“Our true nationality is mankind.”H.G.

ደም ፈላጊው በዛ ፤ የሚፈለገው መጠን ደም የለም – የባሕርዳር ደም ባንክ አገልግሎት

‹‹ከሞት የታደጉኝን ወገኖቸን ደም በመለገስ ውለታቸውን እየከፈልኩ ነው፡፡›› በባሕርዳር ከተማ ፖሊስ መምሪያ ረዳት ሳጅን የሽበር ሙሃባው

ባሕር ዳር፡መስከረም 24/2011 ዓ.ም(አብመድ) ረዳት ሳጅን የሽበር ሙሃባው በባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ በፖሊስ ሙያ እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በተለያዩ አደጋዎች ደም ፈሷቸው እርዳታ ለሚሹ ሰዎች የሚሆን ደም ሲለግሱ ነው ያገኘናቸው፡፡ደም ለመለገስ ያነሳሳቸው ምክንያት ደግሞ ከሶስት ዓመት በፊት የደረሰባቸው የመኪና አደጋ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ የመኪና አደጋ ደርሶብኝ አሰቃቂ የአካል ጉዳት ባጋጠመኝ ወቅት ከፍተኛ ደም ፈሶኝ ስለነበር በህይዎት ይተርፋል ብሎ የጠበቀ ሰው አልነበረም፡፡የተረፍኩት በጎ ፍቃደኞች በለገሱኝ ደም ነበር፡፡ አሁን ከሞት የታደጉኝን ሰዎች ውለታ ለመመለስ ደም እየለገስኩ ነው፡፡›› ብለዋል፡፡

ረዳት ሳጅን የሽበር ሙሃባው እንደነገሩን ደም በመለገስ ደም በማጣት ህይወታቸውን የሚያጡ ወገኖችን ህይወት ከመታደግ በላይ የሚያስደስት ነገር የለም፡፡

ልክ እንደ ረዳት ሳጅን የሽበር ሙሃባው በባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የሚገኙ የፖሊስ አባላት እና በባሕርዳር ከተማ የሚገኙ የክልሉ ልዩ ሀይል የአንደኛ ብርጌድ ሁለተኛ ሻለቃ አባላት በበጎ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ የደም ልገሳ አድርገዋል፡፡

የባሕርዳር ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ዋለልኝ ዳኘው እንደነገሩን ፖሊስ የህብረተሰቡን ሰላም እና ፀጥታ ለማስጠበቅ እየሰራ ከሚገኘው ተግባር ጎን ለጎን ደም ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ደም በመለገስ ወገናዊነቱን ማሳየቱ መልካም ተግባር ነው፡፡

ፖሊስ ወገንተኛነቱን በተግባር እያሳየ ነው የሚሉት ኮማንደር ዋለልኝ ዳኘው በፖሊስ መምሪያው ከ6መቶ በላይ አባላት ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት ደማቸውን ለመለገስ ፈቃደኛ ናቸው፡፡ የፖሊስ ደም ልገሳ ዛሬ ተጀምሯል፤በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡

የልዩ ሀይል ፖሊስ አባላት ከአሁን በፊት ለሶስት ጊዜ ደም እንደለገሱ የነገሩን ኮማንደር ዋለልኝ ዳኘው ይህን በጎ ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥሉበት ያላቸውን ተስፋ ገልጸውልናል፡፡

በባሕርዳር ከተማ በትራፊክ አደጋ በዓመት 28 ሰዎች ህይወታቸው እንደሚያልፍ ከከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ በወሊድ እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ደም ፈሷቸው በየሆስፒታል እርዳታ እየጠየቁ የሚገኙት የህብረተሰብ ክፍሎች ቁጥራቸው ከፍተኛ ነው፡፡

ይሁን እንጅ ከደም ለጋሾች የሚገኘው ደም ዝቅተኛ መሆኑን ከባሕርዳር ደም ባንክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡ 
ባለፈው ዓመት 11ሺህ ዩኒት ደም ከለጋሾች መሰብሰብ ቢቻልም ከደም ፈላጊው ጋር ባለመጣጣሙ ለደም ፈላጊው ማህበረሰብ በወቅቱ ደም ማድረስ አልተቻለም፡፡

በበጀት ዓመቱ የባሕርዳር ደም ባንክ አገልግሎት ከ13ሺህ በላይ ዩኒት ደም ከበጎ ፈቃደኞች ለመሰብሰብ እቅድ ይዟል፡፡

ዘጋቢ፡-ሀይሉ ማሞ

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የዘረኝነት ጥግ “እናት ነኝ የሌሎች ህፃናት ወላጆችን ግን ገደልኩ”
0Shares
0