በዩኔስኮ በመመዝገብ ቀዳሚ፤ግን ደግሞ ለከፋ ጉዳት የተዳረገው ረቂቁ አሻራችን! ያልተፈቱ እንቆቅልሾችን፣ ረቂቅ ምስጢራትን እንደያዙ ዘመናትን የተሻገሩ፤ አፍን በእጅ ጭኖ፣ አቅልንም ስቶ እንዲመለከቱ የግድ የሚሉ ቅርሶች፤የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት፡፡ የያኔዎቹን ቅድመ አያቶቻችን ትጋት እና በጥልቅ የመመርመር እና የመመራመር ብቃት የሚመሰክሩ ህያዉ አሻራዎቻችንም ናቸው፤ቅርሶቹ፡፡ እንዴት ተገነቡ? እንዴትስ ተቻለ?…የሚሉት እና ሌሎችም እስካሁን ድረስ መልስ ያላገኙ ጥያቄዎች አሁንም ምስጢርነታቸው ለዓለም ሳይገለጥ እንዳሉ ይኖራሉ፡፡

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ካስመዘገበቻቸው ዘጠኝ የሚዳሰሱ ቅርሶቿ መካከል ሁለቱ በበኩርነት ይታወቃሉ፤የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት እና የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ፡፡ ሁለቱም እ.አ.አ. በ1978 ነበር በዩኔስኮ የተመዘገቡት፡፡ ሁለቱም ግን የዓለም ቅርስ በመሆን ባላቸው ዝና ብቻ አይደለም የሚታወቁት፤እየደሰረባቸው ባለው ጉዳት እና ስጋትም ጭምር የጋራ ታሪክን ይጋራሉና፡፡

43243411_823770077797988_4684058575302033408_n.jpg

የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ እ.አ.አ. ከ1996 ጀምሮ በአደጋ መዝገብ ውስጥ መግባቱ ይታወቃል፡፡ ልቅ ግጦሽ፣የብርቅዬ እንስሳቱ ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት፣በፓርኩ ውስጥ መኖሪያ ቤቶች መኖራቸው እና የእርሻ መሬት መስፋፋት ናቸው ቅርሱን ከ20 ዓመታት በላይ በአደጋ መዝገብ ውስጥ እንዲቆይ ያደረጉት፡፡ አሁን ላይ ግን በአደጋ መዝገብ ውስጥ እንዲገባ ምክንያት የነበሩ ችግሮች በመስተካከላቸው ከአደጋ ነጻ ተብሏል፡፡

የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት ዕጣ ፋንታም ጉዳት፣መሰነጣጠቅ እና የመፍረስ ስጋት ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ የቅርሶቹ ገጽታ ወዘናው ጠፍቷል፤ የተሰነጣጠቀ ሰውነታቸው ‹ከድረሱልኝ ጥሪ› በላይ አፍ አውጥቶ ይናገራል፡፡ አዎ! ‹ቅርሶቹ ወደ ነበሩበት ሳይመለሱማ እንዴት የሰላም እንቅልፍ እተኛለሁ!› የሚሉ ተቆርቋሪ ኢትዮጵያዊያንን ይሻሉ፡፡ ውቅር አብያተ ክርስትያናቱ የዓለም ቅርስ ናቸው ከሚል ትርክት ያለፈ ገቢራዊ ፈውስ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ቅርሶቹም ሁነኛ መዳኛቸውን ፍለጋ እጆቻቸውን ከዘረጉ ሰነባብተዋል፡፡

ከ80 በመቶ በላይ ጎብኚዎች የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናትን ታሳቢ አድርገው እንደሚገቡ ጥናቶች ቢያሳዩም፣ ከላልይበላ አልፎ ለኢትዮጵያ መጎብኘት ዋነኛ ምክንያት እንደሆኑ ቢታመንም፣ ለህመማቸው ፈጥኖ ደራሽ ሀኪም ማጣታቸው ግን ለምን እንደሆነ ሳይገለጥላቸው አሁን ድረስ ቀጥሏል፡፡ ላለፉት 800 ዓመታት መንፈሳዊ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ አብያተ ክርስቲያናት ታመዋል፤ጉዳት ላይ ናቸውና፡፡ እናም ‹‹በቅርብ ያልመለሰ እረኛ ሲሮጥ ይውላል›› ነውና አባባሉ፣ የዘገየም ቢሆን ከዚህ በላይ ሳይዘገዩ መፍትሄ መስጠቱ ለነገ ባይባል ብዙ ያተርፍልናል፡፡

ኢትዮጵያ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ዘጠኝ የሚዳሰሱ ቅርሶች አሏት፡፡ የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ እና የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት (እ.አ.አ. በ1978)፣ የአጼ ፋሲል ምድረ ግቢ (እ.አ.አ. በ1979)፣ የአክሱም ሃውልቶች፣የጢያ ትክል ድንጋዮች፣የታችኛው ኦሞ እና አዋሽ ሸለቆዎች (እ.አ.አ. በ1980) ነው የተመዘገቡት፡፡ የጀጎል ግንብ(እ.አ.አ.በ2006)፣ የኮንሶ መልከዓምድር ደግሞ (እ.አ.አ. በ2011) ነበር በዩኔስኮ መዝገብ ላይ የሰፈሩት፡፡

በአስማማው በቀለ – አማራ መገናና ብዙሃን

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *