“Our true nationality is mankind.”H.G.

” መንግሥት የታጠቁትን ማስፈታት መጀመር አለበት፤… ያለምንም እሹሩሩ በሕግ አግባብ በገሃድ ተጠያቂ ማድረግ ያስፈልጋል” ከጸጋዬ አራርሳ


አሁን የሥልጣን ሽኩቻና እሽቅድምድሙ አልቋል። ስለዚህ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግሥት፣ ሙሉ አትኩሮቱን ወደ አገር ማስተዳደሩና ወደ ሽግግሩ ሥራ ይመልሳል ተብሎ ይታሰባል። ብዙ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ሥራዎች ይጠብቁታል።

አንገብጋቢ የዕለት ተእለት አስተዳደራዊ ጉዳዮች፥ የኢኮኖሚ ፍትህ ማየስፈን ጉዳይ፥ ፖለቲካዊ ምላሽ የሚሹ ፖለቲካዊ የሕዝብ ጥያቄዎችን የመመለስ ጉዳይ፥ የዴሞክራሲያዊ ሽግግሩን ሂደት ለማቀላጠፍ እንዲረዳ መፈፀም ያለበት የፓለቲካ ምህዳሩን የማስፋት ሥራ፥ ታጣቂዋችን ትጥቅ በማስፈታት፣ እየታጠቁ ያሉትንም እያስቆሙ ፖለቲካውን ከብረት የማላቀቅ ሥራ፥ ተፈናቃዮችን የማረጋገት (መልሶ የማቋቋም) የሰብዓዊነት ሥራ፥ ያደሩና የከራረሙ ታሪካዊ ቁስሎችን ለመፈወስና ለመሻር የሚያስፈልግ የአገራዊ እርቅ (ማለትም የእውነት [truth]፥ የይቅርታ [apology]፥ ምህረት [forgiveness]፥ መታረቅ [reconciliation–horizontal and vertical]፥ እና ፍትህ የማስፈን) ሥራ ከፊቱ ተደቅነው ይጠብቁታል።

ዛሬ፣ እየናረ ያለውን የኑሮ ውድነት መግታትና አስፈላጊ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ማዳረስ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። በተለይ በከተሞች አካባቢ ያለው የኑሮ ውድነት፣ በልቶ ማደርንና የቤት ኪራይ ከፍሎ ወር መዝለቅን አስቸጋሪ አድርጎታል። የተማሩ ወጣቶች የሥራ ማጣት ጉዳይም እንደዚሁ ሌላው እራስ ምታት ነው። በዚህ ረገድ፣ በኦሮምያ ተጀምሮ የነበረው የ”የኢኮኖሚ አብዮት”፣ አንዳንድ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ከመክፈት ውጭ ያስገኘው ውጤት መኖሩ ሊጤን ይገባዋል። ይኼ ተሞክሮ (ውጤቱ ጥሩ ከሆነም) ወደሌሎች አካባቢዎች ተስወዶ፥ ይጠቅም እንደሆነ ታይቶ scale up ቢደረግ መልካም ይሆን ይሆናል።

አሁንም የቤት እጥረት በከተሞች (በተለይ በፊንፊኔ) እንዳለ ነው። የኮንዶሚኒየም አሰጣጥ ሥርዓቱም እላይ እየሆነ ያለውን ለውጥ ተከትሎ እየተለወጠ አይመስልም። ከሆነም ፍጥነቱ ዝግተኛ ነው።

የመሬት አስተዳደር፣ የመሬት ነጠቃውን (እና ችብቸባውን) ለመግታት ፍላጎትም ብቃትም ያለው አይመስልም። ፊንፊኔ ዙሪያ (ለምሳሌ በለገ-ጣፎ እስከ ሰንዳፋ፥ አለልቱ፥ ገዋሳ፥ ቅንብቢት፣ በቱሉ ዲምቱ፥ ወዘተ) መንግሥት ያለ እስከማይመስል ድረስ የመሬት ነጠቃው ተግባር እየተስፋፋ ቀጥሏል። ይሄ የመሬት ነጠቃ ሂደት ካልተገታ የሚፈጥረው መፈናቀል፥ የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ኢፍትሃዊነት፥ እና የሚቀሰቅሰው ቀውስ ፖለቲካውን መልሶ እንዳያናጋው ያሰጋል።

በመሆኑም፣ የዋጋ ቁጥጥር ማድረግ፥ የቤት እጦትና የኮንዶሚኒየም ኪራይ ዋጋ ችግርን መፍታት፥ የሥራ ዕድል ፈጠራ ተግባርና የመሬት ነጠቃና ማፈናቀልን የማስቆም ሥራ ዛሬውኑ ቅድሚያ ተሰጥቶት ሊጀመር የሚገባው ተግባር ነው።

ተፈናቅለው በብዙ መከራ ውስጥ ላሉት ሚልዮኖችም ፈጣን የመልሶ ማቋቋም ሥራ ለመስራት አስፈላጊው አስተዳደራዊና የርህራሄ እርምጃ (measures of compassion) መወሰድ አለበት።

ከዚህ ባሻገር፣ በተቃውሞ እንቅስቃሴው ወቅት የተነሱ የፖለቲካ ጥያቄዎች እስካሁንም አልተመለሱም። ለመመለስም እየተወሰደ ያለ ጠንከር ያለ እርምጃ አይታይም። የኦሮሞ ወጣቶች ያነሱት የአገር ባለቤትነት ጥያቄ (ለምሳሌ በፊንፊኔ ላይ ኦሮምያ ያለው ሕገ-መንግሥታዊ የልዩ ጥቅም ጥያቄ)፥ ቋንቋውን የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ የማድረግ ጥያቄ፥ ከመሬት ያለመፈናቀል ጥያቄ ፥ የድንበራችን ይከበርልን ጥያቄ ፥ የሰላም ጥያቄ ፥ ወዘተ አትኩሮት ተሰጥቶአቸው፣ ለመፍትሄዎቹ አስፈላጊውን ሕጋዊና ሕገ-መንግሥታዊ ሂደት ማንቀሳቀስ ያስፈልጋል። አስፈላጊው ፖለቲካዊ ውሳኔም ሊወሰን ይገባዋል።

ይህ እየተደረገም (በመንግሥት ብቻ ሳይሆን በሁሉም የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች)፣ በአስቸኳይ ሊሰራበት የሚገባው ጉዳይ የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ነው። ከመከላከያ ሠራዊቱና ከሕግ አስከባሪ ኃይሎች ውጪ ትጥቅ መታጠቅ አስፈላጊም፥ ሕጋዊም፥ ትክክልም አይደለም።

ከዚህ በፊት የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ ኅይሎች፣ ከአሁን በኋላ በትጥቅ የሚያራምዱት ፖለቲካ ስለማይኖር፣ የነበራቸውን የታጠቀ ኃይል ወደ ሠራዊቱ ለማቀላቀል ድርድርና አስፈላጊውን እንቅስቃሴ ሁሉ በፍጥነት ማካሄድ አለባቸው። ኃይሎቻቸው ሙሉ በሙሉ እስኪዋሃዱ ድረስም፣ በሰላም መጠበቁ ተግባር (ቢያንስ በስፋት በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች) ላይ ድርጊቶቻቸውን ከአገሪቱ ሠራዊት ጋር ማቀናጀት (coordinate ማድረግ) ግድ ይላል።

በየክልሉ “ልዩ ኃይል” እየተባሉ የተፈጠሩ፣ በመሠረቱ ፀረ-ሰላምና አፋኝ የሆኑ ታጣቂዎች፣ ወይ ወደ መደበኛው ሰራዊት፣ ወይ ወደ ፖሊስ ሠራዊት መግባት አለባቸው። በወንጀል ሲሳተፉ የነበሩትም በሕግ ተጠይቂ ሊደረጉ ይገባል። ተቋማቱ ግን መፍረስ አለባቸው።

የክልሎች የፖሊስ አቅም መጠናከር አለበት። (ለመጀመርያ ጊዜ ያለ ፌዴራል ጣልቃ-ገብነት የእራሳቸውን አካባቢያዊ ሰላም የማስጠበቅና ሕግን የማስከበር ሃላፊነት ስለሚሸከሙ ፈተናቸው ብዙ ነውና።)

በየአካባቢው ሲቪሉን ሕዝብ የማስታጠቅ ተግባር (እና እራስን የማስታጠቅ ጥሪ ሁሉ) በአስቸኳይ መቆም አለበት። ይሄ ካልተደረገ፣ ሥርዓቱን ወደ ዴሞክራሲ የማሸጋገር ዕቅድ ሊሰናከል ይችላል።

የዴሞክራሲያዊ ምርጫው ውጤት አያስደስተኝ አይስማማኝ ይሆልና ብሎ የሰጋ ቡድን ሁሉ ከወዲሁ ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገውን ጉዞ ለማስተጓጎል፣ በዚህ ፖለቲካዊ ተጠያቂነት በሌለው ማሕበረሰባዊ ብረት ሊጠቀም ይችልላ።

ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ እስከዛሬ እንደነበረው ፖለቲካችን ከብረት እንዳይላቀቅ በማድረግ፣ የሰላማዊ-ዴሞክራሲያዊን ፖለቲካ ተስፋ አምክኖ፥ ባዶ ህልም ብቻ አድርጎ ያስቀርብናል። ስለዚህ መንግሥት የታጠቁትን ማስፈታት መጀመር አለበት። እየታጠቁና እያስታጠቁ ያሉትን ሁሉ ማስቆም አለበት።

የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች ፖለቲካዊ ኃይሎች ሁሉ ለሰላም መተባበር አለባቸው። የሰላም ፍላጎታቸውንም በግልፅ ለሕዝብ እየገለፁ ተጠይያቂነትን መሸከም መጀመር አለባቸው።

መንግሥትም የሁላቸውንም ሰላምና ደህንነት ሳያዳላ ለማስጠበቅ፣ ዋስትና መስጠትና በተጨባጭ መንቀሳቀስ ይጠበቅታል። ከመስጋት የተነሳ እራሳቸውን እያስታጠቁ ላሉ ወገኖችም፣ ሙሉ የግሕ ጥበቃ በመስጠት በመብታቸው ላይ የሚቃጣን ጥቃት ሁሉ በሕግ ማስቀጣት ይገባልዋ። ለዚህ ደግሞ የሕግ የበላይነትን አጠናክሮ መተግበር ግድ ይላል።

ከመብት ያለፈ የፖለቲካ ምኞትን ለማሟላት በማሰብ ብቻ እራስን በማስታጠቅ ያልተገባ የፖለቲካ ፍላጎትን በመሳሪያ በመመካት ሌሎች ላይ ለመጫን የሚንቀሳቀሱ የእብሪት ኃይሎችን ያለምንም እሹሩሩ በሕግ አግባብ በገሃድ ተጠያቂ ማድረግ ያስፈልጋል።

በክልሎች መካከል የድንበር ሰላም ለመፍጠር እንዲቻል ሕገ-መንግሥታዊ የሰላምና የፍርድ ተቋማትን (ለምሳሌ የፌደሬሽን ምክር ቤትን) ማንቀሳቀስ ያስፈልጋል።

ሰላምን ማስፈን አስፈላጊነቱ፣ ዴሞክራሲያዊ ሽግግሩን ለማቀላጠፍ ነው። መንግሥት ከምር ሽግግሩን የሚሻ ከሆነ፣ አፋኝ ህጎቹን ለመሻርና እንደስአፈላጊነቱም ለማሻሻል በፍጥነት መንቀሳቀስ አለበት። በተለይ የምርጫ ሕጉንና ምርጫ ቦርድን እንደ አዲስ የማደራጀቱ ሥራ ሳይውል ሳያድር መጀመር አለበት። ይሄ፣ ለምርጫ ዝግጅትም የመጀመሪያው እርምጃ ነው።

ይኸን ሁሉ ማድረግ ቀላል አይደለም።

ነገር ግን የሰሞኑ የኢሕአዴግ ሊቀ-መንበሮች ምርጫ ውጤት እንደሚያሳየው፣ የጠቅይላ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግሥት ቢንያስ ከፓርቲያውቸ ሙሉ ዕምነት፥ ሙሉ ማንዴትና ፍፁም የሆነ የመተማመኛ ድምፅ (vote of confidence) አግኝቷል። ይሄንን ማንዴት በመጠቀም ተጨባጭ እርምጃ በመውሰድ ይኼንን ኃላፊነት ለመወጣት ሥራ የመጀመሪያ ጊዜው አሁን ነው።

ዳይ – ወደ – ሥራ!

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ከተሞች የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሽብር ቡድን በቁጥጥር ስር ዋለ- ትህነግ “ክብሪት” የተባለ ገዳይ ቡድን ማቋቋሙ ታወቀ፣
0Shares
0