የመስቀል በዓል ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን (327 ዓ.ም) ጀምሮ እንደሚከበር ይነገራል፡፡ በዓሉ ሃይማኖታዊ ትውፊት ያለው በዓል ነው፡፡ በዘመኑ የነበረችው ንግሥት እሌኒ እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል አስቆፍራ ካስወጣችበት ጊዜ ጀምሮ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ይከበራል፡፡ ንግሥቲቱ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ቂራቆስ በተባሉ አባት ጠቋሚነት ለማግኘት ደመራ አስደምራ ፍለጋ የጀመረችው መስከረም 17 ቀን እንደሆነ የክርስትና ሃይማኖት ድርሳናት ያወሳሉ፡፡

የሃይማኖት አባቶችን አሰባስባ በፀሎት እንዲረዷት ጠይቃ፤ ከደመራው በሚወጣው ጢስ ጠቋሚነት መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ አግኝታለች፡፡ መስቀሉም ከወራት ቁፋሮ በኋላ መጋቢት 10 ቀን ወጥቷል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መስከረም 16 ቀን ‹ደመራ› እና መስከረም 17 ቀን ‹የመስቀል በዓል› እየተባለ ይከበራል፡፡
ከአራተኛው ምዕተ ዓመት ጀምሮ እንደሚከበር የሚነገርለት ይህ በዓል ከአራት ዓመታት በፊት በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ላይ በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል፡፡

እኛም በዚህ የመስቀል በዓል ዳሰሳችን ከደቡቡ የኢትዮጵያ ጫፍ የጉራጌ ብሄረሰብ ዞን እስከ ሰሜናዊው የኢትዮጵያ ተራራማ ቦታ ግሸን ደብረ ከርቤ ድረስ የበዓሉን ታሪካዊ ዳራ እያንሰላሰልን በአጭሩ ልናስቃኝችሁ ወደድን… ተከተሉን፡፡
የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱ እንዳለ ሆኖ በየአካባቢው እንደ ማህበረሰቡ ባህልና ወግም ይከበራል፡፡ መስቀል ሲወሳ ጉራጌ፤ ጉራጌ ሲነሳ መስቀል የሚነጣጠሉ አይመስሉም፡፡ በስራ ትጋታቸውና ታታሪነታቸው ምሳሌ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ጉራጌዎች የመስቀል በዓል ሌላው የባህል አምባሳደራቸው ነው፡፡ መስቀል በጉራጌ እጅጉን ይለያል፡፡

ከመስከረም 12 ቀን እስከ ጥቅምት 5 ቀን በተከታታይ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች የሚከበረው የጉራጌዎች የመስቀል በዓል በዘመናት መካከል ነባር ትውፊቶቹን ጠብቆ የዘለቀ ደማቅ በዓል ነው፡፡ የመስቀል በዓል በጉራጌ ብሄረሰብ አባላት የበዓላት ሁሉ አውራ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

ከደመራና መስቀል ቀናት በፊትና በኋላ ባሉት ቀናት በተለያዩ ስነ ስርዓቶች የሚከበረው መስቀል፤ በተለያዩ ቦታዎች የሚኖሩ የጉራጌ ተወላጆች ወደ ትውልድ ቀያቸው በመሄድ በዓሉን ከቤተሰቦቻቸው ጋር በአንድነት ያከብሩታል፡፡
መስቀል በጉራጌ ትልቅ በዓል እንደመሆኑ ዝግጅቱም ያንኑ ያክል ሰፊ ነው፡፡ የመስቀል በዓል ከተከበረበት ዕለት ጀምሮ ለሚመጣው ዓመት የመስቀል በዓል ዝግጅት ይጀመራል፡፡ ጉራጌዎች ለመስቀል በዓል ዝግጅት ሲጀምሩ ስራ በእድሜና በጾታ ክፍፍል ይደረጋል፡፡ በዚህም መሰረት ልጆችና ወጣት ወንዶች ጫካ ወርደው እንጨት ፈልጠው ለደመራ ሲያደርቁ አባቶች የእርድ ከብቶችን ያደልባሉ ያዘጋጃሉ፡፡ እናቶች ለበዓሉ ቅቤ ሲንጡና እንሰት ሲፍቁ ልጃገረዶች ቤት ማዘጋጀትና ማስዋብ ድርሻቸው ይሆናል፡፡ ‹ሌማት ይወርድቦ ቀነ› በመባል በሚታወቀው መስከረም 12 ቀንም ግድግዳ ላይ የተሰቀሉ የምግብ እቃዎች ወርደው ይፀዳሉ፡፡

የጉራጌ እናቶች የምግብ ሙያ ግሩም የሚባልለት ክትፎ መስከረም 16 ቀን በጣባ ይበላል፡፡ ክትፎ የጉራጌ ሴቶች ልዩ ክህሎትም ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በከተሞቻችን ባሉ ምግብ ቤቶች ‹የጉራጌ ክትፎ› የሚለው ማስታወቂያ የጉራጌ ሴቶች በክትፎ ምን ያክል እንደሚጠበቡ አመላካች ሳይሆን አይቀርም፡፡
ከላይ ለማንሳት እንደሞከርነው ከመስከረም 12 ቀን ጀምሮ እስከ ጥቅምት 5 ቀን ድረስ ጉራጌ በመስቀል ትደምቃለች፡፡ ልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ማህበረሰባዊ ወጎችና ልምዶች በእየለቱ ይከወናሉ፡፡ መስቀል በጉራጌ ይደምቃል፤ ጉራጌም በመስቀል ሃሴትን ታደርጋለች፡፡ በመጨረሻም በመስቀል በዓል ማጠናቀቂያ ወቅት ስለግብርና እና ንግድ አባቶች ይመክራሉ፡፡ ወጣቶችም ከእድሜ ባለፀጎች ኃላፊነት ተቀብለውና ተመራርቀው በዓሉ ያከትማል፤ ጉራጌዎችም ከርሞን ያልማሉ፡፡
በደቡብ የኢትዮጵያ ጫፍ የምትገኘው ጉራጌ በድምቀት የምታከብረው የመስቀል በዓል ስረ መሰረቱ ሃይማኖታዊ ነው፡፡ የዚህ ሃይማኖታዊ በዓል ሌላው ቅርንጫፉ በሰሜናዊው የኢትዮጵያ መስቀለኛ ተራራማ ቦታ ደግሞ እንዲህ ይከበራል፡፡
በንግስት እሌኒ አማካኝነት ከተቀበረበት የወጣው የክርስቶስ ግማደ መስቀል ክፋይ ከሰሜን ኢትዮጵያ ተራራማ ሰንሰለቶች በአንዱ በመስቀለኛው ተራራ ግሸን ደብረ ከርቤ ይገኛል፡፡ ይህንን በዓል ለማክበርም ቁጥሩ የበዛ ምዕመን ወደ ታራራማዋ ስፍራ ይጓዛል፡፡
ግሸን ደብረ ከርቤ በደቡብ ወሎ ዞን ከዞኑ ዋና ከተማ ደሴ በ82 ኪ.ሜ ርቀት ላይ አምባሰል ወረዳ ውስጥ በተፈጥሮ የመስቀል ቅርጽን ከያዘው የግሸን ዓምባ ላይ የተመሰረተች ገዳም ናት፡፡
ግሸን ደብረ ከርቤ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ጥንታዊ ገዳማትም ውስጥ አንዷ ናት፡፡ ግሸን አምባ ከባሕር ጠለል 3 019 ሜት (9905 ጫማ) ከፍታ ላይ የምትገኝ ሲሆን በአምባው ላይ 37.74 ሄክታር ስፋት ባለው ቦታ ላይ አራት አቢያተ ክርስቲያናት ግሸን ማሪያም፣ እግዚያብሄር አብ (በመስቀል ቅርፅ የታነፀው)፣ ቅዱስ ገብርኤልና ቅዱስ ሚካኤል ይገኛሉ፡፡

የግሸንን ደብር የመሰረቷት አንድ በስራቸው ፃድቅ የሆኑ መነኩሴ እደነበሩ ይነገራል፡፡ ዘመኑም በ514 ዓ.ም ከዘርዓይቆብ መነሳት 900 ዓመታት በፊት ነበር፡፡ አሁን ቦታው በይበልጥ የሚታወቀው የእየሱስ ክርስቶስ ግማደ መስቀል የሚገኝበት መሆኑ ነው፡፡
አፄ ዘርዓይቆብ በነገሱ ዘመን ወደ ስናር (ሱዳን) ሄደው ግማደ መስቀሉን እና ሌሎች የቤተክርስቲያን ውድ ንዋየ ቅድሳትን በማምጣት መስከረም 21 ቀን 1446 ዓ.ም አስቀመጡት፡፡ ከአራት ዓመታት በኋላም መስከረም 21 ቀን 1449 ጀምሮ የመስቀል በዓል በዚሁ እለት መከበር እንደተጀመረ ይነገራል፡፡
ምንም እንኳን መስቀል በመላው ኢትዮጵያዊያን ዘንድ በድምቀት የሚከበር በዓል ቢሆንም የደቡባዊቷ ኢትዮጵያ ጥግ ጉራጌዎች መስቀልን በተለየ ድምቀት ሲያከብሩት፤ በሰሜናዊ አቅጣጫ የምትገኘው ግሽን ደብረ ከርቤ ደግሞ የዚህኑ የመስቀል ክፍል ወደ ኢትዮጵያ የመጣበትን ንግስ በሚሊየን ከሚቆጠሩ ምዕመኖቿ ጋር በድምቀት አክብራ ትውላለች፡፡
እኛም መስቀልን ከጉራጌ እስከ ግሸን ደብረ ከርቤ የቃኘንብትን አጭር ዳሰሳ በዚሁ ቋጨን፡፡
መልካም በዓል!!!
በታዘብ አራጋው –Amhara Mass Media Agency

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *