‹‹በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በቂ የኩላሊት እጥበት መሳሪያ ባለመኖሩ ህይወታችን አደጋ ላይ ነው፡፡›› የኩላሊት ህሙማን

ባሕር ዳር፡ መስከረም 28/2011 ዓ.ም(አብመድ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የኩላሊት እጥበት ክፍል የኩላሊት ህሙማን የእጥበት ህክምና እንዲያገኙ ታስቦ ጥቅምት 2/2009 ዓ.ም ነበር የተቋቋመው፡፡

አገልግሎቱን የጀመረው በሶስት የኩላሊት እጥበት ማሽኖች ነበር፡፡ በወቅቱ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉ የኩላሊት እጥበት መስራት መጀመሩን የሰሙ የአካባቢው ነዋሪዎች ከፍተኛ ደስታ ተሰምቷቸውም ነበር፡፡ በተለይ የኩላሊት ህመም ያለባቸው ሰዎች፡፡ አሁን ግን ማዕከሉ የተሟላ አገልግሎት መስጠት ባለመቻሉ ህሙማኑን ጭንቀት ውስጥ እንዲወድቁ አድርጓቸዋል፡፡

አገልግሎት ይሰጡ ከነበሩት ማሽኖች መካከል አንደኛው ሙሉ ለሙሉ ስራውን አቁሟል፡፡ ሌላኛው የተለየ የጤና ችግር ገጥሟቸው የኩላሊት እጥበት ለሚያደርጉ በሚል ሌሎች ህሙማን አይጠቀሙበትም፡፡ አንደኛው ብቻ ነው አብዛኛው ህሙማን የሚጠቀሙበት፡፡ የሚሰራውም ቢሆን በተደጋጋሚ ለብልሽት ስለሚዳረግ አገልግሎቱ የሚቋረጥበት ይበዛል፡፡
በማዕከሉ 19 ቋሚ እጥበት የሚደረግላቸው ህሙማን ሲኖሩ በድንገተኛ እና በተመላላሽ የኩላሊት ህክምና አገልግሎቱን የሚያገኙት በርካታ ሰዎች በአንድ ማሽን ታግዘው እጥበት ለማግኘት የግድ በተራ መጠቀም እንደሚኖርባቸው የኩላሊት እጥበት ክፍሉ ቡድን መሪ ሲስተር ፍሬ ህይዎት ገልፀውልናል፡፡ አንድ ህመምተኛ አስከ አምስት ሰዓት ሊወስድ የሚችል የእጥበት ሂደት ማሳለፍም ይኖርበታል፡፡ 
አንድ የኩላሊት ህመምተኛ ሰው የመኖር ተስፋውን ለማለምለም በሳምንት ለሶስት ጊዜ እጥበት ማግኘት እንደሚጠበቅበት ደግሞ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ የማሽን እጥረቱ ግን ይህን ማድረግ የሚያስችል አይደለም፡፡
ከእጥበት መስጫ ማሽኖች እጥረት በተጨማሪ ለዕጥበቱ የሚያስፈልጉ ኬሚካሎች አለመሟላት ሌላው የስራው ተግዳሮት ነው፡፡
ወይዘሮ የሻሽ ወርቅ በላይ የኩላሊት ህመም ገጥሟቸው የእጥበት ህክምና ከጀመሩ ስምንት ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ለአንድ ጊዜ እጥበት እስከ 1ሺህ 5 መቶ ብር እየከፈሉ በሳምንት ሶስት ጊዜ አገልግሎቱን ይጠቀሙ ነበር፡፡ አሁን ግን የህክምና ወጭ ለማግኘት በመቸገራቸው በሳምንት ለአንድ ጊዜ ብቻ ይታጠባሉ፡፡
ያም ሆኖ ማሽኑ በመበላሸቱ በሳምንት ኩላሊታቸውን ለመታጠብ የሚያስቸግሩ ሁኔታዎች በዝተዋል፡፡ ሁኔታውም አሳስቧቸዋል፡፡
ወጣት ናስር አህመድ የኩላሊት እጥበት ለማግኘት በመቸገራችን ህይወታችን አደጋ ላይ ነው ሲሉ ሀሳባቸውን ካካፈሉን ህሙማን አንዱ ነው፡፡

‹‹በቅርቡ ማዕከሉ አገልግሎት መስጠት በማቆሙ እኔ እና ሁለት የኩላሊት ህሙማን ባሕርዳር ከተማ ወደ ሚገኘው ፈለገ ህይወት ሆስፒታል አመራን ፤ ተገቢውን የህክምና አገልግሎት ማግኘት ባለመቻላችን ከመካከላችን አንዱ ታካሚ ህይወቱ አለፈ፡፡ የኛም እድል ከዚህ ያለፈ አይሆንም ሲል ብሶቱን አጫውቶናል፡፡››
ዶክተር ፍስሃ አድማሱ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ዳሬክተር ናቸው፡፡ የኩላሊት ህመምተኞች ያቀረቧቸው አቤቱታዎች ትክክል መሆናቸውን ነግረውናል፡፡
የኩላሊት እጥበት ማሽን እጥረቱን ለመቅረፍ በያዝነው ዓመት ከ5 እስከ 6 አዳዲስ ማሽኖችን ለማስገባት እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ቀሪ ሶስት ማሸኖችን ደግሞ ከጳውሎስ ሆስፒታል ለመረከብ ስምምነት ተደርጓል ነው ያሉን፡፡ 
ዶክተር ፍስሃ የህሙማኑን ህይወት ለመታደግ ተጨማሪ የማሽኖች ግዥ አስፈላጊ መሆኑን ቢናገሩም የግዥ ስርዓቱ ቢሮክራሲያዊ አሰራር ለችግሩ መባባስ ዋነኛው መንገድ ነው ይላሉ፡፡

ለኩላሊት እጥበት የሚያገለግሉ ኬሚካሎች አቅርቦት ገበያ ላይ አለመኖር ደግሞ ሌላኛው ችግር ነው፡፡
ማዕከሉ የተሟላ አገልግሎት እንዳይሰጥ እንቅፋት እየፈጠረ ነው፡፡ የአቅራቢ የንግድ ድርጅቶች አቅምም አጠያያቂ መሆኑን ዶክተር ፍስሃ ተናግረዋል፡፡ የሰውን ህይወት ከሞት ለመታደግ የግዥ ስርዓቱን ስንከተል መድሃኒቶች ያልቃሉ፡፡ ይህን ለመቅረፍ አዲስ አሰራር መዘርጋት እንዳለብን ተስማምተናል ነው ያሉን፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለኩላሊት እጥበት የሚያገለግሉ ዘመናዊ ህክምና ማሽኖች አለመኖሩ በዓሰራር ስርዓታችን ላይ ተፅዕኖ ፈጥሮብናል የሚል መልስ ይስጥ እንጅ ሶስት ምንም ያልተሰራባቸው ዘመናዊ የኩላሊት እጥበት ማሽኖች አገልግሎታቸውን ያልጨረሱ ከወዳደቁ ቁሳቁሶች ጋር ተቀላቅለው መመልከት ችለናል፡፡
በርካታ ገንዘብ ወጥቶባቸው የተገዙ የህዝብ ንብረቶች ግልጋሎት ሳይሰጡ ተበላሽተው መውደቃቸው ምክንያቱ ምንድን ነው ስንል ስለ ጉዳዩ ዶክተር ፍስሃን ጠይቀናቸዋል፡፡
በመድሀኒት ፈንድ ኤጀንሲ ተገዝተው አገልግሎት ያልሰጡ ማሽኖች መሆናቸውንም ዶክተር ፍስሃ ገልጸውልናል፡፡የማሽን ማስቀመጫ ቦታ አመቻችተን አገልግሎት የሚሰጡበትን መንገድ እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
መሆን አልቻሉም፡፡ 
ዘጋቢ፡-ሀይሉ ማሞ amara mass media

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የዓለም ጤና ድርጅት ለቻይናው ክትባት ይሁንታውን ሰጠ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *