“Our true nationality is mankind.”H.G.

ኢትዮጵያ በ2012 በድምሩ 30 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ይኖሯታል ተብሎ ይጠበቃል።

ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ላይ ተሳትፏቸውን እንዲያጎለብቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ።

በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልል አዳማ ከተማ በ140 ሚሊየን ዶላር ወጪ የተገነባው የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመጀመሪያ ምዕራፍ ዛሬ በይፋ ተመርቋል።

በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር የሃገሪቱን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ ልማትን ማፋጠንና ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ማስፋፋት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከውጭ ባለሃብቶች ባሻገር የሃገር ውስጥ ባለሃብቶችም በዘርፉ ተሳትፏቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው ጠቅሰው፥ መንግስትም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን በአፍሪካ የማምረቻው ዘርፍ ማዕከል ለማድረግ የተያዘው እቅድ እንዲሳካም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ መንግስታዊ ተቋማትና ህዝቡ ርብርብ ማድረግ ይገባዋል ብለዋል።

ለአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ መሬታቸውን የለቀቁ አርሶ አደሮችና የአካባቢው ነዋሪዎች የልማት ተጠቃሚነታቸው እንደሚረጋገጥም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኩ መሰማራት ለሚፈልጉና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም መንግስት ልዩ ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ መስፋፋት ለሃገር ኢኮኖሚ መበልጸግና ለማህበራዊ እድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

በሃገሪቱ የሚገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተለይ ለወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠራቸው ባሻገር የቴክኖሎጂ ሽግግር እንደሚያደርጉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።

ወጣቶችም ከአሁን በኋላ ሙሉ ትኩረታቸውን ወደ ልማት እንዲያዞሩም ጥሪ አቅርበዋል።

በመልዕክታቸው አሁን በሙሉ ልብ የምንታገለው ድህነትን ማሸነፍ መሆን አለበት ሲሉም አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ድህነትን ለመታገልና የተጀመረውን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መሰረት ለማስያዝ ህጎችና አሰራሮችን በተገቢው መንገድ ማጠናከር እንደሚገባም አውስተዋል።

የአዳማ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ከሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክና ቀደም ብለው ከተገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልምድ በመውሰድ የተሰራ ነው ያሉት ደግሞ፥ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር አርከበ ዕቁባይ ናቸው።

ፓርኩ ትላልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የሚስተናገዱበት ፓርክ ነው ያሉት ዶክተር አርከበ፥ ከአፍሪካ ትላልቅ የኢንዱስትሪ ፓርኮች አንዱ መሆኑንም አውስተዋል።

አሁን ላይ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚስተዋለውን የሃይል አቅርቦት እጥረት ለመፍታትም በትኩረት መሰራት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

የአረርቲ፣ አይሻ፣ ሰመራ፣ አሶሳ፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚገነባው የዩሮ ስፔስ ማኑፋክቸሪንግና የሁናን አዳማ የማሽን አምራች ኡንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ በዚህ ዓመት የሚጀመር መሆኑንም ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው የኢንዱስትሪ ልማት የሃገሪቱን ገጽታ የሚቀይርና ግብርናን በማዘመን ኢንዱስትሪው መሪነቱን እንዲይዝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው ነው ብለዋል።

ከዚህ አንጻርም መንግስት ለኢንዱስትሪ ልማት ትኩረት በመስጠት በርካታ ስራዎች እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

ፓርኩ ከውጭ ሃገር የሚገቡ ምርቶችን በሃገር ውስጥ ማምረት የሚያስችልና የአርሶ አደሩን ገቢ የሚያሻሽል መሆኑንም በንግግራቸው ጠቅሰዋል።

አቶ ለማ በንግግራቸው ፓርኩ የቴክኖሎጂ ሽግግር የጥናትና ምርምር ማዕከል እንደሚሆን ጠቅሰው፥ ወጣቶችም በአነስተኛና ጥቃቅን በመደራጀት ለፓርኩ ግብዓት እንዲያቀርቡ ሁኔታዎች እንደሚመቻቹም ጠቁመዋል።

የክልሉ መንግስትም ለአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት።

ግንባታው በ2009 ዓመተ ምህረት የአዳማ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በ102 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፥ ለግንባታውም ከ4 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል።

ፓርኩ በተለያየ ዘርፍ ለሚሰማሩ ኩባንያዎች የሚያገለግሉ 19 የመስሪያ ሼዶችን የያዘ ነው።

ከእነዚሀ ሼዶች ውስጥም ስድስቱ በ11 ሺህ ካሬ ሜትር፣ ዘጠኙ በ5 ሺህ 500 ካሬ ሜትር፣ አራቱ ደግሞ በ3 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፉ ናቸው።

የኢንዱስትሪ ፓርኩን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳና እና ሌሎች የክልል ርዕሳነ መስተዳድራን፣ ከፍተኛ የፌደራልና የክልል ባለስልጣናት እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

ፓርኩ በተሟላ ሁኔታ የማምረት ደረጃ ላይ ሲደርስ ከ1 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ ሀገሪቱ ከወጪ ንግድ እንድታገኝ የሚያስል ሲሆን፥ ከ60ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ደግሞ የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

ጃንሱ-ሰን ሻይን በ80 ሄክታር እንዲሁም ኪንግደም በ30 ሄክታር ላይ የሚያርፉ የጨርቃ-ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካዎች ናቸው። ኢትዮጵያ በ2012 በድምሩ 30 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ይኖሯታል ተብሎ ይጠበቃል።

ኤፍ.ቢ.ሲ

0Shares
0