“Our true nationality is mankind.”H.G.

ኦሮሚያ በክልል የቢሮዎችን ቁጥር ቀነሰ፤ የዞን፣ወረዳና ቀበሌ አደረጃጀቶች በአዲስ እንዲዋቀሩ ተወሰነ

ጨፌ ኦሮሚያ የክልሉን አስፈጻሚ አካላት መልሶ ለማደራጀትና ስልጣንና ሃላፊነታቸውን ለመወሰን የወጣውን አዋጅ አፀደቀ። የጨፌ ኦሮሚያ በዛሬው እለት እያካሄደ ባለው 4ኛ ዓመት 5ኛ የስራ ዘመን 3ኛ አስቸኳይ ጉባኤ ነው የክልሉን አስፈጻሚ አካላት መልሶ ለማደራጀትና ስልጣንና ሃላፊነታቸውን ለመወሰን የወጣው አዋጅ ያፀደቀው።

በተጨማሪም ጨፌው የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለማቋቋም የወጣው ረቂቅ አዋጅም አፅድቋል። በዚህም መሰረት የኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ ጨፌው በዛሬው እለት ባፀደቀው አደረጃጃት መሰረት የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ተብሎ የሚጠራ መሆኑም ተገልጿል።

የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ በዚሁ ወቅት አንዳሉት፥ የአደረጃጀት ለውጥ ማድረግ ያስፈለገው ባለፉት ጊዜያት በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዳሉ በመለየት የተለያዩ የማሻሻያ ስራዎች ቢሰሩም የህዝብን ቅሬታ መፍታት እና እርካታን መፍጠር ስላልተቻለ ነው።

ይህም በተለይም ከስራ ፍጥነት እና ጥራት ያለው አገልግሎት ከመስጠት ጋር በተያያዘ ክፍተት በማሳየቱ እንዲሁም ተሃድሶ ተብለው የተጀመሩ ስራዎችም የአመራሩን እና የሰራተኛውን አመለካከት ከማደስ ባለፈ እርካታን ባለመፍጠራቸው ነው ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ የሚሰራበት መንገድ መለወጥ እንዲሁም የተጀመሩ ለውጦቸን ለማስቀጠል የሚያስችሉ የመዋቅር እና የአደረጃጀት ለውጥ ማምጣቱ አስፈልጓል ብለዋል።

አዲሱ አደረጃጀተም በዋናነት ህዝቡን ማእከል ባደረገ መልኩ ሰፊውን ህዝብ ማግኘት የሚቻልበትን ቀበሌን ማእከል በማድረግ መስራት የሚያስችል መሆኑንም ገልፀዋል።

እንዲሁም ችግር የሚስተዋልበትን የአስፈጻሚ አካላት አደረጃጀት፣ የሰው ሀይልና በጀት አጠቃቀም ላይ የሚስተዋለውን ሰፊ ክፍተት የሚቀርፍ መሆኑንም አንስተዋል።

ከዚህ በፊት በነበረው አደረጃጀት በክልል ደረጃ 42 የነበሩ ቢሮዎች በዛሬው እለት በፀደቀው አዋጅ መሰረት ወደ 38 ዝቅ እንዲደረጉ መወሰኑንም ርእሰ መስተዳደሩ አቶ ለማ መገርሳ ገልፀዋል።

በአዲሱ አደረጃጀት መሰረትም፦

 

Related stories   ‹‹የህዳሴው ግድብ ለሱዳን ከፍተኛ ጥቅም አለው፤ የቀጠናውን የኢኮኖሚ ትስስር ያጠነክራል››

1. የርእሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት

2. የእርሻ እና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ

3. የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ

4. የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ

5. የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ

6. የትምህርት ቢሮ

7. የጤና ጥበቃ ቢሮ

8. የፀጥታ እና አስተዳደር ቢሮ

9. የውሃ እና ኢነርጂ ልማት ቢሮ

10. የመሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም ቢሮ

11. የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

12. የንግድ ቢሮ

13. የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ

14. የባህልና ቱሪዝም ቢሮ

15. የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ

16. የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ

17. የኢንተርፕራይዝና ኢንደስትሪ ልማት ቢሮ

18. የትራንስፖረት ባለስልጣን

19. የመንገዶች ባለስልጣን

20. የመንግስት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን

21. የአካባቢ፣ የደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን

22. የኮንስትራክሽን ባለስልጣን

23. የማእድን ልማት ባለስልጣን

24. የግብርና ግብአቶች ቁጥጥር ባለስልጣን

25. የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና መገናኛ ባለስልጣን

26. የአርብቶ አደር አካባቢዎች ልማት አስተባባሪ ኮሚሽን

27. የእቅድና ኢኮኖሚ ልማት ኮሚሽን

28. የኢንቨስትመንት ኮሚሽን

29. ፖሊስ ኮሚሽን

30. የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን

31. የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን

32. ስፖርት ኮሚሽን

33. የህብረት ስራዎች ማስፋፊያ ኤጀንሲ

34. የእንስሳት ሀብት ልማት ኮሚሽን

35. የገበያ ልማት ኮሚሽን

36. የግብርና ጥናት ኢንስቲቲዩት

37. የከተሞች ፕላን ኢኒስቲቲዩት

38. የመንግስት ህንፃዎች አስተዳደር በመሆን በአዲስ መልክ ተደራጅተዋል።

እንዲሁም በዞን፣ በወረዳ እና በቀበሌ ደረጃ የነበሩ አደረጃጀቶችም በአዲስ መልክ እንዲዋቀሩ ተወስኗል።

በሰርካለም ጌታቸው -(ኤፍ.ቢ.ሲ) 

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0