ከቀናት በፊት ከህግና ደንብ ውጪ ቤተ መንግስት በመሄድ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የማነጋገር ፍላጎት እንዳላቸው የጠየቁትን የመከላከያ አባላት በሚመሩ የነላይ መኮንኖች ላይ ምርመራ ተጀመረ። በምርመራው መሰረት አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድ ተሰማ። 

የመከላከያ አባላቱ የዕዝ ሰንሰለታቸውን ጠብቀው ጥያቄያቸውን አለማቅረባቸው እና ድርጊቱ ሲፈጸም የቅርብ አላቆች ምን እየሰሩ ነበር ወይም ከድርጊቱ ጀርባ የተወጠነው ውጥን ምን ነበር የሚለው የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል መነጋገሪያ ነበር።

የሰራዊቱ አባላት ወደ ቤተ መንግስት የተላኩበትን ምክንያት ያወቁት በዋናነት የታቀደው እቅድ መክሸፉና በሌላ ተወርዋሪ ሃይል መከበባቸው ከታወቀ በሁዋላ ጉዳዩን የደሞዝና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ ተደርጎ እንዲቀርብ መደረጉን የሚጠቁሙ ክፍሎች፣ የደህንነት ሃይሉ አስቀድሞ መረጃ ደርሶት እንደነበር ይጠቁማሉ።

በዚህም መነሻ ቤተ መንግስት እንደደረሱ መከበባቸውን ያስታወቁት እነዚሁ ክፍሎች በወቅቱ ትጥቅ ከመፍታት በስተቀር አማራጭ እንዳልነበራቸው ይንገራሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሲያነጋግሩም አባላቱ ይቅርታ በመጠየቅ አስፈላጊውን መረጃ ሁሉ ሰጥተዋል። ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም ” ውስጣችን ይፈተሽ” ሲሉ በርካታ መረጃ እንደሰጧቸው ዶክተር አብይ ተናግረዋል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ዘይኑም ቁጥራቸው ፪፵ የሚሆኑት የመከላከያ አባላት በጥብቅ ከበባ ውስጥ ሆነው እንደነበር አመልክተዋል። በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለማነጋገር መፍቀድ እንዳልነባቸው ሻለቃ ዳዊት ወልደጎርጊስ ለቪኦኤ ባስረዱት መሰረት ቢከናወን ኖሮ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን እንደሚችል የዛጎል ምንጮች ተናግረዋል። ጥፋቱ ያለው የሰራዊት አባላቱ ወደ ቤተ መንግስት እንዲሄዱ ከጀርባ ሆነው ያቀናጁት ወገኖችና ሃላፊዎች እንጂ የጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳልሆነም አስረደተዋል። በሃይል ለመመለስ ቢሞከር ቤተ መንግስት ዘልቀው ምንም ባይፈይዱም፣ የመጡት ከነ ሙሉ ትጥቃቸው በመሆኑ ወደ አለመግባባቱ ወደ አልተፈለገ ግጭት ሊለወጥ ይችል ነበር። እዛ የሚከሰተው ችግር ወደ ተለያዩ ክፍሎችም ሊዛመት የሚችልበት አጋጣሚም ሰፊ ነበር። እናም በዚህ መመዘኛ በሰላም አናግሮ መመልሰና በእርጋታ ጉዳዩን አጣርቶ እርምጃውን ከቁንጮው ለመጀመር የተኬደበት አግባብ ትክክል ነው።

የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ሞቱማ መቃሳ ይህንኑ ተከትሎ ሰጡ በተባለው መግለጫ የኢፌዴሪ የመከላከያ ማዕከል ግብረ ሃይል 2ኛ ክፍለ ጦር ሬጅመንት አባላትን ጥያቄዎች በቅርበት ያልተከታተሉ አመራሮችን የመለየትና የማጣራት ስራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።  የሬጅመንት አባላት ጥያቄያቸው ትክክለኛ እና ተገቢ ቢሆንም ጥያቄያቸውን ያቀረቡበት መንገድ ግን የተሳሳተና ህግና ደንብን የጣሰ ነው ብለዋል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *