‹‹ዘርና ቋንቋ ላይ የተመሰረተ ፌዴራሊዝም አይጠቀምም ፤ ፍጅት ላይ ወድቀናል፤ልዮነቶቻችንን አስፍቶ ኢትዮጵያዊነታችንን አላልቶታል፡፡ ››
‹‹ፖለቲከኞች በስሜት እየተናጡ ህዝብ ጋር እንደጎርፍ ገብቶ መዋጥ የለባቸውም፡፡ ሀዲድ ሳይሰራ ባቡር እንደመንዳት ነው፡፡››
‹‹ጠንካራ የሆነ አንድ ፓርቲ ሊመሰረት ይገባል፡፡››
ባሕር ዳር ላይ በተካሄደው የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት ፓርቲዎቹ ያነሷቸው ነጥቦች፡፡
11 የፖለቲካ ፓርቲዎች ‹‹የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና›› በሚለው መሪ ሀሳብ መወያያ ላይ በቀረቡ ሁለት ጥናታዊ ፅሑፍ መነሻነት ያነሷቸው ሀሳቦች፡-

• አሁን ያለው ዴሞክራሲ በስልጣን ላይ ባሉት ሰዎች ተለክቶ የሚታደል በረከት ነው፡፡ ብአዴንም የተለካለትን ዳና ብቻ እየተከተለ ነው፡፡
• ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ውስጥ በብሄር እና ብሄረሰብ ላይ የተመሰረተውን አንድነት መልሶ እንዲሸረሸር አድርጎታል፡፡
• ብአዴንም የአማራውን ህዝብ ጥያቄ በትክክል አልመለሰም፡፡ ህዝቡ አንገቱን ደፍቷል፡፡
• የአማራ ህዝብ የሚፈልገው ኢትዮጵያዊ አንድነት ላይ የተመሰረተ የጋራ መልማት እና ፍትሐዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታን ነው፡፡
• የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዛት መልሶ እየከሰመ የሚሂደው በህግ ማዕቀፍ የሚተዳደር ፤ ሀሳብ ያለው ድርጅቶች ነን ወይ የሚለውን እራስን ማየት ስንችል የሚመለስ ነው፡፡
• በክልሉ ውስጥ እኩል የመልማት አካሄድ የለም፡፡ የአገው ህዝቦች ታሪክ በድህነት ተሸፍኖ እንዲሄድ እየተደረገ ነው፡፡ እኩል ማድመጥ የለም፡፡ አብሮ ለመዝለቅ በክልሉ ያሉ ህዝቦች አንድነት እንዲጠናከር ከመስራት ይልቅ ማግለል አለ፡፡
• ዘርና ቋንቋ ላይ የተመሰረተ ፌዴራሊዝም አይጠቀምም ፤ ፍጅት ላይ ወድቀናል፤ልዮነቶቻችንን አስፍቶ ኢትዮጵያዊነታችንን አላልቷል፡፡
• አማራው ስትራቴጂክ በሆነ ስልት እኔ ካልመራሁ ከሚል ሃሳብ ወጥቶ በፌዴራል ደረጃ የሚወክል ጠንካራ ፓርቲ መመስረት ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ 
• ለውጥ ባለበት ዘመን እንኳ በርካታ ለመብት የተሞገቱ የአማራ ዜጎች በተለያዩ ክልሎች ታስረዋል፡፡
• የአማራው ጥያቄ በመሬቱ ወጣቱ ባለቤት ያለመሆን ነው፡፡ ህዝቡ ታክቲካዊ በሆነ የገበያ ጭቆና ውስጥ ገብቷል፡፡ 
• ፖለቲከኞች በስሜት እየተናጡ ህዝብ ጋር እንደጎርፍ ገብቶ መዋጥ የለባቸውም፡፡ ሀዲድ ሳይሰራ ባቡር እንደመንዳት ነው፡፡
• ከባለፈው ይልቅ አሁን ለአማራው ህልውና ከባድ ሁኗል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊያስማሙን በሚችሉ ጉዳዮች ላይ በመግባባት የአማራውን ህዝብ ጥያቄ መመለስ ይኖርብናል፡፡ 
• ለኢትዮጵያዊነት ሲባል የተጀመረውን ለውጥ በማበረታታት በአማራ ስም የተቋቋሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደምረው ጠንካራ ፓርቲዎችን መመስረት አለባቸው፡፡ 
• የአማራ ህዝብ ብቻ ለሁሉም፤ ሌላው ደግሞ ለራሱ ብቻ በሆነ ቁጥር የአማራ ህዝብ ባለቤት አጥቷል፤ መልማትም አልቻለም፡፡ 
• የአማራ ህዝብ ወደፊት ስለሚኖረው ልማት ብቻ እያሰበ እንዲኖር ሁኗል፡፡ አዲስ የድርድር ውጤት የሆነ ሀገራዊ አንድነትን መገንባት ይኖርብናል፡፡ 
• አንድ ሰው እግሩን እሾህ ወግቶት ጉንጩን ቢሳም ሊድን አይችልም፡፡ የአማራው ጥያቄ አሁንም በደንብ መታየት አለበት፡፡
• ማንኛውንም የአማራውን ጥያቄ መመለስ ካስፈለገ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመንግስት ጋር በመሆን የህዝቡን ጥቅም ሊያስከብሩ የሚገባ ተጠያቂነት ያላቸው አሰራሮችን መፈራረም ይገባቸዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምክንያት ላይ የተመሰረተ ክርክር ማጎልበት የሚያመጣውን ተጠቃሚነት በማመን ሊጠናከሩ ይገባል፡፡
• አማራ ተደራጅቶ ውጤታማ እንዲሆን በአማራ ክልል ውስጥ ያሉ ብሄረሰቦች ጋር ያለን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማጠናከር አለበት፡፡
• የአማራ ፖለቲካ ፓርቲዎች የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ እና አንድ ይሁንታ ያለው ድምፅ ለማግኘት ወደተጠናከሩ ፓርቲዎች መደመር አለባቸው፡፡ 
• አማራው በስነ ልቦናው ተለያይቷል ፤ ይህንን ለማቀራረብ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊ በሆነ መንገድ በአንድነት መስራት ይኖርብናል፡፡
ዘጋቢ፡-ግርማ ተጫነ

ባሕር ዳር – (አብመድ)

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *