“Our true nationality is mankind.”H.G.

“ከዚህ ፕሮግራም ሴራ ጀርባ ብዙ ቡድኖች ይታዩኛል …”

Melat Atnafu

በመጀመሪያ ደረጃ አዘጋጇን Betelhem Tafesse ሴቶች በአገራችን በሁሉም የሙያ ዘርፍ ተፅኖ ፈጣሪ ቢሆኑ አገራችንን የተሻለ ደረጃ ያደርሳታል ብላ እንደምታምን አንድ ግለሰብ ላበረታታሽ እወዳለሁ:: ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ስታጠፊ ወይም ከሙያ ስነምግባር ባፈነገጠ መልኩ በተጠና በተሰላና እና አድሏዊ በሆነ ሁኔታ ሙያሽን ተጠቅመሽ ሸፍጥ ስትፈፅሚ አስፈላጊዉን ሒስ በመስጠት ቢቻል ሙያዊ ስነ ምግባርሽን ተከትለሽ በጋዜጠኝነት ነጥረሽ እንድትወጭ ማድረግ ያለብን ይመስለኛል:: ይህንን የምልሽ በExodus ቴሌቪዠን ከምታቀርቢያቸዉ ሐይማኖታዊ ፕሮግራሞች ጀምሮ አሁን ላይ በLTV እስከምትሰሪቸዉ ፕሮግራሞች ድረስ የተወሰኑትን ስላየሁ በቅንነት ከተጠቀምሽበት በዉስጥሽ እምቅ ችሎታ እንዳለሽ ስለተገነዘብኩ ነወ:: ሴት ልጅም መበረታታት እንዳለባት አብዝቼ ስለማምን ነዉ!
ፕሮግራሞችሽ ላይ እንደተመለከትኩት ጥሩ ነገር እንዳለሽ ሁሉ አንቺ ያልተመቸሽን ሰዉ እንዴት እንደምታጠቂ የተመቸሽን ደግሞ እንዴት እንደምትክቢ ወይም እራሱ ወይም ሁኔታወች እንዲክቡት እንደምታደርጊ በተደጋጋሚ አይቻለሁ::
ዛሬ ማተኮር የምፈልገዉ በLTV ትላንት ከአብን መሪ ዶ/ር
Dessalegn Chanie Dagnew ጋር ባደረግሽዉ ቆይታ ላይ ነዉ ::
በመጀመሪያ ደረጃ የአብን መሪ ወደ ፕሮግራምሽ ስትጋብዣቸዉ ድርጅቱ በኢትዯዺያ ታሪክ በአጭር ጊዜ ዉስጥ በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ፣ አባላትን በማሰባሰብ ፣ ብዙ ቅርጫፍ ቢሮወችን በመክፈትና ከፍተኛ ቁጥር ባለዉ ህዝብ ተቀባይነትን ከማግኜቱ አንጻር ዉይይታችዉ ያተኩራል ብየ ያሰብኩት በፓለቲካ ፕሮግራማቸዉ ላይ ፣ ከፍተኛ ድጋፍ የቸራቸዉን የአማራ ህዝብ የማንነት እና የህልዉና ጥያቄዎች ከሌላዉ ማህበረሰብ ጋር በማጣጣም እንዴት ሊፈቷቸዉ እንዳሰቡ ፣ ዉስብስብና በሴራ የተተበተበ የአማራ ህዝብን ችግር የመፍታት ድርጅታዊ አቅማቸዉ ምን ያህል እንደሆነ ፣ ዉጥንቅጧ የወጣዉን ኢትዯዺያን ለማረጋጋት የሚያበረክቱት አስተዋጾ ምን ሊሆንና እንዴት ሊሆን እንደሚችል እና ተመሳሳይ ተለቅ ተለቅ ያሉ ጉዳዯች ላይ ያተኩራል ብየ ነበር:: ነገር ግን እጂግ ከጠበኩት በታች ቃላቶችን ከረጅም ንግግሮችና ቃለመጠይቆች መካከል መዞ በማዉጣት እና ከቀረቡበት አዉድ ዉጭ ተተርጉመዉ እንዲታዩ በማድረግ ሴራ ስትሰሪና እጂግ በወረደ መልኩ በተራ አሉባልታ ላይ ስታታተኩሪ እና በዚህ ዉስጥም ማስተላለፍ የፈለግሽዉን ተራ ፕሮፓጋንዳና ሴራ ስመለከት እንደ አማራ ብቻ ሳይሆን እንደማንኛዉ ተመልካች ከልቤ አዝኜብሻለዉ!
አንቺ በዚህ ዉይይት ዉስጥ ማስተላለፍ የፈለግሽዉ መልክት እኔ እንደተረዳዉት አጠር አድርጌ ለማስቀመጥ ያህል
1ኛ . አብን ለኢትዯዺያዉያን ጠብ አጫሪ ፣ አግላይ ፣ ትምክህተኛ እና ኢትዯዺያዊ ስሜትን የሚንድ ድርጅት አስመስሎ በመሳል በዚህ ድርጅት በተወሰነ መልኩ የሚቀነቀነዉን የአማራ ብሔርተኝነት ላይ ጥርጣሬ መፍጠር አላማ ያነገበ ነበር::
ይህ እጅግ ሞራል የጎደለዉ አካሄድ ለረጅም አመታት በአማራ ህዝብ ላይ በህወሃትና ኦነግ የተነዛዉን ፀረ-አማራ ፕሮፓጋንዳ እና ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ በአብን ሆነ በአማራ ብሔርተኝነት ላይ በሐሳዊዉ የአንድነት ቡድን ግምቦት ሰባት የሚነዛዉ ፀረ ኢትዯዺያዊና አፍራሽ አቋም አላቸዉ የሚለዉን ከአማራ ፍራቻና ጥላቻ የተመሰረተ መሰረት ቢስ ክስ አስተባብሮ እዉነት መሆኑን ለማሳየት የተሞከረ ሴራ ነበር!
2ኛ. የድርጅቱን መሪዎች የፓለቲካ ብስለት የሌላቸዉ በስሜት የሚመሩና ግብተኞች አስመስሎ ማሳየትና በአመራሮቹ መካከል መከፋፈልና መቃቃር እንዲነግስ ለማድረግ የተደረገ ሙከራ ነበር::
በተለያዩ ቦታወች የተነገሩ ነገሮችን ከረጅም ፁሁፍና ንግግሮች መካከል መዞ በማዉጣትና ከተጠቀሱበት አዉድ ዉጭ የተለየ ትርጉም ያላቸዉ አስመስሎ በማቅረብ ድርጅቱን ለማሳጣት ከመሞከር በተጨማሪ ዶ/ሩ ማብራሪያ ሲሰጡ በማዋከብ ልክ አንዳች አገር የሚንድ ስህተት እንደሰሩ አሳምኖ በተደጋጋሚ ይቅርታ ጠይቁ ብሎ በመገፋፋት ስህተታቸዉን ስህተት ነዉ ብለዉ አምነዋል ብሎ ለማሳየት የተደረገ ሙከራ በግልፅ አይተናል:: ዶክተሩ ይቅርታ ጠይቁ ለተባሉት ሁሉ እንደተፈለገዉ ይቅርታ ጠይቀዉ ቢሆን ኖሮ ድርጅቱ እስከዛሬ በስሜት ተገፋፍቶ አገር አፍራሽ ስራ ሲሰራ የኖረና ለዚህም ይቅርታ የሚጠይቅበት ሚዲያ እንደተዘጋጀለት አስመስሎ የፓለቲካ ፕሮፓጋንዳ ለመስራት እቅድ የነበረ ያስመስላል::
ሌላዉ ነገር ደግሞ ዶ/ሩ ስህተት ናቸዉ እንዲሉ ይቀርቡላቸዉ ከነበሩት ክሶች መካከል በሌሎች አመራሮች የተነገሩ ያሉበት ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ ዶ/ሩ እንደታሰበዉ ይቅርታ ጠይቀዉ ቢሆን ኖሮ አመራሮቹ የማይናበቡ እና በመሰለኝ እና ደሳለኝ የሚንቀሳቀሱ አስመስሎ ከማሳየት በተጨማሪ በአመራሮቹም ላይ ክፍተት ለመፍጠር ታቅዶ እንደነበር ያሳብቃል!
3ኛ . የአማራ ህዝብ የትግል ጥያቄ መነሻዎችን መሰረት ቢስ አስመስሎ ማሳየት እና በአማራ ህዝብ ላይ የተቃጣ የስነ ልቦና ጦርነት ማድረግ
በመጀመሪያ ደረጃ የህልዉና ስጋትን በቁጥር ብቻ በመመንዘር የተመለከትሽበት አካሄድ ትክክል አይመስለኝም :: አንድን ህዝብ እንደ ህዝብ ማንነቱን የሚያስቀጥሉ እርሾዎች ላይ የማያባራ ጦርነት ከፍቶ እርሾዎቹን በማጥፋት ቀሪዉን ህዝብ እንደ ባሪያ በመግዛት የተጀመረዉን አገር የማሳጣትና ቁጥሩን የመቀነስ ስራ በረጅም ዘመን መስራት ፣ ታሪክና ማንነቱን በማሳጣት ገባር ህዝብ አድርጎ ሌላ ማንነት መጫን የህልዉና ጥቃት እንደሆነ ቤቲ ቤቲ ስተሸዋል ብየ አላስብም!
የአማራ ህዝብ ለዘመናት የማንነት መገለጫወቹና ሊህቃኖቹ ላይ ጥቃት ደርሶበታል:: ታሪኩን ፣ ማንነቱ እና ስነልቦናዉን ከፍ የሚያደርጉ እሴቶቹ እና አሻራወቹ ላይ ከፍተኛ የሆነ የማጥላላት ዘመቻ ተካሂዶበታል:: ታሪኩን እና ባህሉን የመሻማት እና የመቀማት ዘመቻ ተካሂዶበታል:: በማህበረሰቡ ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸዉ የሐይማኖት አባቶች ፣ የሐገር ሽማግሌዎች ፣ የጦር አበጋዞች ፣ ሙሁራን ፣ የኪነጥበብ ባለሞያወች ፣ ነጋዴዎች ፣ ፓለቲከኞች እና ሌሎች ተፅኖ ፈጣሪዎች ሁሉ እየታደኑ ተገድለዋል ፣ ታስረዋል ፣ ደብዛቸዉ ጠፍቷል ወይም አገር ለቀዉ እንዲሰደዱ ሆኖል :: ተተኪዉን ትዉልድ የአማራ ወጣትም በተመሳሳይ መልኩ በማጥቃት እና እንዳይማር በማድረግ ጥቃት ተፈፅሞበታል:: ይህ የረጅምና እና የአጭር ጊዜ ግብ አንግቦ የአማራን ህዝብ ሊህቃንን የማጥፋት ዘመቻ የተካሄደዉ ህዝቡን ለማጥፋት በመጀመሪያ ሊህቃኑን አጥፍቶ ቀሪዉ ህዝብ ለእርድ በሚፈለግበት ሁሉ እሽ ብሎ ይጎተታል በሚል የተጠና ስልት ነዉ::
ከዚህ በተጨማሪም በበሽታ በተለየ ሁኔታ እንዲጠቃ ፣ በከፍተኛ ድህነት እንዲማቅቅ ፣ በየ አካባቢዊ በጥላቻና በጥርጣሬ እንዲታይ ፣ እንዲገደል ፣እንዲፈናቀል ፣ ሴቶች እንዲመክኑ ፣ የህፃናት ሞት በተለየ ሁኔታ እንዲጨምር የሆነዉ እኮ በደንብ በተሰላና በተቀነባበረ ቀመር ነዉ::
በኢትዯዺያ የተደረጉ የህዝብ ቆጠራወችን ለተመለከተ ሰዉ የአማራ ህዝብ ቁጥር እድገት ከሌሎች ብሔሮች ጋር ሲነፃፀር ከሚጠበቀዉ በታች መሆኑ ምንን ያሳያል?
በቆርጦ ቀጥልነቱ እና በክህደቱ ለዘመናት የሚታወቀዉ ፓርላማ እንኳን እኮ 2.5 ሚሊዯን አማራ ጠፋብኝ ብሎ ሲያፈላልግ እንደነበር ቤቲ አልሰማሽ ይሆን?
ባጠቃላይ የአማራን ህዝብ ባህሉን በመንጠቅ ፣ ታሪኩን በሐሰት ጥላሸት በመቀባትና በመቀራመት ፣ እርስቱን በመቀማት ፣ ሊህቆቹን በማጥፋት ፣ በበሽታ በመግደል ፣ በማምከን ፣ ከርስቱ በማፈናቀል ፣ በመግደል ፣ በማደህየት ፣ ፓለቲካዊና ወታደራዊ ስልጣን በማሳጣት ተዘርዝሮ በማያልቅ ማንነቱና ህልዉናዉ ላይ የተቃጣ ጥቃት እንደተፈፀመበት የሚታወቅ ፀሐይ የሞቀዉ ሐቅ ነዉ!
ቤቲ እነዚህን የህልዉና ፈተና የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃወች እንዳሉ እያወቅሽ ለዘመናት የአማራ ህዝብ ላይ የስነ ልቦና ጦርነት በመክፈት የሚታወቀዉ የአማራ ቴሌቪዠን የሰራዉን ከዚህ ግባ የማይባል ትርጉም የማይሰጥ አርሶ አደሮች ለምን ጫማ አያደርጉም የሚል ቪዲዯ ቀንጭበሽ በማሳየት ዶ/ሩን ለማሸማቀቅ ከመሞከር በተጨማሪ ለሰፊዉ የአማራ ህዝብ ያለሽን ንቀትም አሳይተሽበታል!
ከአንድ ሐላፊነት ከሚሰማዉ ሴት ጋዜጠኛ የምጠብቀዉ ግን ልጅ መዉለድ አቃተን ብለዉ በየፀበሉ ልጅ ለመዉለድ ስለሚንከራተቱ የአንድ አካባቢ ሰዎችን የሚያሳይ ቪዲዯን እንደ ግባት ለመጠቀም እንድትሞክር ነበር ፣ 2.5 ሚሊዯን አማሮች ጠፉብን ብሎ የኢትዯዺያ ፓርላማ ግራ ገብቶት ሲወያይ የነበረዉን ቪድዯ እንደ ግባትነት እንድትጠቀም ነበር ፣ በሁሉም የአገሪቱ ኮርነሮች የአማራ ህዝብ መገደሉንና መፈናቀሉን የሚያሳዩ መረጃዎችን እንድትጠቀም ነበር! ቤቲ ግን በአማራ ህዝብ ላይ የሚሳለቅ ቪድዯ በማሳየት በህወሃት ዘመን ሲከፈትብን የነበረዉን የስነ ልቦና ጦርነት አቅርበሽ ተሳልቀሽብናል!
ከዚህ በተጨማሪ ከፍተኛ ግርምት የፈጠረብኝ ደግሞ የአማራ ህዝብ ጥያቄየን ያስተጋባልኛል ብሎ ከገጠር እስከ ከተማ ከፍተኛ ድጋፍ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ከተሰጠዉ ድርጅት መሪ ይልቅ እራስሽን እንደ አማራ ህዝብ የልብ አዋቂ አድርገሽ “ህዝቡ ለነገሩ የህልዉና ስጋት አለብኝ አይልም እናንተ ነዉ የምትሉት” ማለትሽ ነዉ:: incredible!
4ኛ. የአማራ ብሔርተኝነትን በማጥላላት የአማራ ሊህቃንን ወደ ነበሩበት የዩሉንታና ጠላት ከማፍራት ዉጭ ምንም ወዳልፈየደዉ ሐሳዊ የአንድነት ቡድን ተመልሰዉ እንዲገቡ ለማድረግ የተረገ የማሸማቀቅ ሙከራ ነዉ!
የግንቦት ሰባትን ስም ታጠፋላችሁ ፣ ለምን የአማራ ሙስሊምን ብቻ ለይተህ የእንኳን አደረሳችሁ መልክት አስተላለፍክ …ይቅርታ ጠይቅ እና ሌሎች መሰረተ ቢስ እና ትርኪ ምርኪ ክሶችን ስታቀርቢ ነበር የዋልሽዉ::
ቤቲ አንድ ነገር ያልተገነዘብሽዉ ወይም ሆን ብለሽ ያለፍሽዉ ነገር ግን አለ ይህም አብን እያንፀባረቀዉ ያለዉ እንደ ኤርታሌ ከሚንቀለቀለዉ የአማራ ብሔርተኝነት ዉስጥ አንድ ሺኛዉን እንኳን እንዳልሆነ ነዉ!!!
የአማራ ህዝብ ፍፁም አስተዋይ የሆነ ልበ ብርሐን ህዝብ ነዉ:: አንድ ነገር ሲወስን ከብዙ አቅጣጫ መርምሮና አመዛዝኖ ነዉ! ከወሰነ ደግሞ ምንም የምድር ሐይል አያስቆመዉም! አብን ከጀመረዉ የብሔርተኝነት ጉዞ እንኳን ወደ ሆላ ማፈግፈግ ይቅርና ባለበት እንኳ ቢቀጥል በካልቾ ይጠለዛል! ስለዚህ ማንም ሐይል የአማራ ብሔርተኝነትን ከግቡ ሳይደርስ ሊገታዉ አይችልም! አንቺም ሆነ ይህንን ሴራ አብሮሽ የጎነጎነዉ ሐይል ይህንን ጠንቅቆ ሊያዉቀዉ ይገባል !
ቤቲ በአብን እና በአማራ ህዝብ ላይ ያሳየሽዉን መስመር የለቀቀ የተንሸዋረረ ፕሮፓጋንዳ በቅርብ ጊዜ ከጀዋር መሐመድ ጋር አድርገሽዉ ከነበረዉ ዉይይት ጋር በማነፃፀር ምን ያህል አድሏዊ መሆንሽን መገንዘብ ይችላል::
ጀዋር መሐመድ በግሉ በተደጋጋሚ ብዙ አወዛጋቢ ነገሮችን በመናገር ይታወቃል:: ከነዚህ ዉስጥ ለመጥቀስ ያህል… ኢትዯዺያ ከ”ኦሮሚያ” ትዉጣ ፣ “ኦሮሚያ” ነፃ ትሁን ፣ ባደኩበት አካባቢ አንድ ከጎንደር የመጣ ክርስቲያን ቀና ብሎ ቢያየን በሜንጫ አንገቱን ነዉ የምንለዉ ፣ ኦሮሞዎች ከሐበሾች ተለይተዉ የሚያመልኩበት የራሳቸዉ መስጊድ እና ቤተክርስቲያን ሊኖራቸዉ ይገባል..እና ብዙ ለመጥቀስ የሚያዳግቱ ነገሮች ተናግሮል!
ሰዉየዉ ምንም ሳይዘባርቅ አንድ ጥሩ ነገር ያወራበትን ጊዜ አላዉቅም :: በግልፅ ደጋግሞ “ኦሮምያን” መገንጠል አስፈላጊና አዋጭ ከመሰለን እናደርገዋለን ብሎ ተናግሮል::
እሱ በሚመራዉ OMN ቴሌቪዠን በተለያዩ ሰዎች እንዲህ ተብሏል
*አዲስ አበባ ከባለቤቱ ከኦሮሞ ህዝብ የተነጠቀችና በሴተኛ አዳሪዎች ፣ ሌቦች ፣ ዱርየዎችና ፓሊሶች የተሞላች የኦሮሞ ህዝብ ብቻ አገር ናት :: ኦሮሞ ከተማዉንና ጥቅሙን ሊያስመልስ ይገባል
*ኦሮሞ ከአበሻ ጋር መጋባት ማቆም አለበት እና ሌሎች እጂግ ብዙ አስፀያፊ ነገሮች ተብለዋል :: ነገር ግን ዶ/ር ደሳለኝን .. የሚመራዉን ድርጅትና.. የወከለዉን የአማራ ህዝብ ላይ ያደረግሽዉን ማንጏጠጥ ፣ ማዋከብ እና የማጠልሸት ሴራ ቅንጣቱን ያክል እንኳ በጀዋር እና በሚዲያዉ የተስተጋባዉን አይን ያወጣ ህዝብን ከህዝብ የሚያፋጅ ፍረጃዎች እና ንግግሮች አንዱንም ማብራሪያም አልጠየቅሽበትም …ይቅርታም ጠይቅም አላልሽዉም !
ለይምሰል ጀዋር አብይን ወራዳ ብሎ የሰደበዉን እንኳ እንዲያብራራ ጠይቀሽዉ ትላንት የተወለደ ልጅን የማያሳምን መልስ ሲሰጥሽ ምንም ሳትይ በመሽቆጥቆጥ ነዉ ያለፍሽዉ:: ጀዋር አብይን ወራዳ ያልኩት ለትግሉ ስልት ነዉ ብሎ ቀልዶ ሲያልፍ ዝም ነዉ ያልሽዉ!
ባጠቃላይ ግን ዶ/ር ደሳለኝ በራሱ በድርጅቱ እና በሚወክለዉ የአማራ ህዝብ ላይ የተቃጣበትን ሴራ በተረጋጋና ፍፁም በአማራዊ ስነ ምግባር መክቶታል የሚል እምነት አለኝ:: የዶ/ር ደሳለኝ ቆይታ ከጋዜጠኛዋ ግልፅ የሆነ ደባ ሲመዘንና እና ለሚድያም ብዙ ልምድ የሌለዉ ከመሆኑ አንፃር በቃለ ምልልሱ የነበረዉን ቆይታ ረክቸበታለሁ:: ለእርሱ ያለኝም ክብር ጨምሮል! አንድ ግን ትንሽ መሻሻል ያለበት የሚመስለኝ ነገር ግን ይሉንተኝነት አሁንም ያለበት ይመስለኛል:: ዶ/ር ደሳለኝ በፍፁም እንደ አሸዋ ለበዛዉ ጠላታችን ይሉኝታ ሊኖርህ አይገባም! የአማራ ሙስሊምን እንኳን አደረሳችሁ ማለትህም ይቅርታ የሚያስብል ነገር አልነበረዉም!
ዶ/ር እንደ ኤርታሌ የሚንቀለቀለዉን የአማራ ብሔርተኝነት ስሜት ምንም ሳታስቀር በቻልከዉ መጠን አስተጋባዉ! በይሉንታ ያተረፍነዉ መገደልን ብቻ ነዉ:: ሞትን በአማራ ብሔርተኝነት ድል እንንሳዉ!
በመጨረሻ ከዚህ ፕሮግራም ሴራ ጀርባ ብዙ ቡድኖች ይታዩኛል! የዚህ ቴሌቪዠን ባለቤት Dr. Gemchis Buba ሆነ የፕሮግራም ሐላፊዉ ነገሩን ይበልጥ እንደሚመረምሩት ተስፋ እናደርጋለን!
Melat Atnafu

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   ሕዝብን ማን ይሰራዋል?
0Shares
0