በመጪው የኢትዮጵያ ዓመት – በ2012 ኢትዮጵያ መደበኛ አገር ዐቀፍ የሕዝብ እንደራሴዎች ምርጫ ታካሒዳለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ምርጫውን አጓጊ የሚያደርገው ላለፉት አራት ዓመታት ኢትዮጵያን ሲንጣት ከቆየው ሕዝባዊ አመፅ ቀጥሎ መምጣቱ ብቻ ሳይሆን፣

ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ተለውጫለሁ ባለበት – ነገር ግን ውስጥ ውስጡን በተከፋፈለበት፣ በሽብርተኝነት ሳይቀር ተፈርጀው የነበሩ ድርጅቶች ወደ ፉክክሩ የገቡበት ወቅት መሆኑ ነው፡፡ ምርጫው ምናልባትም ከምርጫ 1997 ወዲህ ከፍተኛ ፉክክር የሚኖርበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 

በዚህ ምርጫ ጉዳይ የተለያዩ የፖለቲካ ተዋናዮች ገና ካሁኑ የተከፋፈለ አቋም ወስደዋል፡፡ ዋና ዋናዎቹን በሁለት ከፍለን መመልከት እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው ነጻ፣ ገለልተኛ እና ተአማኒነት ያለው ምርጫ ይደረግ እና «ይዋጣልን» የሚሉት ቡድኖች/ግለሰቦች ስብስብ ሲሆን፣ «የለም! አሁን ባለው ሁኔታ የምርጫ ፉክክር ማድረግ አንችልም፤ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳው ይራዘም» የሚሉት ቡድኖች/ግለሰቦች ስብስብ ሌላኛው ነው፡፡ በርግጥ፣ «መደበኛ ምርጫ ለማካሔድ ቅቡልነት ያለው አካል የለም፤ አሁን የሚያስፈልገን ሁሉን አሳታፊ የሽግግር መንግሥት መመሥረት ነው» የሚሉም አሉ፡፡ ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ሊያናግሩ በሔዱበት ወቅት «እኔ አሸጋግራችኋለሁ» የሚል ቁርጥ ያለ መልስ በመስጠታቸው የዚህ ጥያቄ አቅራቢዎች ቁጥር ቀንሷል፡፡

«ይዋጣልን» ባዮች
ምርጫው በጊዜ ሰሌዳው ተካሒዶ አሸናፊው አካል መንግሥት እንዲመሠርት የሚጠይቁት የፖለቲካ ቡድኖች፣ ምርጫው ከተራዘመ ሥልጣን ላይ ላለው አካል የመበላሸት ዕድል ይሰጠዋል የሚል ስጋት ያለባቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን ዋናው ስጋታቸው ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የፖለቲካ ስርዓቱ፣ የመንግሥት መዋቅሩ እና ሁሉም ነገር እንዲቀየርም አይፈልጉም፡፡ «ወቅታዊ ምርጫን ያህል ነገር ከተራዘመ፣ ሕገ መንግሥቱ እንዲሁም ፌዴራላዊ መዋቅሩ ሊነካ የማይችልበት ዕድል የለም» የሚል ፍርሐትም አላቸው፡፡ ይህንን ለማስወገድ አሁን በሚስተዋለው፣ አንፃራዊ ነፃ የፖለቲካ ምኅዳር ምርጫውን ማካሔድን እንደ ብቸኛ አማራጭ አድርገው ያቀርቡታል፡፡ እነዚህኞቹ ቡድኖች «አማራጭ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚያስፈልጋቸው ጤናማ የፖለቲካ ምኅዳር ብቻ ነው» ባይ ናቸው፡፡ «ምኅዳሩ ከተገኘ ቀድሞውኑ የተቋቋሙለትን የፖለቲካ ግብ ይዘው ተወዳድረው ማሸነፍ ይችላሉ» የሚል ጠንካራ እምነት አላቸው፡፡

