ሰሞኑን ቲያትር በነጻ ነው። ቲያትሩ የማያዝናና ቢሆንም ሕዝብ ተከታትሎታል። ቲያትሩ አሰልቺና ባዶ ውዳሴ የበዛበት፣ እንዲሁም በመላው አገሪቱ ሃፍረት የሚባል ነገር መጥፋቱን ያረጋገጠ ነው። ሁሉም በሚባል ደረጃ አደባባይ ያለውን እውነት ክደው ሲመራረቁና በጭብጨባ ሲደምቁ የሚያሳየው ቲያትር አስገራሚ ነገሩ ዳጎስ ያለ በጀት ማንከቱ ብቻ ነው።

አመራሮቹ፣ ካድሬዎቹ፣ መንጋው፣ ጨዋው ሕዝብ ሁሉም ኢህአዴግ በድርጅት ደረጃ ነቅዞ አፈር መብላቱን ያውቃሉ። መንቀዝ ብቻ ሳይሆን ቀደም ሲል ነበራቸው የሚባለው የ”ዓላማ አንድነት” በግልጽ መወላለቁን ይረዳሉ። ህወሃት አዲስ አበባን ለቆ ትግራይ ተጠቃሏል። ብአዴን ከወትሮው በተለየ ” አማራ ወይም ሞት” በሚል ነጻነቱን አውጇል። ኦሮሚያን የሚመራው ኦህዴድ እየበረረ ያለበት የልዩነት መጠን ማንም የሚያስቆመው ዓይነት አይደለም። ደህዴንም ቢሆን ከለውጥ ሃይሎች ጋር ተስማምቶ አቋሙን አሳይቷል።

እውነታው ይህ ነው። በድርጅት መሪዎችና መንጋ ደጋፊዎች ደረጃ ኦህዴድን ማየት የማይፈልጉ፣ ኦህዴድ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል። “አማራውና ኦሮሞው እንዴት ተግባቡ” ብሎ ሲያለቀስና በእልህ ሲዘት የነበረ ሰው አማራ ክልል ሄዶ ” የህዝቦቹ ቁርኝት እኛው የፈጠርነው ስላልሆነ ልናጠናክረው እንጅ የፖለቲካ ጥቅምን ለማረጋገጥ ሲባል ነካክተን ልናበላሸው አይገባም” ይላል። “ህወሃት በደም የተጨማለቀ ድርጅት ነው። ሰፊውን የኦሮሞ ሕዝብ ጨርሷል” በሚል በገሃድ አቋም ይዞ የታገለ ድርጅት ተወካይ መቀሌ ሄዶ ትግርኛ ለመናገር ሲንተባተብና ” እናነት ጅግኖች ” እያለ ሲያወድስ ስምተናል። ሌላዋም ተነስታ ” የአንበሳውን ድርሻ ለናንት” ስትል ጭብጨባው ቤቱን እስኪያፈርሰው ድረስ ሲጎም ስምተናል።

Related stories   መከላከያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ “ጁንታውን” ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን አስታወቀ! በርካታ በቁጥጥር ስር ውለዋል

ይህ በመለዮ፣ በቀይ ካኔቴራ፣ በቁርጥራጭ ባንዲራዎች፣ በመፈክር የታጀበ የእህት ድርጅቶች ጉባኤ አንዱ ሌላውን እያሞገሰ ዛሬ ባለተራው ደህዴን ደጅ ደርሷል። ድርጅቶቹ በግል ቤታቸው በራቸውን ዘግተው የተወያዩበት አጀንዳ በርካታ ነው። የተነገረንን የአባላት ሹም ሽር ትተን በዋና የፖለቲካ ጉዳዮችና መርህ ዙሪያ የተያዘው አቋም ውጤቱ የሚታወቀው በዋና የኢህአዴግ ስብሰባ በመሆኑ በዝግ ስለተመከረባቸው ጉዳዮች አስተያየት መስጠት አይቻልም።

ያም ሆኖ ግን አንዱ ድርጅት የሌላውን ድርጅት መሪ ለመብላት ብር እየከሰከሰ ባለበት፣ አቋም ተይዞ ኦህዴድ መምራት እንደማይችል  ለምሳየትና ለማሳጣት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በሚቀጣጠልበት፣ በተያዘው የለውጥ ሂደት ያኮረፉ፣ ያዘኑ፣ ቂም የያዙ፣ ጥቅም የነጠፈባቸው፣ የፖለቲካ ቃርሚያ ፍለጋ የሸፍጥ ድራማ እያሴሩ እንደሆነ በግልጽ በሚታወቅበት ሁኔታ ሌላ ካባ ለብሶ መሞጋገሱ ያልወለድኩት ልጄ ቢለኝ አባ አፌን አለው ዳባ ዳባ …. እንዲሉ ነው።

Related stories   ሰበር ዜና – ትህነግ በዲፕሎማሲ ዘመቻ ቀውስ ገጠመው፤ “ በሃሰት መረጃ አሳፈራችሁን ” የቅርብ አጋሮቻቸው

የልብስና የቀለም እንጂ፣ ሌላ መመሳሰል የጠፋበት የኢህአዴግ ህብረት ወዴት እንደሚያመራ በውል ባይታወቅም ወደ ቀድሞ ቅርጹ ይመለሳል የሚል ግምት የለም። አይታሰብም። ምኞትም ካለ ተራ ምኞት ከመሆን የሚዘል አይመስልም። ከምኞት ከዘለለ የሚሆነው አጉል ትርምስ ብቻ ነው።

ይህንን እውነት በመረዳት በፌደራል ደረጃ በፖለቲካው አመራር ላይ እንደ አቅማቸው የሚደርሳቸውን “ኮታ” ተቀብለው ለመኖር በመስማማትና በሰላም ለመኖር፣ ተከባብሮ ለመቀጠል አቋም ለመያዝ የተችገሩ፣ ከመቸገርም በላይ የሚጓጉጣቸው ከክልል ክልል እየተዘዋወሩ መሃላና ውዳሴ ሲያሰሙ መስማትም ሆነ መመልከት ይጠወለውላል።

አስቡት አቶ ጌታቸው ረዳ አማራ ክልል ሄደው እንዴት ነው ስለ አማራው የሚናገሩት። ህወሃት ሲጀመር አቶ ጌታቸውን ባህር ዳር መላኩ ምን ለማለት ነው? አቶ ጌታቸውስ የዛሬ ዓመት ምን ብለው ሲፎክሩ እንደነበር ረስተው ነው?  እንደው ለመሆኑ ምን ዓይነት ሞራል ቢኖራቸው ነው አማራው ፊት ቆመው መናገር የቻሉት?  ለውጡ በተፋፋመበት ወቅት ” አማራና ኦሮሞ እንዴት አንድ ሆነ” ብለው የተራገሙትን እርግማን እንዴት ይረሱታል?

Related stories   መከላከያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ “ጁንታውን” ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን አስታወቀ! በርካታ በቁጥጥር ስር ውለዋል

የኦዴፓ ተወካይ መቀሌ ሄደው ያወረዱት ምስጋናና ውዳሴ ከልብ ነው?  የአማራው ተወካይ ለህወሃት የሰጡት ቡራኬ አሁን ካለው የብአዴን አቋም የተቀዳ ነው? እንዲህ ያለው የፖለቲካ ወሲብ እስከመቼ ይቀጥላል?  አሁን አገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ዝም ብሎ መወዳደሱ የት ያደርሳል?  የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች – አሰልቺ ውዳሴ፣ መፈክርና ተራ የቀለም ጋጋታ – ሃፍረት መጥፋቱን የሚያሳይ ትዕይንት ከመሆን የማያልፈው ለዚህ ነው። ድል ለአኩራፊዎች!!

በነገራችን ላይ እስካሁን ከተደረጉት ጉቤዎች በኮፊያና በብጥስጣሽ ጨርቆች ያልተብረቀረቀ፣ ለመለዮ በጅት ያልመደበ ብአዴን ነው። ፎቶ  – ጉባኤን ለማመላከት ብቻ የተመረጠ እንጂ አርቲክሉን በሙሉ አይወክልም

ግሩም ሲሳይ

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *