“Our true nationality is mankind.”H.G.

ከደቡብ ሱዳን መሳሪያ በገፍ እየገባ ነው፤ በጀቱ የማን ነው?

ደቡብ ሱዳን ላይ አንድ የተረጋጋ መንግስት እንዲኖርና ሰላም እንዲሰፍን ኢትዮጵያ የምትችለውን ሁሉ ልታደርግ እንደሚገባ እምነት አለ። እምነቱ ግን ወደ ግራና ቀኝ እየተጎተተ የተፈለገውን ውጤት ሊያመጣ አልቻለም። ከአገራዊ አጀንዳ በላይ ንግድና የፖለቲካ ቁማርና ኪስ ማደለቢያ ተደርጎ መወሰዱ የደቡብ ሱዳን ሰላም ታጥቦ ጭቃ እንደሆነ በገሃድ የታየ ነው።

ፕሬዚዳንቱ ሳልቫኪር ሳይሆኑ በሌላኛው ወገን የሳቸው ባላንጣ የሆኑት ሪክ ማቻር እጃቸው እስከ ጋምቤላ ድረስ የተዘረጋ ነው። የኑዌር የጎሳ አባል የሆኑት ሪክ ማቻር ማዕከላዊ መንግስት ሳያውቅ ጋምቤላ ቤተ መንግስት ተንፈላሰው መመለሳቸውን የሚያስታውሱ አሁን ካሉት የጋምቤላ መሪ ጋር ቅርብ የሆነ ግንኙነት እንዳላቸው፣ በሳቸውም አማካይነት በማዕከል ደረጃም ሪክ ማቻር ገመድ እንዳላቸው ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ይናገራሉ።

ጋምቤላ ከውስጥ ይልቅ ተሻግሮ እንዲገባ በተፈቀደ የደም ትሥሥር አማካይነት ችግር እንደሚከሰት ስጋት ቢኖርም አሁን ይብልጥ አሳሳቢ የሆነው በሪክ ማቻር ዙሪያ ያሉ ክፍሎች መሳሪያ በገፍ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ እያደረጉ መሆናቸው ነው። ” እለፈኝ ” ሲል ስሙን የማይናገረው የጋምቢላ ነዋሪ ለዛጎል እንደሚናገረው ከደቡብ ሱዳን መሳሪያ እየገባ ነው። ጋምቤላን የሚመሩት ክፍሎች ይህንን ያውቃሉ።

ለኢትዮጵያ እና ቀደም ላሉት መሪዎች ክብር ያላቸው ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር በዚህ ተግባር እንደማይታሙ ለማንም ግልጽ እንደሆነ የሚናገረው የጋምቤላ ነዋሪ፣ የጋምቤላ በይፋ ያለመደመርና ለውጡን ያለመቀበል ችግር ዋና ምንጭ ከሌብነት ባሻገር ማን በጀት እንደሚቆርጥለት የማይታወቀው የመሳሪያ ዝውውር ጉዳይ ነው።

በጋምቤላ አድርጎ ወደ አገሪቱ መዕራባዊ ክፍል መሳሪያ ለማሰራጨት የሚሰሩ እንዳሉ ጥቆማ የሚሰጠው ይህ ወጣት የጋምቤላ አስተዳደር ጉዳዩን በደንብ ያውቀዋል ባይ ነው። ስም ዘርዝሮ እንዳስታወቀው ከሆነ ጉዳዩ ጥንቃቄ የሚያሻው ነው። በዚህ ከጀርባው በግልጽ የማን እጅ እንዳለበት በውል የማይታወቀው የመሳሪያ ዝውውር የተወሰኑ የጎሳ ቡድኖችን በነብስ ወከፍ እንዲታጠቁ አድርጓቸዋል።

በክልሉ የበታቸ አመራር ሆኖ የሚሰራ እንዳለው በጋምቤላ ላይ አሁን የመከላከያ ሰራዊት ከወጣቶች፣ ሰላም ወዳድ ከሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችና ተሰሚነት ካላቸው አክቲቪስቶች ጋር እያደረገ ያለውን የቁጥጥር ስራና ችግሮች ሳይባባሱ እንዲቋጩ ማድረጉን ያደንቃሉ። ይሁን እንጂ የራስን ችግርና ሌብነት፣ ከዛም አልፎ ከጀርባ በሚደረግ ግፊት የሚከናወኑ ተጋባራት ሙሉ በሙሉ እንዳልተገቱ ይናገራል።

በጋምቤላ በኩል መሳሪያ ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ ማን እንደሚያጋግዝ ስም ጠርቶ መናገር ባይችልም ሁሉም ጉዳይ ሚስጢር አለመሆኑንን  አይክድም። እናም አሁን እንደተጀመረው አጠናክሮ በመስራትና ህዝብን በማደራጀት ጋምቤላን መደመር ለአፍታም ቸል የማይባል ጉዳይ እንደሆነ ያሳስባል።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   “አቡነ ማቲያስ የሰጡት መግለጫ የግላቸው እንጂ የቅዱስ ሲኖዶስ ወይም የቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ አይደለም”
0Shares
0