ሃዋሳ ከትሞ በተካሄደው የኢህአዴግ ጉብኤ ከራሳቸው አንድ ድምጽ በቀር ሁሉንም ድጋፍ አግኝተው ለሊቀመንበርነት የተመረጡት ዶክተር አብይ አሕመድ መሆናቸው ይፋ ሲሆን የጉባኤው አዳራሽ ደስታውን የገለጸበት መንገድ አስገራሚ ነበር። እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ አቶ ደመቀ መኮንንም ምክትል ሊቀመንበርነት ሲታወጅ ጉባኤው ፈንድቋል። ውጤቱን ተከትሎ ማህበራዊ ገጾች አበባ በትነዋል። ደስታቸውን ገልጸዋል። ቅር ያላቸውም መንጨርጨራቸውን አሳይተዋል። አላስፈላጊ ብሽሽቅም ታይቷል። አዝናኝ ጉሸማዎችም ተሰምተዋል።

በተለያዩ ወገኖች በዙ ሲባልለት የነበረው ይህ ጉባኤ በፍጥነትና በተያዘለት የጊዜ ገደብ ከመጠናቀቁ ውጪ በኦፊሳል የታወቀ ውዝግብ አልተሰማበትም። ኢህአዴግ ሊፈርስ  እንደሚችል፣ ህወሃት ባለመግባባት ከህብረቱ ሊወጣ እንደሚችል ብዙ ትንተና ቢሰጥም እስካሁን በውል የታየው ከቅድመ ግምቶቹ ሁሉ የተለየ ነው።

የመስመርም ሆነ የርዕተዓለም ለውጥን አስመልክቶ ልዩነት አለመኖሩን፣ አጀንዳም እንዲሆን ሃሳብ እንደሌለ ያስታወቀው ጉብኤ፣ አንድ ዓይነት ቀለም እንዳለው ቢያስመስልም ቢያንስ አቃጣሪ የቪዲዮ ካሜራዎች እንደሚመሰክሩት ከጭብጨባ፣ ከጎን ግንኙነትና በሚታይ የግጽታ ስሜት ውስጥ መሰረታዊ ልዩነት መኖሩን መደበቅ አይቻልም። በየክልሉ ከሚዶለተው የፖለቲካ ቁማር በተጨማሪ!!

ከወትሮው በተለየ ጥብቆና መለዮ ተመሳስሎ ያልታየው የኢህአዴግ ጉባኤ ባወጣው መግለጫ “የዜጎች ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመስራት መብት እንዲከበርና ብሄራዊ ማንነትና ሃገራዊ አንድነት እንዲጠናከር አበክሮ መስራትም በጉባኤተኞቹ ስምምነት ተደርሶበታል” የሚለውና የህግ የበላይነት እንዲከበር የተያዘው አቋም ” ከዚያስ” የሚለው ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ብቻ የሚቀርብ ጥያቄ አይሆንም።

“ስርዓት አልበኝትን በማስወገድና ሰላምን በማስፈን የህግ የበላይነትን ማረጋገጥና ለህግ የበላይነት መከበርና ለሰላም መስፈን የሚተጋ ዜጋን መፍጠር” እንደሚገባ ያስታወቀው የኢህአዴግ መግለጫ አገርን ማረጋጋትና ወደ ሰላም መውሰድ የህዝብ ስምምነትንና ተባባሪነትን የሚጠይቅ መሆኑን አመላካች ነው። ይህ ካልሆነና በመስማማት ወደ ሰላም መንገድ መሄድ ካልተቻለ አገሪቱን የሚያደቃት የተለመደው የጉልበት አካሄድ እንደሚከተል ” የፀጥታ አካላትም ፀጥታን የማስከበር ህገ መንግስታዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ ቀርቧል ” የሚለው የመጨረሻው የመግለጫው ክፍል ያስረዳል። 

መግለጫው ብዙ ጉዳዮችን ቢያነሳም፣ ስብሰባ የማይታክተው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻአሚ በተደጋጋሚ ቃል ከገባቸውና ወደ ተግባር መለወጥ ካልቻሉት ጉዳዮች የተለየ ሃሳብ እንዳላካተተ የሚናገሩ አሉ። ችግሩ ያለው አጋር ክልሎች ላይ ተለጥፎ አገርን የማተራመስና ለዚሁ ተግባር በጀት መመደብ ላይ እንደሆነ የሚተቹ ክፍሎች ” ከዛስ ” ይላሉ።

እነዚሁ ክፍሎች እንደሚሉት ኢህአዴግ ሃዋሳ ቁጭ ብሎ ሲመክር፣ መገለጫ ሲያወጣ ፣ እዛ ጎን ለጎን በተቀመጡ ክልል መሪዎች በሚተዳደሩ አካባቢዎች ውስጥ መርዶ ይሰማል። በአገሪቱ የሚታየው መፈናቀል፣ ግድያና ሰብአዊ ቀውስ መረን የወጣው እነዚሁ እዛው የተሰበሰቡት ወገኖች በሚመሯቸው አስተዳደሮች ውስጥ መሆናቸው እየታወቀ እዛው የጎንዮሽ ድርድርና ውይይት በማድረግ መፍትሄ ሲፈልጉ አልተሰማም። 

በዚህ አልሰክን ባለ የደባ ፖለቲካ ተነክሮ እየተጓዘ ያለው የአገሪቱ የለውጥ ጉዞ በተለይም በአፋር፣ በቤኒሻንጉልና በከፊል በጋምቤላ ባስቸኳይ የተከፈለው መስዋእትነት ተከፍሎ መላ ካልተባለ ችግሩ አሳሳቢ እንደሚሆን ከጉባኤው ድምቀት በስተጀረባ ያለው ቀለም ነውና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጠንቀቅ ሊሉ ይገባል በሚል ፍርሃቻ አዘል አስተያየት የሚሰጡ አሉ። በተለይም የስማሌው ክልል ሰንኮፍ ሲነቀል ወደ አፋር በአፋር ክልል መዛወሩን ጥንቅቀው የሚያውቁ እንደሚሉት አፋር ክልል ዋና ጉዳይ ነው። 

ምርጫው አልቋል። ጉባኤው ድጋፍ አድርጓል። ባስቸኳይ የወረዳና የቀበሌ መዋቅርን በማደራጀት አገሪቱን ማረጋጋት ግድ ነው። እገሌ ከገሌ ሳይባል ድጋፍም ሊያደርግ ይገባል። አዲሱን አመራር መውደድ በመታዘዝና በማገዝም ጭምር በመሆኑ ሕዝብ አገሩን በማስተዋል ሊጠብቅና ማስከን አለበት። ህግን በማክበርና በማስከበር መብትን ማስከበር ፣ ግዴታን መወጣት የሁሉም ሃላፊነት  እንደሆነ ሁሉም ዜጋ ሊረዳ እንደሚገባ ምክር የሚለግሱ ጥቂት አይደሉም።

አሁን የሚታየው የብሽሽቅ ፖለቲካና ነገር ስንጠቃ፣ ከግል ስሜትና ከቡድን ወኔ በመነጨ የሚነዛው አሉባልታ አገር ያፈርሳልና ሁሉም ልብ ሊል እንደሚገባ የገባቸው እየወተወቱ ነው። እነዚሁ ወገኖች አሁን ያለው ቀውስ በዝግታ መላ ካልተፈለገለት አደጋው ሊከፋና ከቁጥጥርም ውጪ ሊወጣ ስለሚችል ከተራ ጀብደኝነትና ብሽሽቅ መራቅ አስፈላጊ እንደሆነ ያሰምሩበታል። ከዚህ ውጪ እብደት የሚመስለው የማህበራዊ ሚዲያ ጦርነትና ሸረኞች የሚለኩሱትን በማራገብ ሳያውቁ የጥፋት ሰላብ የሚሆኑ አካላትም ራሳቸውን ሊመረምሩ እንደሚገባ ይመክራሉ።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *