የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ከማህበራዊ ህይወታቸው ሳይርቁ የቤት ባለቤት እንዲሆኑ የሚያስችል የመኖሪያ አፓርታማዎች ግንባታ እቅድ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገለፀ።

የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ‘‘በነቃ የወጣቶች ተሳትፎ ያጋጠሙንን ፈተናዎች በማለፍ ዕድገታችንን እናስቀጥላለን’’ በሚል መሪ ቃል ዛሬ ከኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወጣቶች ጋር ውይይት አካሂደዋል።

በዚህ ወቅት እንደገለጹት የከተማዋን ነዋሪ ከማህበራዊ ህይወቱ ሳይርቅ የቤት ባለቤት ማድረግ የሚያስችል የቤት ልማት እቅድ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በቅርቡ ስራ ይጀምራል። ፕሮጀክቱ የከተማዋን ነዋሪ የቤት እጥረት ችግር ለመቅረፍ የተጀመረው የቤት ልማት አካል መሆኑንም ተናግረዋል።

በመሆኑም በእያንዳንዱ ክፍለ ከተማ 36 ሄክታር ላይ የሚያርፉ የመኖሪያ አፓርታማዎች ለመስራት መታቀዱንና በቅርቡ ሥራ እንደሚጀመርም አስታውቀዋል።

የቤት ልማት እቅዱ የከተማዋ ነዋሪ ከማህበራዊ ህይወቱ ሳይርቅ የቤት ባለቤት የሚሆንበትና አርሶ አደሩም ሳይፈናቀልና ወደ ጫፍ ሳይገፋ ተጠቃሚ የሚሆንበትን አሰራር የሚፈጥር መሆኑም ተገልጿል።

በውይይቱ ላይ ከክፍለ ከተማው 15 ወረዳዎች የተውጣጡ ከ2 ሺህ በላይ ወጣቶች የተሳተፉ ሲሆን፥ በክፍለ ከተማው ሁሉም የአስተዳደር እርከኖች የመልካም አስተዳደር ጉድለት፣ ሙስናና አድሏዊ አሰራር መኖሩን የውይይቱ ተሳታፊዎች ገልፀዋል።

በተለይም የሥራ ፈጠራን ለማፋጠን ተብለው በመንግስት የተገነቡ የጥቃቅንና አነስተኛ ማምረቻ ሼዶች ሥራ ለሌላቸው ወጣቶች መሰጠት ሲገባቸው አግባብ ባልሆነ መንገድ ለማይገባቸው አካላት መጠቀሚያ እየተደረጉ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የክፍለ ከተማው ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኢሳያስ ምህረት ክፍለ ከተማው በአዲሱ የመዋቅር ለውጥ የማደራጀት ሥራ መጀመሩን ጠቅሰው፥ በዚህም ከቀበሌ እስከ ወረዳ ያለው የአመራር መዋቅር ተሰርቶ በመጠናቀቅ ላይ ነው ብለዋል።

ወደ ሥራ ያልገቡ፣ የተዘጉ፣ በአድሏዊ አሰራር የተያዙና ለሌሎች መተላለፍ የሚገባቸውን የጥቃቅንና አነስተኛ ሥራ ማስኬጃ ሼዶችን በተመለከተም ጥናት እየተካሄደ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ከዚሁ ጋርም ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ ወጣቶች በእነዚህ ሼዶች ሥራ እንዲጀምሩ ለማድረግ የሚያስችል እንቅስቃሴ እየተካሄደ መሆኑንና በቅርቡም ሼዶቹ ለሚገባቸው ወጣቶች እንደሚሰጡ አንስተዋል።

የከተማው ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ወጣቱ በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ የመንግስት ቤቶችንና ታጥረው የተቀመጡ መሬቶችን ጨምሮ የኪራይ ሰብሳቢነት ባህሪ የሚስተዋልባቸውን አሰራሮች በማጋለጥ ከአስተዳደሩ ጎን እንዲሰለፍ ጥሪ አቅርበዋል።

ፋና ብሮድካስት

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *