የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለሁለት ቀናት ድነገተኛ  የስራ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ ገብተዋል። መንግስት ጉብኝታቸው በሁለቱ አገራት መካከል የተጀመረውን አዲስ ግንኙነት ለማጠናከርና የተለያዩ ስምምነቶች ለመፈጸም መሆኑ ቢገልጽም ጉዳዩ በዋናነት ኦነግን ለመሸምገል እንደሆነ ተጠቁሟል።

በኦነግ ስም ከሚጠሩት አንዱን ክንፍ ከሚመሩት አቶ ዳውድ ኢብሳ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ከትጥቅ መፍታት ጋር በተያያዝ የተነሳውን አለምግባባት ለመጨረሻ ጊዜ ለመሸምገል አዲስ አበባ መግባታቸውን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ለዛጎል ጠቁመዋል። 

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የኦሮሚያ ባለስልጣን እንዳሉት መንግስት ከኦነግ ጋር በትጥቅ ጉዳይ የተነሳውን ውዝግብ በአፋጣኝ እልባት የመስጠት ፍላጎት እንዳለና በተለያዩ ደረጃዎች ንግግር እየተደረገ መሰንበቱን ጠቁመዋል። ሻዕቢያ አቶ ዳውድ ለስድስት ዓመታት እስር ላይ ከቆዩ በሁዋላ ከእስር ቤት እንዲያመልጡና አስመራ እንዲገቡ የረዳቸውና ህይወታቸውን ያተረፈላቸው ድርጅት መሆኑ የሚታወቅ ነው።

የኦነግ ደጋፊዎችና ርዳታ አድራጊዎች በመሰላቸት አቶ ዳውድ ላይ ከፍተኛ ዘመቻ በማድረግ አዲሱ ትውልድ ከሳቸው እንዲነጠል፣ ድጋፉን እንዲያቆም፣ መዋጮውን እንዲገታ ቢደረግም አቶ ዳውድ ግን ወደ ኢትዮጵያ እስከተመለሱበት ቀን ድረስ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር እጅግ የጠበቀ ግንኙነት ነበራቸው። ወደ ኢትዮጵያ ለመግባትም ንግግር ሲደረግ ኢሳያስ አፉወርቂ ሚና ነበራቸው።

አቶ ዳውድ ኢብሳ ሰራዊታቸው ትጥቅ እንደማይፈታ በመንግስት ሚዲያ ቀርበው ምላሽ ከሰጡ በሁዋላ ከመንግስት ወገን ተቃውሞውና ምላሹ እየተካረረ በመሄዱ አቶ ኢሳያስ ይህንን ጉዳይ በማሸማገል የወዳጅነት ሚናቸውን ለመወጣት አዲስ አበባ እንደገቡ፣ አዲስ አበባ ከመግባታቸውም በፊት ንግግር ማደረጋቸውን የዜናው ሰዎች አመልክተዋል።

ኦነግ ትጥቅ አልፈታም ማለቱን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፣ ጉዳዩ በአስቸኳይ መፍት እንደሚያገኝ በተናገሩ ቀናት ውስጥ አቶ ኢሳያስ አዲስ አበባ መግባታቸው ከላይ የመረጃው ሰዎች ያሉትን የሚያጠናክር እንደሆነ አመላካች ተደርጎ ተወስዷል። አቶ ዳውድም ቢሆን ከቪኦኤ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በቀጥታም ባይሆን በተለሳለሰ መልኩ ድርድር እየተካሄድ እንደሆነ የሚያመላክት ምላሽ ሰጥተዋል።

አቶ ዳውድ ከአስመራ ይዘውት የገቡት አንድ ሺህ አምስት መቶ የሚጠጋ ሰራዊት በዛላምበሳ በኩል ወደ አገር ቤት ከገባ በሁዋላ ትጥቅ ፈቶ በካምፕ ውስጥ እየኖረ ሲሆን፣ አሁን ትጥቅ አንስተዋል የሚባሉትን ሃይሎች ማን እያስታጠቃቸው ነው የሚለው ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል። የመከላከያ ኤታምጆር ሹም ቅዳሜ በሰጡት መግለጫ ከፍተኛ የሚባል ትጥቅ በኮንትሮባንድ መልክ አገሪቱ ውስጥ እንደሚገባ ተናግረዋል። ከዚህ የመሳሪያ ሸመታና ማስተላለፍ ጀርባ የሚሰሩ መኖራቸውንም ይፋ አድርገዋል።

ፕሬዚዳንት ኢሳያስን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን  አቀባበል አድርገውላቸዋል። በቆይታቸውም በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ወደ ተግባር ከተሸጋገረ ጊዜ አንስቶ ጥልቀት እያገኘ በመጣው በሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት ዙሪያ ውይይት እንደሚያደርጉ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ፍፁም አረጋ ጠቅሶ ፋና ዘግቧል። ከዚህም በተጨማሪም በንግድና ልዩ ልዩ ትብብሮች ዙሪያ ውይይት እንደሚያካሂዱ ተመልክቷል።

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አገር ለማተራመስ በህቡዕ የተደራጁ በርካታ ግለሰቦችን ከነመዋቅራቸውና መስሪያዎቻቸው በቁጥጥር ስር አዋለ፤

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *