5 የኦሞ ኩራዝ ስኳር ፕሮጀክቶች በደቡብ ኦሞ ዞን መገንባታቸውን ተከትሎ በጂንካ ከተማ በ18 ነጥብ 2 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው የከረጢት ፋብሪካው “ኮርፖሬት ኒው ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት” በተሰኘ ተቋም ግንባታው ተጠናቆ የሙከራ ምርት ማምረት ችሎ ነበር።

ሆኖም ፋብሪካውን የሚያስተዳድረው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን አምርቶ መሸጥ ለሚችል 3ኛ ወገን ሳያስተላልፍ በመቆየቱና ለሙከራ የቀረበው ግብዓትም በማለቁ አሁን ፋብሪካው ምርት ማቆሙን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በስፍራው ባደረገው ቅኝት አረጋግጧል።

የጅንካ ከረጢት ፋብሪካ በሙከራ ወቅት ከ400 ሺህ በላይ ከረጢት ያመረተ ሲሆን፥ ፍብሪካው ለሚመለከተው አካል አለመተላለፉን ተከትሎ የገበያ ትስስር ሊፈጠርለት አልቻለም።

ከዚህ ባሻገርም ፋብሪካው በራሱ በብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የውስጥ ስምምነት መሰረት 130 ሰራተኞችን ቀጥሮ እንዲንቀሳቀስ ሲያደርግ ቢቆይም፥ በተጠቀሱት ምክንያቶች ስራ እንዲያቆም ሲደረግ 89 ሰራተኞች ከስራ እንዲሰናበቱ መደረጉ እና በበረሃ አበል ክፍያ ላይ ችግሮች መኖራቸው ቅሬታ እንዲፈጠር አድርጓል።

የጅንካ ከረጢት ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ቀረብህ ህብስቱ እንደተናገሩት፤ ፋብሪካውን ተረክቦ ምርት እያመረተ መሸጥ ለሚችል አካል ለማስተላለፍ እና የሙከራ ምርቶቹንም ለመሸጥ የጨረታ ማስታወቂያ ወጥቶ ክትትል እየተደረገ ነው።

የፋብሪካው የሰው ሃይል አስተዳደር አና ልማት ሃላፊው ሺህ አለቃ ማጆር ተሰማ በበኩላቸው ከስራ ገበታቸው የተሰናበቱ ሰራተኞች ፍብሪካው እስኪተላለፍ ድረስም ቢሆን እንዲመለሱ እና የክፍያ ቅሬታቸውም ውይይት እንዲደረግበት መወሰኑን ገልፀዋል።

የጅንካ ከረጢት ፋብሪካ በሙሉ አቅሙ መስራት ሲጀምር በአመት 30 ሚሊየን ከረጢት የማምረት አቅም ያለው ሲሆን፥ በሙከራ ወቅት በቀን ከ100 ሺህ በላይ ከረጢት የማምረት ብቃት እንዳለው ተረጋግጧል።

በሶዶ ለማ – ፋና ብሮድካስቲንግ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *