ ተግባር ግንባር ቀደም ተከሳሽ ከሚሆኑት መካከል አቶ ጃዋር መሐመድና ባልደረቦቻቸው መሆናቸውን አላማንሳቱ አግባብ ተደርጎ አልተወሰደም።

ኢሳትን ጨመሮ የተለያዩ መገናኛዎችን በመረጃ ከተደገፈ በስም ጠቅሶ ማሳጣትና በህግ እንዲጠየቁ ማድረግ ሃላፊነት የሚሰማው አካሄድ ሆኖ ሳለ፣ አቶ ጃዋር መሐመድ የሚመሩት ሚዲያ ትናንትም ሆነ ዛሬ የሚያቀርባቸው ዝግጅቶች ከሌሎች የተሻሉ፣ ሙያን ያከበሩ፣ ፍቅርና ሰላምን የሚስብኩ፣ ልዩነትን በሰለጠነ መንገድ የሚያራምዱ፣ የተገኘውን ለውጥ ወደ አንድ ጥግ የማይጎትቱ፣ ለሁሉም ብሄሮች እኩል ሚዛን ያላቸው ተደርጎ ከተወሰደ ይህ አካሄድ በራሱ አደጋ ያለው ነውና ድርጅቶቹ ሊመረምሩት የሚገባ እንደሆነ ያሳሰቡም አሉ።

በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት ተግተው እየሰሩ ነው” ሲል በደፈናው የሚወነጅለው መግለጫ” መገናኛ ብዙሃኑ በህግም በታሪክም ፊት ተጠያቂ መሆናቸውን አውቀው ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ” ሲል ማሳሰቡ ከላይ እንደተባለው የግልጽነት ጥያቄ ከማንሳቱ በስተቀር ጥፋት ግን የለበትም። በስመ ሚዲያ ለዜና ማጀቢያ የማይሆኑ ምስሎችን ከመጠቀም አንስቶ፣ የተገኘውን ሁሉ በማግበስበስ ህዝብ ከህዝብ ጋር እንዲባላ የሚያደርጉ መረጃዎችን የሚያሰራጩ ሚዲያዎች መኖራቸው ሃቅ ነው።

ለመከረኛ ሳንቲም ለቀማ ሲባል ፊደል እንኳን ሳይለቀም፣ እውነትነቱ ሳይጣራ፣ የወሬው ዓላማ አስፈላጊነት ሳይታይ፣ አንዳንዴ እነማን ለምን ዓላማ እንዳሰራጩት እየታወቀም ቢሆን ሃላፊነት የመውሰድ ችግር የሚታይባቸው ሚዲያዎች አሉ። አብዛኛው አንባቢውም ከበሰለው እና እውነት ላይ ከተመረኮዘው ይልቅ በጅምላ በተግበሰበሰ መረጃ የሚረካ በመሆኑ፣ አንዳንዴም ሳያነብና፣ ሳይረዳና ሳይሰማ ላማሰራጨት የሚተጋ መሆኑ የችግሩን አሳሳቢነት ያጎላዋል። 

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ቻይና በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት የሚካሄደውን የህዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር እንደምትደግፍ ገለጸች
0Shares
0