«ይራዘም» ባዮች
ምርጫው መራዘም አለበት የሚሉት የፖለቲካ ቡድኖች እና ድርጅቶች እንደ ምክንያት የሚያስቀምጡት የአገሪቱን አለመረጋጋት እና የዴሞክራሲ ተቋማትን ነጻ እና ገለልተኛ አለመሆን ነው፡፡ እነዚህኞቹ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ስትዳክርበት ከነበረው የሕዝባዊ አመፅ «ሀንጎቨር» አሁንም መውጣት ስላልቻለች፣ በዚህ ስሜት ውስጥ አገር ዐቀፍ ምርጫ ማካሔድ ተጨማሪ አመፅ መጋበዝ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ነጻ፣ ገለልተኛ እና ተአማኒነት ያለው ምርጫ ለማካሔድ የሚያስፈልጉት ነጻ እና ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማት አለመኖራቸው በምርጫው ሒደት ወይም ውጤት ላይ አለመስማማት ብሎም ቀውስ እንዲመጣ ያደርጋል የሚል ስጋት አላቸው፡፡ «ምርጫው መራዘሙ የዴሞክራሲ ተቋማትን ነጻ እና ገለልተኛ አድርጎ መልሶ ለማዋቀር ጊዜ ይሰጣል» ብለው የሚከራከሩት እነዚህኞቹ ቡድኖች፣ «ሒደቱ ወይም ውጤቱ የሚያጨቃጭቅ እና ወደ ቀውስ የሚያመራ ምርጫ በጊዜው ሰሌዳ መሠረት ከማካሔድ አለማካሔዱ ይጠቅማል» ባይ ናቸው፤ ምክንያቱም በእነርሱ አባባል፣ «አሁን የአገሪቱ ኅልውና አደጋ ላይ ነው»፡፡
የነዚህ ሙግቶች ግንባር ቀደም አራማጆች የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ተቀዳሚ ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ እና የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ናቸው፡፡ ሁለቱ ግለሰቦች ቡድናቸውን ወክለው እና አንዳንዴም የግል አስተያየታቸውን ጨምረው በተናገሩባቸው መድረኮች እነዚህን ተቃራኒ አማራጮቻቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ የሆነ ሆኖ ዋናው ውሳኔ አሁንም በገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ እጅ ነው፡፡ ኢሕአዴግ በሚቀጥለው ሳምንት ለረዥም ጊዜ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውን መደበኛ ጉባዔውን ያደርጋል፡፡ እንደፓርቲ በውስጥ ችግሮች እና መከፋፈል የገጠመው ኢሕአዴግ የድርጅት ችግሮቹን መፍታት ብቻ ሳይሆን እንደዚህ ዓይነት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይም ድርጅታዊ አቋም ማሳለፍ አለበት ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 
ይሁን እንጂ አገር ዐቀፍ ምርጫን የማራዘም ወይም ያለማራዘም ጉዳይ በአንድ የፖለቲካ ድርጅት አቋም ብቻ የሚወሰን ጉዳይ አይደለም፡፡ ሌላው ቀርቶ በሕዝብ እንደራሴዎች ፍላጎትም ቢሆን ይህንን ማድረግ አይቻልም፤ ምክንያቱም የሕዝብ እንደራሴዎችም ቢሆኑ ከተመረጡለት የአገልግሎት ጊዜ በላይ ለመቆየት የመወሰን መብት የላቸውም፡፡ ስለሆነም፣ በጉዳዩ ላይ ድርጅቶቹ የተለያዩ አቋሞችን ቢያሳልፉም ቅሉ፣ ውሳኔው ከመተላለፉ በፊት ሰፊ ሕዝባዊ ውይይት ሊደረግበት ይገባል።

በፈቃዱ ኃይሉ
በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሀፊው እንጂ የዶይቸ ቬለን አቋም አያንጸባርቅም።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ኢትዮጵያና የዓለም ባንክ የ200 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ተፈራረሙ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *