ክንፉ አሰፋ  – ከሰሞነኛው የ“ፊንፊኔ ኬኛ” ትርክት መሃል፤ ያልጠበቅነው ተዋናይ ብቅ ብሎ የማህበራዊ ድረ-ገጹን አውድ በአንዲት ሃሳብ ይቀይራታል። መልዕክትዋን በደንብ ላላጤነው፤ ትንሽ ፈገግ ማድረጉ አልቀረም። የሶማሌ ተወላጅ ነው። ከግራና ከቀኝ ከተወጠረው ገመድ መሃል ገብቶ፤ ልክ እንደ እብድ ገላጋይ ሶስተኛ ገመድ ይወጥራል።

“በአዲስ አበባችን ላይ፣ አማራ እና አሮሞን የሚያጣላ ምንም ምክንያት የለም። ከተማዋ የኛ፤ የሶማሌ ናት። …እናንት ሰፋሪዎች… ወደ መጣችሁበት፣ ወደ ጎንደር እና ወደ ባሌ ሂዱ…” ይላል ሶማሊያዊው ወንድማችን። ሰዎቻችን በይቅርታ እና በአንድነትን ድባብ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ሲቸለስበት፣ የአዲስ አመት ብሩህ ተስፋ በመጥፎ የአስተሳሰብ ጠረን ሲበከል፣ ታሪክ እና አፈ-ታሪክ እርስበርስ ሲምታቱ፣ የበዓሉን ዓውድ ሊመልስ የሚችለው እንዲህ አይነቱ ኩምክና ብቻ ነው። “ቀልዱን እናንተው ከጀመራችሁ እኔስ ምን ይለኛል?” ማለቱ ይመስላል።

የሶማሌው ተወላጅ ከቀልድ ያለፈ ነገርም ይዟል። ስለ ቦረና እና ባሬንቱ (ሙስሊም ኦሮሞ) የጫራት የታሪክ ሃቅ በዊኪፔዲያ ገጾች ላይም ጉብ ብላለች። ዊኪ፤ በ16ኛው ክፍለ ዘመን በአራቱም አቅጣጫ ስለነበረ የባሬንቱ አሮሞዎች ፍልሰት መረጃ እያጣቀሰ ያነሳል። ልብ በሉ! ዘንድሮ “የሶማሊያ ግዛት እስከ ናዝሬት ነው!” እየተባልን ብቻ አይደለም። በዚሁ ፕሮፓጋንዳዊ አስተምሮት ምክንያት ወገናችን ዋጋም እየተከፈለ ይገኛል። በመቶ ሺዎች የሚቀጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች ከጅጅጋ ተፈናቅለዋል። ትላንት ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ ተብሎ እንደዋዛ ሲነገር የነበረ አፈ-ታሪክ፤ ውሎ ሲያድር ዛሬ ነብስ ሰለመዝራቱ ከዚህ በላይ ምስክር ሊገኝ አይችልም።

አዲስ አቤ ላይ ከሰሞኑ እየተዘፈነች ያለች ይህች የኋላ-ቀሮች ቅላጼ እንዲህ በዋዛ አትታለፍም። የባህሩ ውሃ ጸጥ ስላለ ብቻ ደርሶ መዳፈር ብዙ ያስከፍላል። “ሰፋሪ” እና “መጤ” ሲሉት ሰምቶ እንዳልሰማ ሲያልፍ፣ እነሱ ግን እንደሌለ ከቆጠሩት እጅግ ተሳስተዋል። ጽዋው የሞላ እለት ሱናሚ ሆኖ ሊበላቸው እንደሚችል ቢያውቁ ኖሮ አፍ ከመክፈታቸው በፊት የሚናገሩትን አምስቴ ያስቡበት ነበር። አዲስ አበባ ዘር አታውቅም። አዲስ አበባ የሁሉም ነች። …አዎ አዲስ አበባ የሶማሌ ሳትሆን የሶማሌም ነች!

በምህረት እና በምጽዋት መልክ ባገኙዋት መልካም እድል ላይ ተንጠልጥለው፣ በለቀቁት መርዘኛ መልዕክታቸው ረጂም ርቀት እንደማይጓዙ ግልጽ ነው። በአብሮነት ቋት እየተሳሳረ ያለ ሕዝብን ለመበከል ግን በቂ የሚያስብል መርዝ ረጭተዋል። “ትንሽ ፍሳሽ ትልቅ መርከብ ታሰምጣለች” እንዲሉ፤ በአንዲት መርዘኛ ቃል ምክንያት ስምንት መቶ ሺህ ሕዝብ ያለቀበት የሩዋንዳ ታሪክ ብቻ እማኝ ይሆነናል። በጆርጂስ ሩጊዮ የተነገረች አንዲት የጥላቻ ንግግር፤ ለዚያ እልቂት እርሾ ሆና የዘር ማጥፋት ዘመቻው ተካሄደ። ሩጊዩ በአለም አቀፍ ፍርድ ቤት ቀርቦ ለዚህች መርዘኛ ቃሉ ዋጋ ይክፈልበት እንጂ፤ የሩዋንዳ ቁስል ግን እስካሁን አልሻረም።

እኛም በዚያኛው መንገድ ተጉዘን፤ በቂ ቀውሶችን አልፈናል፣ ህልቀ -ሳፍርት ወገኖቻችንንም ገብረናል። ጥግ ላይ ሆነው የወገን አስከሬን ይቆጥሩ የነበሩ፤ የወንበር ጥመኞች፤ አሁንም ከዚያ መንገድ ፈቅ አላሉም። እነሱ ምን አለባቸው? እንኳንና እሳቱን፤ ወላፈኑም አያውቁት! አርባ አመታት ሙሉ በአንድ መንገድ ብቻ ተጉዘው ከግባቸው ግን ሊደርሱ ያለመቻላቸውን አሁንም አይማሩበትም። የሚያሳዝነው፤ ግን በ21ኛው ዘመን ላይ ሆነውም ከ16ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ ያለመውጣቸው ነው። የሚገርመው፤ አለም ተለውጦ እነሱ አሁንም በዚያው መንገድ ላይ መዋተታቸው ነው። የሰው ልጅ ይማራል። ከህይወቱ ካልሆነ፤ ከስህተቱ ይማራል። ከስህተቱ ካልተማረ ደግሞ ከትውልዱ ይማራል። በዚህ ሁሉ መንገድ አልፎ የማይለወጥ ከሆነ ፤ በላዩ ላይ ትምህርት ቤት አይሰራበት?

የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞች፤ አሸናፊ ሆነው ከተሸናፊነት ስነ ልቦና፣ ትልቅ ሆነው ክትንሽነት ስነ-ልቦና፣ የበላይ ሆነው የበታችነት ስነ-ልቦና ውስጥ አይወጡም። ለዚህም ምክንያቱ ግልጽ ነው። ከዚያ ስነ-ልቦና ከወጡ የፖለቲካ ንግዳቸው ትርፍ አይኖረውም። የንግዳቸው ቢዝነስ ሞዴል የተቀረጸው እንወክለዋለን ያሉትን ጎሳ ማሳነስ፣ ከሌላው እያነጻጸሩ ማጥላላትና ለሱ የማይመጥን ጠላት መፍጠር ነውና። “ጠላቶቻችን የኦሮሞን ሕዝብ ለማጥፋት…” የሚለው የመግለጫቸው ሃረግ ለዚህ እሳቤ እማኝ ይሆነናል። ሕልውናቸው በወገን ስቃይ ላይ የተገነባ በመሆኑም የእርስበርስ እርቅ እና ሰላም ሲፈጠር ነጋዴዎቹ እንደሚጠፉ ያውቁታል። እናም ቁጭታቸው ለታይታ ብቻ የሚቀርብ፤ በኦሮሞ ስም የሚትጫወቱት ቁማር ነው።

“ከዚህ ዘር” ወይንም “ከዚያ ዘር ልሁን” ብሎ ያልተፈጠረው አዲስ አበባ የዚህ ፖለቲካ ሰለባ ቢሆን አይደንቅም። የመኖር መብት ሰጪ እና ከልካይ ሆነው ሲመጡ ግን የሞራል ልዕልናቸው ብቻ ሳይሆን ድፍረታቸው ገደብ እንዳጣ መንገሩ ተገቢ ይሆናል። ቀይ መብራት የሚያሳይ አካል ከሌለ፤ ሰዎቹ በዚህ አካሄዳቸው፣ የሊዝ ግዜያችሁ አብቅቷል። ወይ ጥገኝነት ጠይቁ ወይም ውጡ ስላለማለታው ምንም ዋስትና የለም።

ጥያቄያቸው የመብት ከሆነ፤ አሁን ከምን ግዜውም በላይ ለኦሮሞ ህዝብ ምቹ ጊዜ ተፈጥሯል። ቤተ-መንግስት የተቀመጡት ከኦሮሞ አብራክ የወጡ ዘመናዊ መሪዎች ናቸው። ሕዝቡን ከ”እንገንጠል” አባዜ አፋትተውት፣ ከበዳይ እና ተበዳይ ልቅሶ አውጥተውት፤ ሃገሪቷን መምራት እንደሚችሉ እያሳዩን ነው። የዘር ግንዳቸው ተቆጥሮ ሳይሆን፤ ከኢትዮጵያ አልፈው ስለ አፍሪካ-ቀንድ ውህደት ማለማቸው ነው እውቅና እና ድጋፍ የሚጎርፍላቸው። ከዘውጌ ጠባብ አስተሳሰብ ወጣ በማለታቸው ነው በመላው ሕዝብ የተወደዱት።

ትውልዱን እና ዘመኑን የዋጁ፤ በስልጣኔ ታንጸው “ጣና ኬኛ – ኢትዮጵያ ኬኛ” ብለው እንጂ “ፊንፊኔ ኬኛ” ብለው አልተነሱም። ምክንያቱም ትርክቱ ሕጋዊ እውቅና ሊገኝለት አይችልም፣ ታሪካዊ ማስረጃም አይቀርብበትም። ከሁሉም በላይ ደግሞ የፖለቲካዊ ፋይዳ የለውም። ጠቀሜታው ለፖለቲካ ነጋዴዎች ብቻ ነው። በእርስ-በርስ እልቂት የሚገኝ ትርፍ። አንድ ብሄር ከሁሉም፤ ሁሉም ብሄር ከአንዱ ብቻ የሚላተሙበት ርካሽ ስትራቴጂ።

የኦሮሞ ሕዝብ የረጅም ባህልና ትውፊት ባለቤት ነው። ከኦዳ ዛፍ ስርዓትና ከአባ-ገዳ አስተምሮት ያወቅነው ስለ ይቅር ባይነትና ስለ ቸርነት እንጂ ስለመነጣጠል አይደለም። “ቤት የእግዚአብሄር ነው” ብሎ የሚያስተናግድ እንግዳ ተቀባይ ሕዝብ ነው ኦሮሞ። የዛሬው በቀለ ገርባን ያፈራች ወለጋ የጀግናው ኮሎኔል አብዲሳ አጋን ያፈራች መሆንዋን ለአፍታም መዘንጋት የለብንም። ልክ እንደ በጋው መብረቅ፣ ጀነራል ጃገማ ኬሎ አይነት፤ ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር አብረው የሚራመዱ መሪዎች በዚህ ዘመን ባይፈጠሩ ኖሮ፤ አሁን ከምናየው የባሰ ክፉ ነገር ሊከሰት ይችል ነበር።

ድንክ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች፤ ዘመኑንና ወቅቱን የሚመጥን ስራ ሊሰሩ አይችሉም። የብቃት መመዘኛውን ስለማይወጡት በዘር ተኮር ቅስቀሳ ስልጣን ለመያዝ መቀነታቸውን ታጥቀው የተነሱ ይመስላል። የነሱ ስህተት እጁን አውጥቶ ያልመረጣቸውን ይህንን ሕዝብ “እንወክልሃለን” ማለታቸው ብቻ አይደለም። ባልወከላቸው ብሄር ስም ተደራጅተው ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተት ይፈጽማሉ። የማይገባውን የጠባብነት ስም እያስለጠፉበት፤ አብሮ ከሚኖር ከጎረቤቱ ሁሉ ለማቃቃር መሞከራቸው ነው ትልቁ ስህተት።

“ኦሮሞዎች ፊንፊኔን በኃይል ተነጥቀው እንዲጠፉ ተደርገዋል።…” በማለት ልክ ፤ እንግሊዞች አቦርጅኖችን ከምድረ አውስትራሊያ እንዳጠፉት እና አንግሎ-ሳክሰኖች ደግሞ ሬድ-ኢንዲያን ከአሜሪካ እንዳጸዱ አይነት ወንጀል ተፈጽሟል የሚል ክስ ይዘው ብቅ ብለዋል። የታሪክ ማስረጃ የማይቀርብበት፤ ህጋዊ ሰነድ የሌለውና በስነ-ምድር ጥናት የማይድገፍ ይህ ትርክት ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ የሚቀርብ አፈ-ታሪክ ከመሆን አያልፍም። የዚህ ሃሳብ ጠንሳሾች እንዲህ አይነት ሃላፊነት የጎደለው መግለጫ ከመልቀቅ ባሻገር፤ ከምሁራን ጋር ጠረጲዛ ላይ ቁጭ ብለው ሕዝብን ሊያሳምኑ አይችሉም።

ምዕራባውያን የታሪክ ተመራማሪዎች ያስቀመጡት እውነታ ግን ከነሱ አስተምሮት ጋር ፋጽሞ ይጻረራል።

አክቲቪስት አቻሜለህ ታምሩ፤ ጆሃን ክራፕፍ የተሰኘ ጀርመናዊ ያታሪክ ምሁርን ጠቅሶ በማህበራዊ ገጹ የለቀቀው፤ “ፊንፊኔ ልክ እንደ የካ፣ ገላንና ጉለሌ ራሷን የቻለች መንደር፤ የየካ፣ የገላንና የጉለሌ ጎሳዎች አካል ያልሆነ የራሷ ጎሳ ይኖርባት የነበረች እንጂ የየካ፣ የጉለሌና የገላን ጎሳዎች የመኖሪያ፣ የእርሻና የግጦሽ ቦታ አልነበርችም።” ይለናል። በቀላል አማርኛ ፊንፊኔ አንድ መንደር ናት። ልክ እንደ ስድስት ኪሎ፣ አራት ኪሎ፣ ፒያሳ እንጂ አዲስ አበባና ፊንፊኔ አንድ አይደሉም። ታሪክ የሚነግረን ይህንን ነው። ይህ መራራ ሃቅ እንጂ ደብተራ የጻፈው ታሪክ አይደለም።

በነሱ አባባል አዲስ አቤዎች “መጤ እና ሰፋሪዎች” ሳይሆኑ ይልቁንም የቱለማ፤ ሜጫ እና ከረዩ ኦሮሞዎች ፈልሰው የሰፈሩበት ስፍራ ነው። እነዚህ ሰዎች፤ ከላይ በተጠቀሱት የአዲስ አበባ ቦታዎች መች እንደሰፈሩም መች እንደሰፈሩም ጭምር ይተቅሳሉ ጀርመናዊ ያታሪክ ምሁር።

የ”ሰፈራ” እና “ወረራ” እሰጥ እገባ እና ገመድ ጉተታ ውስጥ ገብቶ መዋተቱ ለማንም አይጠቅምም እንጂ፤ የ16ኛው ክፍለዘመን ታሪክ የሚነግረን ከኦነጎቹ ፕሮፓጋንዳ የተለየ ነው። እዚያም ቤት እሳት አለ እንዲሉ፤ መርዘኛ ፖለቲካቸውን የሚያረክስ አያሌ እውነታዎችን ማቅረብ ይቻላል። አፈ-ታሪክን ተንተርሶ ሳይሆን በጥናት እና ምርምር የተረገጠ እውነታ። በኮሎኝ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናትና ምርምር ፕሮፌሰር የሆኑት ማሪን ገርስት በ16ኛው ክፍለ ዘመን የነበረው የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራምራ ጽፋለች። ማን ወራሪ፤ ማን ፈላሽ፤ ማን ሰፋሪ እና ማን ነዋሪ እንደነበር ይህ ጥናት በግልጽ አስምጦታል። ፕሮፌሰርዋ በጥናታቸው ዋቢ ከሚያደርጉዋቸው ምሁራን ውስት ደግሞ የኦሮሞ ታሪክ ተመራማሪ የሆኑትን ዶ/ር መሃመድ ሃሰንም ይገኙበታል። እውነቱን የሚሹ ሁሉ ስለ አጼ ሶስንዮስ እና ስለ አጼ ፋሲለደስ ዘመን የተጻፈውን የምርምር ስራ ማየት ተገቢ ይሆናል።

የዘር ፖለቲከኛ እንደ መርገምት የተጫነባት ኢትዮጵያ፤ የታሪክ ዝንፈት አዲስ አይደለም። በዘውጌ የተቃኙ ታሪክ ጸሃፊዎችም ከዋናው የታሪክ አስተምሮት (Mainstream historiography) የወጣ፤ ለራስቸው የሚመች ታሪክ ሲጽፉ ምክንያት አላቸው። አንዱን ባንዱ ለማነሳሳት!

ሶርያን ያየ በእሳት አይጫወትም። የመንን ያልተመለከተ የሰቆቃን ምንነት አያውቃትም። ከሊቢያ የማይማር ካለ ድንጋይ ብቻ ነው። ይህንን የ ”ሰፈሪ” ፖለቲካ የሚያራምዱ ወገኖች ከሁሉም ጋር የተዋለደ እና የተሳሰረውን የሮሞ ሕዝብ ከማን እና ከማን ጋር እያላተሙት እንደሆነ በደንብ ይረዱታል። የፖለቲካ ነጋዴዎቹ እንዲያተርፉ ሲባል የኦሮሞ ሕዝብ አሁንም ብዙ ድግስ ይጠብቀዋል። ለራሳቸው የፖለቲካ ትርፍ ብቻ ሲሉ ይህንን ታላቅ ሕዝብ ከምስራቅ፣ ከምራብ፣ ከሰሜን እና ከደቡብ ደም እያቃቡት እንደሆነ ያስተውሏል።

ከዳር ቁጭ ብሎ የሚታዘባቸው ግን አንድ ጥያቄ ይጠይቃል። ኦነጋውያን የሚኒሊክ ቤተ-መንግስትን እስኪይዙ ድረስ ስንት ኦሮሞ ማለቅ አለበት? በስሙ የሚነገድበት ይህ ሕዝብ ከስንቱ ወገኑ ጋርስ መላተም አለበት? በደቡብ ከጌዲዮ ጋር ደም አቃቡት። በምስራቅ ከሶማሌው ይፋለማል፣ በምእራብ ከሸዋው፣ ከቤን ሻንጉል፣ በሰሜን ደግሞ ከአማራው የጦር አዋጅ ያውጁለታል፣ … ዛሬ ደግሞ ከአዲስ አበባ ጋር ክፉኛ ሊያላትሙት የጦር ነጋሪት ነፍተዋል። ለነሱ የፖለቲካ ትርፍ ሲባል ብቻ፤ የኦሮሞ ወገኖቻችን ከአማራ፤ ከጉራጌ፣ ከጋሞ፣ ከጌዲዮ እና ከሶማሌ ጋር እንዲጋጭ እልቂትን ደግሰውለታል። የአራቱ ድርጅቶች ጠላቶቻችን እያሉ የጠቀሱትን መግለጫ ያስተውሏል?

የሰው ልጆች ሕይወት የተከፈለበት የዘር ቁርሾ ከኋላችን ጥለን፣ በይቅርታ የምንሻገርበት የአዲስ አመት አዋጅ ገና ተነግሮ ሳያበቃ፤ “የእኛ – እና – የእናንተ” ፖለቲካ ቀማሚዎች መድረክ ላይ ወጥተው፤ የአብሮነትን ድባብ በአጓጉል ትርክት በከሉት። የይቅርታን መንፈስ በጥላቻ መርዝ ከለሱት።

ባትሪ እንደጨረስች መኪና ጉልበት ሲከዳቸው፤ ከተኙበት ተነስተው የበዳይ እና ተበዳይ ስሜት እየቀሰቀሱ፤ በብሄር እና በአዲስ አበባ ላይ ማቅራራት አዲስ አይደለም። ህወሃትም ማጠፊያው ባጠረበት ግዜ ከመሳቢያ የሚያወጣት ዶሴ ነበረች። መዘዙ ግን አዲስ አበባ ላይ አያቆምም። አፍንጫ ሲመታ አይን ያለቅሳል፤ እንዲሉ ጉዳዩ እንደ ዶሚኖ እየተንከባለለ ከጫፍ ጫፍ የሚነሳ ሰደድ እንዳይሆን ያሰጋል።

የሰዎቹ ችግር ግልጽ ነው። አመክንዮ አልባ በሆነ ትውፊት ተወጣጥረው አንዳች የለቲካ እና ፖለቲከኛ ቁመና ሳይገነቡ ቆዩና፤ መድረኩን ይዘው ማጠፊያ አጠራቸው። ሃሳባቸውን ገበያ አውጥተው እንዳይሸጡ የሃሳብ ካዝናቸው ነጠፈ። በሰለጠነው አለም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሃሳብ ይዘው ይፋለማሉ። የጡንቻ ሳይሆን የሃሳብ ጉልበቱ ጠንከር ያለ ይዘርራል። የተዘረረም ሽንፈቱን በጸጋ ተቀብሎ፣ ለባላንጣው መልካሙን ተመኝቶ ይሄዳል። ሰብቅ አይስብም። ዘውጌ ፖለቲካ ውስጥ ሃሳብ የለም። እናቱም አባቱም ዘር ነው። በብሄር የተደራጁ ሃይሎች ችግር ለገበያ የሚያቀርቡት ሃሳብ ያለመኖር ነው። ዘር ይዘው ብቅ ይሉና እንደ ሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ ያደነቁራሉ። ስለዚህ ሌላ ታሪክ መፈጠር አለበት። በአፈ-ታርክ የተቃኘን የታሪክ አስተምሮት! ይህች ደግሞ ሃሳብን ጠረጴዛ ላይ አስቀምጠው ለመወያየት ሞራላዊም ሆነ ምሁራዊ ድፍረቱ የሌላቸው ሰዎች ትርክት ናት። ከየማዕዘናቱ የሚነሳው አውሎነፋስ አዋራውን ሲጠራርግ ገመናቸው ተገለጠ።

ፖለቲካው በኢትዮጵያ ኬኛ ሲቃኝ እነሱ ተኝተው ካልነበረ፤ ይህንን ያረጀ ትርክት ለማንሳት አሁን ግዜው አልነበረንም። መሬት የብሄረሰብ መሆኑን እነ በቀለ ገርባ ነግረውናል። በመንጌ ግዜ መሬት የሕዝብ ነው ተብለን ነበር። በመለስ ግዜ ደግሞ መሬት የመንግስት ነው ‘አራት ነጥብ’ ተባልን። መሬት በብሄረሰብ ባለቤትነት ሲያዝ ግን ይህ በታሪክ የመጀመርያው መሆኑ ነው።

ምህረት ተድርጎላቸው ሃገር ቤት የገቡት፤ እነ ሌንጮ ለታ እና እነ ዲማ ብልህ ቢሆኑ ኖሮ የተሰጣቸውን ተቀብለው ዝቅ ብለው መብረር ነበረባቸው። ዛሬ ደርሰው እዩኝ እዩኝ ማለቱ ረፈድ ሲል ደብቁኝ ያስብላቸዋል። መካሪ ቢኖራቸው ኖሮ የበደኖን ቁስል ባይቀሰውሱት፣ የወተርን አጽም መልሰው ባይወጉት ይነግራቸው ነበር። ዝምታ ወርቅ ነው!

የፍሪደም ሃውስ ሲኒየር ኦፊሰር፤ ጆሴፍ ባድዋዛ በወሩ መግቢያ ላይ በኒውዮርክ ታይምስ ሲመሰክሩ፤ “…ውጭ የነበሩት (ኦነጎች) መግባት በጎ አቅጣጫ ይዞ ይጓዝ የነበረው የፖለቲካ ምህዳር አወሳሰበው፤ መልካሙን ድባብም እምቅ ውስጥ አስገባው።” ይላሉ። ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐብይ አሕመድ ለእነዚህ፤ መለያየትን እና መገንጠልን የሚያራምዱ የፖለቲካ ድርጅቶች ጥሪ በማድረጋቸው ምክንያት ለዚህ ችግር መዳረጋቸውንም ይገልጻሉ።

ጠቅለል ሲል ሰዎቹ ለሃገሪቱ መፍትሄ ሳይሆን ፈተና ነው የሆኑት።

እነዚህ ሰዎች አሁንም ግንድን ከዛፍ እንገንጥል የሚሉ ከሆነ ከጥንቱ አልተማሩም። አለም አንድ እየሆነች ስትመጣ፤ አሁንም መለያየትን የሚሰብኩ ከሆነ፤ እንመራዋለን ከሚሉት ሕዝብ ሺህ ማይሎች ኋላ ናቸው። ታግሎ፤ እነሱንም ነጻ ባወጣቸው በዚህ ስልጡን ሕዝብ አናት ላይ ቁጭ ብለው ስለ “እኛ እና እነሱ” ፖለቲካ እየደሰኮሩ አሁንም አልሰለጠኑም።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *