ለሱዳን በተሰጠው መሬት ላይ እጀዎት አለበት እየተባለ የሚነሳው ሀሳብ ምን ያክል እውነታ አለው? ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ የብአዴን ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን ምላሽ ሰጡ፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን ‹‹ብዙዎቹ እንዲህ አይነት ቅሬታ ሲመጣ ለምን ግልጽ አላደረገም ምላሽስ ለምን አልሰጠም የሚሉ ሀሳቦችን ሲሰጡ ሰምቻለው፡፡ በዚህ ላይ ግልጽ ማድረጉ ጠቃሚ ነው ብየ አስባለሁ፡፡
ከሱዳን ጋር የሚያዋስነው ድንበርን በተመለከተ ከሚኒሊክ ጀምሮ ሲሰራ የቆየ አካሄድ አለ፤ ይሁን እንጅ ከሚነሳብኝ ቅሬታ አንፃር በወቅቱ ጉዳዩ ሲፈጸም እኔ የነበርኩት እንግሊዝ ሀገር ነው፡፡

ብዙ ጊዜ ሲወራ የምሰማው ደመቀ ለሱዳን መሬት ሰጥቶ ከፍተኛ ሹመት አገኘ የሚል ነው ፤እውነታው ግን እኔ በክልሉ ከፍተኛ የስልጣን እርክን ባገለገልኩበት 14 ዓመታት ያክል ባስመዘገብኩት ከፍተኛ ውጤት ተንተርሶ ድርጅቴ ነው ለከፍተኛ የስልጣን እርክን እንድደርስ ድምጽ የሰጠኝ፡፡በወቅቱ የተሰጠኝን የፌዴራል ስልጣን ለኔ አይገባም ሌሎች ቢሆኑ የሚል ሀሳብ ባቀርብም ድርጅቱ በአብላጫ ድምጽ ይህን ኃላፊነት እንድወጣ ስለጠየቀኝ ብቻ ኃላፊነቱን ለመወጣት ስል ነው የተቀበልኩት እንጅ እንደሚወራው አይደለም›› ብለዋል፡፡

‹‹ምንም እውነታ የሌለው የተቀነባበረ የስም ማጥፋት ዘመቻ ነው የተፈጸመብኝ፡፡ይህ ሆን ተብሎ አንገቴን እንድደፋ እና አመራርነቴም ተቀባይነትን እንዳያገኝ የተደረገ ሴራ ነው፡፡››
በኔ በኩል ጉድለት የምለው ድርጅቱን እየመራሁ መሬት ላይ የተፈጸመውን ስህተት አለማወቄ ነው፡፡ አንድም መሬት አልተሰጠም እየተባለ የተካሄደው የድንቁርና አካሄድ እኔም ድርጅቱም ልንማርበት የሚገባ ነው፡፡ በእርግጥ ስለስም ማጥፋቱ በተወሰነ መጠን በብአዴን ስብሰባ ላይ የተነገረ ቢሆንም የሚያዳምጥ ግን አልነበረም፡፡ አቶ አያሌው ጎበዜ በወቅቱ ርዕሰ መስተዳድር በሆኑበት ወቅት በእኔ ተፈርሞ ለሱዳን የተሰጠ መሬት እንደሌለ ግልጽ አድርገውም ነበር፡፡

በወቅቱ በስራ ላይ የሌሉ መሪዎችን በሀሰት ወሬ መቀባት ድርጅትንም ይጎዳል፤ ተቀባይነትንም ያሳጣል፤ ከዚህም ልንማርበት ይገባል፡፡ የእኛ አመራርነት ጎልቶ እንዳይወጣ ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች ተጠቅመውበታል ነው ያሉት፡፡

አለአግባብ ለሱዳን የተሰጠውም መሬት ተገቢ አይደለም የሚል አቋም ነው ያለን፤ ወደፊትም ማስተካከያ እንዲወሰድበት እየተሰራም ነው ፡፡ የተፈረመ ካለም መስተካካል አለበት የሚል አቋም ይዘን እየሰራን ነው፤ ጉዳዩ በፌደራል እንዲታይም ከፍተኛ ጥረት እያደረግን ነው ብለዋል የብአዴን ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን፡፡ 

አማራ ማስ ሚዲያ
ዘጋቢ፡-ምስጋናው ብርሀኔ 

የአቶ ደመቀን ገለጻ በቪዲዮና አውዲዮ ስር ያድምጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *