የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የህግና አዋጅ ማሻሻያ እንደሚደረግ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ተናገሩ። ፕሬዚዳንቱ የህዝብ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ 5ኛ ዘመን፣ 4ኛ አመት 1ኛ መደበኛ ጉባኤን ሲከፍቱ ነው ይህን ያሉት።

በንግግራቸው ወቅትም የመንግስትን የ2010 ዓ.ም አፈጻጸምና የ2011 ዓ.ም የትኩረት አቅጣጫዎችን አቅርበዋል። በዚህም አብሮነትና መቻቻልን የሚሸረሽሩ አዝማሚያዎችን ማስወገድና የህግ የበላይነትን ማስከበር፣ የዴሞክራሲና የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት፣ የምርጫ ህጉን በትኩረት ማየት፣ የወጣቱን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፣ በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የነጻ ገበያ መገንባት እንዲሁም በፋይናንሱ ዘርፍ ክትትል በማድረግ ማሻሻያዎችን መተግበር ቀዳሚ አጀንዳ ሆነው ተነስተዋል።

ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ያለፈው አመት እንደሃገር የለውጥ መስመር ውስጥ የተገባበትና በዚያው ልክ በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እቅዶችን ለማሳካት የታለመበት እንደነበር አንስተዋል።

ይሁን እንጅ እቅዱ በነበረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ሳቢያ በታሰበው ልክ አለመሳካቱን ጠቁመዋል፤ ያልተገቡና ኢ – ዴሞክራሲያዊ አሰራሮች የሃገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ሲፈታተኑት እንደነበር በመጥቀስ።

የዴሞክራሲ ስርዓቱን ግንባታ እና የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት፦ መንግስት የዴሞክራሲ ስርዓቱን የማስፋት ስራ በማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ዘላቂ የሰላም፣ የህግ የበላይነት፣ የኢኮኖሚ እድገትና ብልፅግና ለማረጋጋጥ በቀጣይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራባቸውን ነጥቦች ዘርዝረዋል።

የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋትና ቁልፍ የዴሞክራሲ አስተዳደር ተቋማትን ከማጠናከርና የአሰራር ነጻነትን ከማጠናከር አንጻር የታየው ክፍተት ህዝቡ አማራጭ የትግል መድረክና ትርጉም ያለው የሲቪል ማህበረሰብ እንዳይኖር ማድረጉን ጠቁመዋል።

ኢህአዴግ ግምገማና የአመራር ለውጥ በማድረግ ችግሩን መፍታት መጀመሩ በሃገሪቱ ዳግም ተስፋ እንዲታይ ማድረጉን ጠቅሰው፥ ከዚህ አንጻርም መንግስት በተከተለው የይቅርታና የመደመር ጉዞ ዜጎች በሃገራቸው ጉዳይ ላይ ንቁ ታሳታፊ ማድረግ ማስቻሉንም ተናግረዋል።

መንግስትም የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዲከበርና የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ በማሰብም በርካቶችን ከእስር መፍታቱን ጠቅሰው፥ በፖለቲካው መስክ ሰላማዊ የፖለቲካ ውይይት እንዲኖርም የነፍጥ ትግልን መርጠው ከሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ጋር ድርድር መደረጉን አስታውሰዋል።

ለዚህ ደግሞ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምህረት አዋጅ ማጽደቁ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረውም አንስተዋል።

ዜጎችም ተሰባስበው በነጻነት መንቀሳቀስ የሚችሉበትን አግባብ በመፍጠርም ምሁራንና ተሟጋቾችን ጨምሮ ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ተንታኞች በሃገራቸው ጉዳይ ላይ መሳተፍ የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

የህግ የበላይነት ጥሰትን ለመከላከል በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አካላት ይህንን ጉዳይ ልዩ ትኩረት በመስጠት የእያንዳንዱን ዜጋ ደህንነት እና ነፃነት ለማስከበር አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስዱ ገልፀዋል።

መንግስት የዴሞክራሲ ስርዓቱን ለማስፋትም የተጀመረው የማሻሻያ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ጠቅሰዋል።

የዴሞክራሲ ስርዓቱ እንዲጎለብትና አሁን ያሉ መልካም ጅምሮች በዘላቂነት ተቋማዊ ቅርጽ እንዲኖራቸው ለማድረግም አማካሪ ኮሚቴ መቋቋሙንም በንግግራቸው አንስተዋል።

አማካሪ ኮሚቴው በቴክኒክ ኮሚቴ የሚታገዝ መሆኑን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ፥ በበጀት ዓመቱም የፀረ ሽብር አዋጅ፣ የሲቪክ ማህበራትና በጎ አድራጎት ማህበር አዋጅ፣ የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ነፃነት አዋጅን ጨምሮ ሌሎች አዋጆችን የማሻሻል ስራ ይጠናቀቃል ነው ያሉት።

በተጨማሪም የሚዲያ ነፃነት እና ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት መከበር ዙሪያ የተጀመረው አበረታች ለውጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

የምርጫ ህግን በተመለከተም መንግስት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በመሆን የምርጫ ህጉ ዴሞክራሲያዊ እና አሳታፊ እንዲሆን የተጀመሩ የማሻሻያ ስራዎች በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቁ ይደረጋልም ብለዋል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ።

ከዚህ ጎን ለጎንም የምርጫ አስፈፃሚ ተቋማትም በገለልተኝነት ስራቸውን እንዲከውኑ የሚያስችሉ እርምጃዎችን መንግስት እንደሚወስድም አውስተዋል።

ከዚህ ባለፈም ዳያስፖራውን በሃገር ጉዳይ ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ማድረጉን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ ይህ ተግባር በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ፦ በውጭ ዲፕሎማሲው መስክም የኢትዮ ኤርትራን ግንኙነት ማዕከል ያደረገና አዲስና ተስፋ ሰጭ ግንኙነት መከፈቱን ገልጸዋል።

ግንኙነቱ ዘላቂ ሰላም፣ የጋራ ተጠቃሚነትና ኢኮኖሚያዊ ውህደትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ተከናውኖ የሃገራቱ ግንኙነት መቀየሩም በዲፕሎማሲው መስክ የተገኘ ውጤት መሆኑንም በንግግራቸው አብራርተዋል።

ኢትዮጵያም በአጋድ ሊቀመንበርነቷ በሁለቱ የደቡብ ሱዳን ኃይሎች መካከል የነበረው አለመግባባት እንዲፈታና፥ ኤርትራና ጅቡቲን ለማቀራረብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክታለችም ነው ያሉት።

ከዚህ ባለፈም ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሃገራት ጋር ያላትን መተማመን ላይ መሰረት ያደረገ ግንኙነት በማስቀጠል፥ ከባህረ ሰላጤው ሃገራት ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማጠናከር የልማት አጋርነትን መሳብ መቻሉንም አስታውሰዋል።

አህጉራዊ ውህደትን ከማምጣት አንጻር ኢትዮጵያ ለሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ዜጎች የምትሰጠውን የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ለመስጠት ትሰራለች።

እንደ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ገለጻ ቀጠናዊ ትስስርና የኢኮኖሚ ውህደትን ለማምጣትም የድንበር አካባቢ ንግድን ህግን ጠብቆ ይፈጸማል፤ ይህም ለቀጠናዊ ሰላም እንደሚበጅ በመጥቀስ።

ኢጋድን በማጠናከር ወደ ዘላቂ ልማት በማስገባትና ውህደቱን ለማጠናከር ኢትዮጵያ እንደምትሰራ ጠቅሰው፥ በአጭር ጊዜ ቀጠናዊ በረጅም ጊዜ ደግሞ የአቡጃን ስምምነት መሰረት በማድረግ አህጉራዊ ትስስርና ኢኮኖሚያዊ ውህደት ለማምጣት ትሰራለችም ብለዋል።

ግብርና፦ በበጀት አመቱ ዘመናዊ የመስኖ ልማት ማስፋፋትና የግብዓት አቅርቦትን በማሻሻል ምርታማነት እንዲጨምር ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ በንግግራቸው አንስተው፥ አዳዲስ የግብርና ስልቶችን በማቅረብና የገጠር ኮመርሻላይዜሽንን የሚያግዝ ፖሊሲ ለመተግበር ይሰራልም ነው ያሉት በንግግራቸው።

አሁን ላይ በሀገሪቱ ያለውን የህዝብ የምግብ ፍጆታ ለመሸፈን እና የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ለማቅረብ የክትትልና ድጋፍ ስርዓቱም ይጠናከራል።

ንግድና ኢኮኖሚ፦ የግል ባለሃብቱ በኢኮኖሚው ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ የፖሊሲና የህግ ማሻሻያዎች የሚደረጉ ሲሆን፥ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ በተለያዩ ምክንያቶች ተፅዕኖ ስር በመውደቁ ሳቢያ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ ነበር ነው የተባለው።

ከዚህ አኳያም አስፈላጊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስልት መተግበር ይገባል ያሉት ፕሬዚዳንት ሙላቱ፥  የመንግስት ብድር ከተቀመጠው ጣሪያ በላይ እንዳያልፍ እንደሚሰራም አስረድተዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል እንድትሆን በትኩረት የሚሰራ ሲሆን፥ የወጪ ንግዱን ማሳደግ የሚያስችሉ እርምጃዎችም ይወሰዳሉ።

የኢንሹራንስ አሰራርን ለማሻሻልና ተደራሽነቱን ለማስፋትና የገቢ አሰባሰብ እና የመንግስት ገቢና ወጪ አፈፃፀም ላይ ክትትል ይደረጋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም የጉምሩክ ስራ በኤሌክትሮኒክስ በአንድ መስኮት የማድረግና ዘመናዊ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ማሻሻያ እንደሚደረግ ተገልጿል።

ከወጣቶች ተጠቃሚነት ጋር በተያያዘም መንግስት ለስራ እድል ፈጠራና ሃገራዊ ደህንነት በትኩረት እንደሚሰራ አብራርተዋል።

ትምህርትና ጤና፦ በትምህርቱ ዘርፍ የትምህርት ፍኖተ ካርታው ላይ ማሻሻያ በማድረግ ተማሪዎችም ትምህርታቸውን ያለ ችግር እንዲከታተሉ ማድረግ ቀዳሚ እቅድ መሆኑ ተነስቷል።

በጤናው ዘርፍም በተለይም የመሰረታዊ የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ማስፋት ዋነኛው የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ ነው።

ከዚህ ጋር ተያይዞም የእናቶችና የህጻናትን ሞት መቀነስም የበጀት አመቱ የዘርፉ እቅድ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው አስታውሰዋል።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   "በፕሮፓጋንዳ እስካሁን የተወናበድኩት ይበቃኛል ብሎ ቆም ብሎ ማሰብም ይገባል ... ወጣቱን ያለ እድሜው ህይወቱን ይቀጩታል"ሌ.ጀ ዮሐንስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *