Skip to content

ቅዱስ ፓትሪያርኩን ጨምሮ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሁሉ በእጃቸው በሚይዙት በትር ላይ የለው እባብ ምንድ ነው ?

በትረ ሙሴ [ አርዌ ብርት ] – ዘመድኩን በቀለ

ቅዱስ ፓትሪያርኩን ጨምሮ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሁሉ በእጃቸው በሚይዙት በትር ላይ የለው እባብ ምንድ ነው ?

አንዳንድ ወገኖች በበትሩ ላይ የሚታዩት አራዊት ዘንዶ ናቸው በማለት ነገርየውን #ከ666 ጋር ለማያያዝ ሲሞክሩ ይታያሉ ።

ነገር ግን በፎቶው ላይ እንደሚታየው ዘንዶ ሳይሆን የእባብ ምስል ነው ። እባቡም ደግሞ እንደምትመለከቱት ከመስቀሉ ስር ነው የሚታየው ።

ምክንያቱም መስቀል የሁሉም የበላይና እባብ የተሰኘው ዲያብሎስም አናት አናቱን የተቀጠቀጠበት ነውና ።

[ መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ ] ማቴ 22፣29 ።

የኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናትን የሚመሩ ቅዱሳን ፓትርያርኮችና ሊቃነ ጳጳሳት ፣ ኤጲስ ቆጶሳትም በእጃቸው የሚይዙት አርዌ ብርት/መስቀልና የእባብ ምልክት ያሉበት/ በትር ምሳሌነቱ ከመስቀሉ ስር ያለው ሙሴ ለሕዝቡ መዳኛ ያደረገው የናስ እባብ ምሳሌ ነው፡፡

“ሙሴም የናሱን እባብ ሠርቶ በዓላማ ላይ ሰቀለ እባብም የነደፈችው ሰው ሁሉ የናሱን እባብ ባየ ጊዜ ዳነ” ። ዘኍ 2፣ 19 ።

ይኼ ምሳሌ መሆኑን ክርስቶስ ሲያስተምር “ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል” ።

ዮሐ 3 ፣ 14 በማለት ምሳሌና ጥላ የነበረውን አማናዊ ለማድረግ፣ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎ ያዩት ሁሉ እንደሚድኑ አመሳስሎ አስተማረበት ፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ የናሱን እባብ ከራሱ ስቅለት ጋራ ሲያነጻጽረው ያላፈረበትን፤ የእኛ አባቶች የናሱን እባብ ምሳሌ “በትረ ሙሴ” የሚባለውን በግራ እጃቸው፣ የተሰቀለበትን መስቀል በቀኝ እጃቸው ቢይዙ የሚያሳፍር አይሆንም፡፡

የብሉይ ኪዳን ምሳሌ የሆነውን የናሱን እባብ ስናይ እስራኤላውያን የዳኑት በዚህ በፓትርያርኩ በግራ እጃቸው ባለው የናስ እባብ ነው ብለን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጻፈልንን እንድናስታውስና፣

እኛ ግን የዳንነው በቀኝ እጃቸው ባለው መስቀል ላይ በተሰቀለው በኢየሱስ ክርስቶስ ነው በማለት ለመመስከር ሁለቱንም ማለትም ብሉዩንም አዲሱንም፤ የናሱን ምስልና የክርስቶስን መስቀልን ይዘው ይታያሉ፡፡

ሌላው መሪው ሙሴ የናሱን እባብ ይዞ በዓላማ ላይ ሲሰቅለው እንዳዳናቸው፤ እግዚአብሔር አብ ልጁን በመስቀል ላይ ሰቅሎ ዓለሙን ለማዳኑ መስካሪዎች ስለሆንን “በትረ ሙሴ” የሚል ስያሜ ያለውን በትር የኤጲስ ቆጶሳቱ አለቃ በእጃቸው ይዘው ይታያሉ፡፡ ሙሴ የእስራኤላውያን መሪ ነው፤ ቅዱስ ፓትርያርኩ ደግሞ የሃይማኖት መሪ ናቸውና ይህን በትር ይይዛሉ፡፡

ሙሴ በትር ይይዝና ተአምራት ያደርግ ነበረ፤ “ይህችንም ተአምራት የምታደርግባትን በትር በእጅህ ይዘሃት ሂድ” ዘጸ 4፣17 ያለው እግዚአብሔር ያለ በትር ተአምር ማድረግ ተስኖት ሳይሆን አንተ መሪያቸውና ቤዛ ሆነህ የምታወጣቸው ነህ ሲለው ነው በትሩን አስይዞ የላከው፡፡

ለዚህ ነው ቅዱስ እስጢፋኖስ “ይህን ሙሴን በቍጥቋጦው በታየው በመልአኩ እጅ እግዚአብሔር ሹምና ቤዛ አድርጎ ላከው” ሐዋ 7፣35 ብሎ የመሰከረለት፡፡

ለክርስቲያኖች ጠባቂና የበላይ አባት የሆኑት ቅዱስ ፓትርያሪኩም ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” ተብለው አደራ የተቀበሉ ስለሆነ፣ የመሪነታቸው ምልክት ይህን በትር ይይዛሉ፡፡

ዘንግ በትር መያዝ የአባትነትና የጠባቂነት ምልክት ነው፡፡

የዕብራዊያን ሁሉ አባት ያዕቆብ ዘንግ ይይዝ እንደነበረና፣ ልጁ ዮሴፍ “በዘንጉም ጫፍ ተጠግቶ ሰገደ” ዕብ 11፣21 ተብሎ የተጻፈው አባቱ ዘንግ ስለሚይዝ ነው፡፡

በተጨማሪም እረኛው ዳዊት “በትር ይዞ” 1ኛ ሳሙ 17፣43 በጎቹን እንደሚጠብቅና በኋላም የሕዝብ ጠባቂ ንጉሥ ሲሆን በትረ መንግሥት እንደሚይዝ ዘፍ 49፣10 ፤

የአዲስ ኪዳን እረኞችም ጠባቂነታቸውን ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ተቀብለዋል “…ግልገሎቼን አሰማራ …ጠቦቶቼን ጠብቅ …በጎቼን አሰማራ።

” ባላቸው መሠረት ከሌሎች ብጹዓን ጳጳሳት ለየት ብለው ለጠባቂነታቸው ምልክት በግራ እጃቸው “በትረ ሙሴ” እና በቀኝ እጃቸው የወርቅ መስቀል ጨብጠው ይታያሉ፡፡

Getu Temesgen

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Copyright - zaggolenews. All rights reserved.

0Shares
0
Read previous post:
የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች – አሰልቺ ውዳሴ፣ መፈክርና ተራ የቀለም ጋጋታ – ሃፍረት መጥፋቱን የሚያሳይ ትዕይንት

ሰሞኑን ቲያትር በነጻ ነው። ቲያትሩ የማያዝናና ቢሆንም ሕዝብ ተከታትሎታል። ቲያትሩ አሰልቺና ባዶ ውዳሴ የበዛበት፣ እንዲሁም በመላው አገሪቱ ሃፍረት የሚባል ነገር...

Close